ናጋርጁነኮርንደ

ከውክፔዲያ
ናጋርጁነኮርንደ ፍርስራሽ

ናጋርጁነኮርንደ በአሁኑ አንድረ ፕረደሽሕንድ ምናልባት ከ90 እስከ 340 ዓም ግድም ድረስ የቆየ ቪሃረ ወይም የቡዲስም ገዳም፣ መቅደስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነበር። ዛሬ የሚታወቀው በተለይ ከሥነ ቅርስ ፍርስራሽ ነው።

የስሙ ትርጉም የናጋርጁነ ኮረብታ (ቴሉጉኛ፦ ኮርንደ) ነው። ናጋርጁነ የመሃያነ ቡዲስም ወገን ዋና ፈላስፋ ነበር። እርሱም በልማድ መሠረት በዚያው ቦታ ምናልባት እስከ 240 ዓም ገደማ ይኖርና ፍልስፍናውን ያስተምር ነበር። ይህ በስነ ቅርስ ገና አልተረጋገጠም።

አሁን ከስነ ቅርስ እንደሚታወቅ፣ የቦታው ስም በዚያን ጊዜ «ቪጃየፑሪ» ተባለ፤ «ናጋርጁነኮርንደ» የሚለውም ስም በኋላ ከመካከለኛው ዘመን ተሰጠው።

ተቋሙ በሳተቫሀነ ሥርወ መንግሥት እንደ ተሠራ ይታስባል። ከሳተቫሀነ ንጉሥ ጋውታሚፑትራ ሳታካርኒ ስድስተኛው አመተ መንግሥት (90-100 ዓም ግድም) የሆነ ጽሁፍ ተገኝቷል። ከሳተቨሀነዎች ቀጥሎ በነገሠው አንድረ ኢክሽቫኩ ሥርወ መንግሥት ዘመን (217-317 ዓም ያህል)፣ ቪጃየፑሪ ዋና ከተማቸው ሆነ። ይሁንና እነዚህ ነገሥታት ሁሉ በእኩልነት የቡዲስምና የሂንዱኢዝም ደጋፊዎች ነበሩ እንጂ ሁላቸው የቡዲስም አባላት አልሆኑም። በቦታውም የሂንዱ ህንጾች ደግሞ ተከሉ።

3ኛው ክፍለ ዘመን ዓም ብዙ ገዳሞች የተገኙበት ዝነኛ ተቋም ሆነ። ተማሮች ከመላው ሕንድ ወይም ከስሪ ላንካ ወይም ከቻይና ይደርሱ ነበር።

ከአንድረ ኢክሽቫኩዎች በኋላ፣ ተቋሙ በካዳምባ ሥርወ መንግሥት ንጉስ መዩረሸርመ እጅ 340 ዓም ግድም እንደ ጠፋ ይታስባል። በ1500 ዓም አካባቢ ሥፍራው «ናጋርጁነኮርንደ» ተብሎ እንደ አምባ ተጠቀመ።