አዲስ ዘመን (ጋዜጣ)

ከውክፔዲያ

አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥር የምተዳደር ነዉ ፣ በየዕለቱ የሚታተም ብሔራዊ ጋዜጣ ነው። አዲስ ዘመን በአሁኑ ጊዜ ከ ፵ በላይ ጋዜጠኞች ያሉት ሲሆን የጋዜጣው መጠን ‘መካከለኛ’ /በርሊነር/ (31.5 cm × 47 cm (12.4 in × 18.5 in) ) ሆኖ የፊትና ጀርባ ገፆችን በሙሉ ቀለም ያቀርባል። ይህ ጋዜጣ የአገሪቱ ብቸኛው ዕለታዊ ጋዜጣ ሲሆን የመንግሥትን አቋም የሚያንፀባርቅ እና በየዕለቱ የተለያዩ ልማታዊ ዜናዎችን ይዞ ይወጣል።

ታሪካዊ ሂደት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከአምሥት ዓመት የኢጣልያ ወረራ በኋላ የኢትዮጵያ ነፃነት መመለሱን ተከትሎ ንጉሠ ነገሥቱ ዙፋናቸው እንደ ተረከቡ ካከናወኗቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ተግባራት አንዱ የመገናኛ ብዙኀን በማደራጀትና በማቋቋም ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህም መሠረት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅዳሜግንቦት ፴ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም በይፋ ሥራ ጀመረ። [1]

ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከጠላት ወረራ በኋላ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ሲገቡ ባደረጉት ንግግር የመግቢያው አንቀጽ፦

«የሰማይ መላእክት የምድር ሠራዊት ሊያስቡትና ሊያውቁት ይቻላቸው ባልነበረ በዚህ በዛሬው ቀን ቸር እግዚአብሔር በመካከላችሁ ለመገኘት ስላበቃኝ በሰው አፍ የሚነገር ምስጋና የሚበቃ አይደለም። ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው፣ ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚሁ በአዲሱ ዘመን ሁላችንም መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል።» [2] የሚል ነበር::

የጋዜጣውም ሥያሜ «ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ ነው» ማለታቸውን መሠረት ያደርጋል።

የጋዜጣው ድረ-ገጽ ስለጋዜጣው ታሪክ ሲዘግብ፤«የመጀመሪያ ዕትም ባለሁለት ገፅ፣ አርበ ጠባብ /ታብሎይድ/» (43.2 cm X 27.9 cm (17 in X 11 in)) እንደነበረና ስርጭቱም ፲ሺ ቅጂ እንደነበር ይገልጽና፤በዚሁ የመጀመሪያ ዕትም ርዕሰ አንቀጽ «"የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጀመር" በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ ‹ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነቱን ሥራ ይሠራ ዘንድ ተመሠረተ› በማለት የተቋቋመበትን ዓላማ ያስረዳል» ይለናል። ቀጥሎም ያንኑ የመጀመሪያውን ርዕሰ አንቀጽ በመጥቀስ፤ «‹ይህ ጋዜጣ የፕሮፖጋንዳ ጋዜጣ ሳይሆን እውነትን፣ አገልግሎትን፣ ረዳትነትን መሰረት አድርጐ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ በአዲስ ሥራ ተመርቶ እንዲረዳ የቆመ ነው› ቢልም ‹አገልግሎት ስንል የኢትዮጵያን ነፃነት ሲመሰስ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው፤ የነበራቸውን ጥቅም ሁሉ አስወግደው፤ ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ሲሉ የሰው አቅም ሊሸከመው የማይችለውን ድካም ተቀብለው፤ ማናቸውም ሰው ሊያደርገው ያልቻለውን በኢትዮጵያ ሕይወት ውስጥ እስከ ዛሬ ያልታየውን ሥራ ከፍፃሜ ላደረሱ ለንጉሠ ነገሥታችንና ላቆሙት መንግሥት የሚያገለግል እንዲሆነ ነው።› በማለትም በዋነኝነት የተቋቋመበትን ዓላማ በግልፅ ይተነትናል።» የሚል ዘገባ እንደነበር የጋዜጣው ድረ-ገጽ አስቀምጦታል።

አዲስ ዘመን ከተጀመረበት ጊዜ እስከ ታኅሣሥ ወር ፲፱፻፶፩ ዓ/ም ድረስ በየሳምንቱ፤በአርበ-ጠባብ፣ በመካከለኛና በአርበ-ሰፊ /ብሮድሺት/ (74.9cm X 59.7cm (291⁄2 in X 231⁄2 in)) መጠን ሲታተም ከቆየ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፲፱፻፶ ዓ/ም ያቋቋመው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ ጽሕፈት ቤቱን አዲስ አበባ ላይ ማድረጉን ምክንያት በማድረግ የጋዜጣው ዕትመት በሳምንት ወደ ስድስት ቀን ተሸጋግሯል።

መስከረም ፩ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ/ም ጀምሮ ደግሞ ጋዜጣው ከሰኞ እስከ እሑድ በሳምንት ሰባት ቀናት ወደመታተምከተሸጋገር በኋላ የጋዜጣው መጠን ከታኅሣሥ ፫ ቀን ፳፻፬ ዓ/ም ጀምሮ ወደ መካከለኛ ጋዜጣነት /በርሊነር/ ዝቅ ብሏል።

ማጣቀሻ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  1. ^ http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/about-addis-zemen Archived ጃንዩዌሪ 15, 2013 at the Wayback Machine ; "የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አጀማመርና አጭር ታሪክ"
  2. ^ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፣ “የታሪክ ማስታወሻ” (፲፱፻፷፪ ዓ/ም)፤ ገጽ ፬፻፲፰

ዋቢ ምንጭ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]