ኡር-ዛባባ
ኡር-ዛባባ በሱመራዊ ነገሥታት ዝርዝር ዘንድ ኪሽ በሱመር ላዕላይነቱን በያዘበት ጊዜ የኪሽ ንጉሥ ነበር።
በነገሥታት ዝርዝሩ ዘንድ ከኩግባው በኋላ በኪሽ የገዙት 7 ወይም 8 የሱመር ነገሥታት ይዘረዝራሉ። ከነዚህ መካከል አንዱ ብቻ የኩግባው ልጅ ልጅና የፑዙር-ሲን ልጅ ኡር-ዛባባ ከሌላ ሰነድ ታውቋል። ሌሎቹ በሱመር ሁሉ እንደ ገዙ አጠራጣሪ ነው። በዚህ ዘመን ሁሉ (ከኩግባው በፊትና እስከ ታላቁ ሳርጎን ድረስ) ሉጋል-ዛገ-ሢ የኡሩክ ንጉሥ መሆኑ ይታወቃል፣ ስለዚህ የኪሽ ላዕላይነት በሙሉ ለበጣም ረጅም ዘመን አልነበረም። በዝርዝሩ ዘንድ ኡር-ዛባባ ለማይመስል ያህል ዘመን ለ400 ዓመታት ገዛ ቢለን፣ አንዱ ቅጂ ግን ለ6 ዓመት ገዛ ሲል፣ ይህ ቁጥር ከዚያው ዕውነት ይመስላል እንጂ። ከዚህ በኋላ ዝርዝሩ የአካድ ንጉሥ ሳርጎንን «የኡር-ዛባባ ዋንጫ ተሸካሚ» ይለዋል።
«ሳርጎንና ኡር-ዛባባ» የተባለው ሰነድ ደግሞ ኡር-ዛባባን ይጠቅሳል።[1] በዚሁ ጽሑፍ ዘንድ፣ ሳርጎን ከኡር-ዛባባ ሎሌዎች መካከል የቤተ መንግሥት አስረካቢ ሲሆን፣ ንጉሡ ኡር-ዛባባ ሕልምን አይቶ ሳርጎንን የ«ዋንጫ ተሸካሚ» ማዕረግ ሾመው፣ ይህም በመጠጦች (ጠጅ) ሳጥን ላይ ሓላፊነቱን ያለው ማለት ነው። ከዚያ ሳርጎን በራሱ ሕልም ኡር-ዛባባ በደም ወንዝ ውስጥ ሲሰመጥ ያያል። ስለዚህ ኡር-ዛባባ ሰምቶ እጅግ ተቸግሮ ሳርጎንን በተንኮል ለመግደል ያቅዳል። ሳርጎን የንጉሥ ተልዕኮ ሆኖ አንድ መልዕክት በጽላት ለኡሩክ ንጉሥ ሉጋል-ዛገሢ እንዲወስደው አዘዘ። መልዕክቱ ግን መልዕክተኛውን ስለ መግደል የሚል ልመና ነበር። ሰነዱ ተሰብሮ ከዚያ በኋላ ምን እንደ ሆነ ቢያጣም፣ ሳርጎን የአካድ መንግሥት መሥራች ለመሆን ስለ በቃ ሴራው እንዳልተከናወነ መገመት እንችላለን።
ሌላው ኡር-ዛባባን የሚጠቅሰው ሰነድ የባቢሎን መቅደስ ዜና መዋዕል (ወይም «የቫይድነር ዜና መዋዕል» [2]) የተባለው ጽላት ነው። ዜና መዋዕሉም እንዲህ ይተርካል፦ ኡር-ዛባባ ዋንጫ ተሸካሚውን ሳርጎንን የመቅደሱን ወይን ጠጅ መሥዋዕት እንዲቀይር አዘዘው። ሆኖም ሳርጎን ይህን ትዕዛዝ በደንብ አልፈጸመም፣ በኋላም የአካድ ንጉሥ ቢሆንም በመጨረሻ የሱመር አረመኔ አማልክት ሳርጎንን ቀጡት በማለት ይጨምራል።
የኡሩክ ንጉሥ ሉጋል-ዛገ-ሢ ወደ ዘመኑ መጨረሻ ኪሽን እንዳጠፋው ይታወቃል። ከትንሽ በኋላ ግን ሉጋል-ዛገሢ እራሱ በሳርጎን ተገለበጠ። ሳርጎን ደግሞ በኡር-ዛባባ ውድቀት ሚና እንዳጫወተ ብዙ ጊዜ ይገመታል፣ ይህ ግን ከተገኙት ጽላቶች ግልጽ አይደለም።
ቀዳሚው የኪሽ ንግሥት ኩግባው |
የሱመር (ኒፑር) አለቃ 2091-2085 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ የኡሩክ ንጉሥ ሉጋል-ዛገ-ሲ |
ቀዳሚው ፑዙር-ሲን |
የኪሽ ገዢ 2091-2085 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ ዚሙዳር |
- ^ የሳርጎን ትውፊት (እንግሊዝኛ)
- ^ "ABC19". Archived from the original on 2006-02-28. በ2013-06-21 የተወሰደ.