Jump to content

ኣዞ

ከውክፔዲያ
ሁለት ሕፃን አዞዎች

ሳይወድሙ ከቀሩት ሕያው ገበሎ አስተኔዎች መካከል አዞዎች ይገኙበታል። እኒህ አዞዎችም በጥቂት ዝርያዎች ብቻ የሚወከሉ ናቸው። በዓለም ላይ 23 የሚሆኑ ዝርያዎች አሏቸው።

አዞዎች ረዘም ብሎ ጠንካራ የሆነ የራስ ቅል አላቸው። በዛ ያሉ ጠንካራ ጥርስ አፋቸው ውስጥ ተደርድረው ይታያሉ። ውኃና ምግብ በአፋቸው በያዙበት ጊዜ እንኳን መተንፈስ የሚያስችላቸው ተፈጥሮ አላቸው።

አዞዎች እንቁላል ጣዮች ናቸው። ከ20 እስከ 50 እንቁላሎች ብስባሽ ቅጠላ ቅጠሎች ውስጥ ጥለው እናቶቻቸው ይጠብቋቸዋል። ይህም እንቁላሉ ሊፈለፈል ሲቃረብ ከእንቁላሉ ውስጥ የሚሰሙት ድምፅ እንቁላሉን ሰብረው ጫጩቶቹ እንዲወጡ ለማድረግ ያስችላቸዋል። እንደ ኤሊዎችና አንዳንድ እንሽላሊቶች ሁሉ እንቁላሎቹ የተጣሉበት ሁኔታ (ጎጆ) የሙቀት መጠን የሚፈለፈሉትን ጫጩቶች ጾታ ይወስናል። ሆኖም ከኤሊዎች በተቃራኒ የእንቁላሉ ጎጆ የሙቀት መጠን መቀነስ ሴቶችን፣ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ደግሞ ወንዶችን እንዲፈለፈሉ ያደርጋል።

አዞዎች ከኢሊጌተሮች በቀላሉ ይለያሉ። የአዞ ጭንቅላት ከዓይኑ አካባቢ ጀምሮ ወደ አፍንጫው ሲወርድ እየጠበበ ይሄዳል። መንጋጋው በሚዘጋበትም ጊዜ ታችኛው መንጋጋ ውስጥ የሚገኘው ትልቅ ጥርስ ወደ ውጭ ይወጣል። የአሊጌተር ጭንቅላት ግን ከዓይኑ ጀምረን ወደ አፍንጫውም ስንሄድ እኩል ስፋት ያለው ነው። ታችኛው መንጋጋ ውስጥ የሚገኘው ጥርስም ገጦ አይወጣም። በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት አሊጌተሮች ይገኛሉ። አንደኛው በደቡብ ምሥራቅ አሜሪካ ሌላኛው በቻይና ሲገኝ፤ አዞዎች ግን በሁሉም የዓለም ክፍል ይገኛሉ።

ሁሉም አዞቻች አምፊቢየስ ይባላሉ። ምክንያቱም ታዳጊዎቹም ትልልቆቹም ከፊሉን ጊዜያቸውን ውኃ ውስጥ ከፊሉን መት ላይ ስለሚያሳልፉት ነው። በአንፃራዊ ሁኔታ መሬት ላይ ያላቸው እንቅስቃሴ እዚህ ግባ የማይባል ነው። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች ሲያስገድዱ ግን አካላቸውን ከፍ በማድረግ አጭርና ወፍራም በሆነ እግራቸው ለአጭር ርቀት በራማያስገርም ፍጥነት ይሮጣሉ። ባሕር ዳርርቻ ላይ ፀሐይ እየሞቀ ያለን አዞ ለመቅረብ በጥንቃቄ መሆን አለበት። ምክንያቱም ብዙዎቹ ሰውን እንዳዩ ወዲያው ወደ ውኃው ዘለው ይገባሉ። አንዳንድ የተራቡ ካሉ ግን በቀጥታ ወደሚጠጋቸው ሰው በመቅረብ ጥቃት ያደርሳሉ።

ረጅምና ጠንካራ ጭራቸው እንደ መሣሪያ በማገልገል ሰውንም ሆነ ሌላ እንስሳ ፊቱ ላይ መትቶ በመጣል ለጥርሳቸው ያቀርብላቸዋል። በውኃ ውስጥም ባላቸው ፈጣን እንቅስቃሴ ከእነሱ ለማምለጥ ከባድ ይሆናል።

ለረጅም ጊዜ ከውኃ ሥር ሆነው መቆየት ቢችሉም እንደሌሎቹ ገበሎ አስተኔዎች በሳምባ የሚተነፍሱ ናቸው። ስለዚህም አፍንጫቸውን ከውኃው በላይ በማውጣት አየር ይስባሉ። አፍንጫቸው ከላይ ስለሚገኝ ጫፉን ብቻ በማውጣት በቀላሉ አየር ሊስቡ ይችላሉ። ብዙዎቹ አዞዎች ከውኃ ዳርቻ አካባቢ ዋሻ ይሠራሉ። የዋሻው መግቢያ ከውኃው ሥር ሊሆን ቢችልም ብዙው ክፍል ግን ከውኃው በላይ ነው። ዋሻውን ለማረፍና ደኅንነቱን ለመጠበቅ ሲገለገልበት እንዳንዴም አዞው የገደለውን እንስሳ (ሰውን ጭምር) ተሸክሞ ይዞ መጥቶ ተረጋግቶ (ተዝናንቶ) የሚመገብበት ሆኖ ይገኛል።

ሁሉም አዞዎች እንቁላል ይጥላሉ። እንደሌሎቹ ገበሎ አስተኔዎችም እንቁላሎቹን መሬት ውስጥ ይቀብራሉ። ሴቶቹ አዞዎች በሚሠሯቸው ጎጆዎች ይለያያሉ። አንዳንዶቹ አሸዋ ውስጥ ቀዳዳ በመቆፈር እንቁላሉን ይቀብሩትና ይሸፍኑታል። ሌሎቹ እንደ አሊጌተር ዓይነቶቹ ብዛት ያለው የበሰበሰ ቅጠላ ቅጠፀል በመሰብሰብ እዛ መሃል እንቁላሉን ይጥሉታል። ብዛት ያላቸው ደርዘን እንቁላሎች (እያንዳንዱ በመጠን ከዶሮ የበለጠ) በአንድ ቁጭታ ሊጥሉ ይችላሉ። ሲፈለፈሉ ታዳጊዎቹ አዞዎች ከ22-25 ሳንቲ ሜትር ቁመት ይኖራቸዋ”ል።

አዞዎች ጥርሳቸውን በተደጋጋሚ ይተካሉ። የሚተካው (ያረጀው) ጥርስ ሥር ያለው አዲስ ጥርስ ሲሆን፤ አዲሱ ተኪ ጥርስ አድጎ ትልቅ ካልሆነ በስተቀር አሮጌው ቶሎ ብሎ ወልቆ አይወድቅም።

-ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹ባለአከርካሪዎች›› (2004)

ሪፖርተር፤ 'ኪንና ባህል' - "አዞዎች" (እሑድ ኅዳር ፲፬ ቀን ፳፻፯ ዓ/ም)[1] Archived ኤፕሪል 4, 2015 at the Wayback Machine የአዞ አይን 360 ዲግሪ ማየት ይችላል። እንዲሁም ሰው 180 ዲግሪ ዘውሮ ማየት ይችላል።