ኤዎስጣጤዎስ
ኤዎስጣጤዎስ | |
---|---|
ከሜትሮፖሊተን ሚዩዚየም የተገኘ ስዕል | |
ኢትዮጵያዊ ቅዱስ | |
የተወለዱት | ሐምሌ ፳፩ ቀን ፩ሺ፪፻፷፭ 15 July 1273 (በጁሊያን ቀን አቆጣጠር)22 July 1273 (በጎርጎርያን ቀን አቆጣጠር) |
የአባት ስም | ክርስቶስ ሞዐ |
የእናት ስም | ስነሕይወት |
የትውልድ ቦታ | ፂራ፣ እንድርታ (ሰሜንምሥራቅ መቀሌ) |
ያረፉበት ቀን | መስከረም ፲፰ ፩ሺ፫፻፵፭ አርሜኒያ |
የሚከበሩት |
በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በበኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአርሜኒያ ቤተክርስቲያን |
የንግሥ ቀን | መስከረም ፲፰[1] |
የሚታወቁት | ስለሰንበት ያላቸው እምነት |
በግዕዝ፡ ኤዎስጣቴዎስ ወይም ዮስጣቴዎስ፣ በጥንት ግሪክ: Εὐστάθιος ሲነበብ ኤዎስታቴዎስ፣ ከሐምሌ ፭ ቀን ሺ፪፻፷፭ – ሺ፪፫፵፬ በኢትዮጵያ ሰለሞናዊ መንግሥት አገዛዝ
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ታላቅ መሪ የነበሩ አባት ናቸው። በጣም አጥብቀው ከሚያስተምሩት ትምህርት ስለ ሰንበት መከበር ነበረ። ተከታዮቻቸው የኤዎስጣጤዎስ ቤት ወይም በግል ሲጠሩ ኤዎስጣጤዎሳውያን ይባሉ ነበር ለተዋህዶ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው።
የኤዎስጣጤዎስ መጀመሪያ ስማቸው ማዕቀበ እግዚ ሲሆን ከእናታቸው ከስነሕይወትና ከአባታቸው ከክርስቶስ ሞዐ ሐምሌ ፳፩ ቀን ፩ሺ፪፷፭ ተወለዱ። እኒህም ደጋግና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ነበሩ ። ኤዎስጣጤዎስ የታወቀውን ደብራቸውን (ደብረ ፀራቢን) የመሠረቱት የተወለዱበት ቦታ እዛው (እንድርታ) እንደሆነ ገድላቸው ይገልፃል። በወጣትነታቸው ዘመን በሺ፪፸፪ አካባቢ ከአጎታቸው አባ ዳንኤል (የደብር ስማቸው አባ ዘካርያስ) ቆርቆር (ደብረ ማርያም) አስተዳዳሪ ጋር እንዲኖሩ ወደ ገራልታ ይላካሉ። አባ ዳንኤልም ኤዎስጣጤዎስን ተቀብለው ተገቢውን የሃይማኖት ትምህርትና የደብር ሕይወትን ካስተማሩ በኋላ ማዕቀበእግዚ በ፲፭ ዓመቱ ቅስና ሥራዬ መሆን አለበት ብሎ በወሰደው ውሳኔ መሠረት ስሙ ኤዎስጣጤዎስ ተብሎ ተሰየመ።
ኤዎስጣጤዎስ ከአባ ዳንኤል የቅስና መዐረጋቸውን ካገኙ በኋላ የራሳቸውን ደብር በ(ሰራይ) መሠረተው በዚያም በማስተማር ብዙ ተማሪዎችን አፈሩ ። በሰንበት ላይ ያተኮረ አመለካከታቸውን ለይተው ያስተምሩ ነበር ፣ የሚቃወማቸው አቡነ ያቆብ ፫ኛው አስኪመጣ ድረስ። ከዛ ግን ከተከታዮቻቸው ከባካርሞስ ፣ መርቆርዮስ ፣ ገብረእያሱ ጋር ኢትዮጵያን ለቀው ወደ ግብፅ (ካይሮ) ገብተው በአሌክሳንድሪያው ጳጳስ ቢንያም ፪ኛው ፊት በሰንበት ባላቸው አመለካከት ፀንተው ከዛም ወደ ኢየሩሳሌም አምርተው በመጨረሻም የሕይወታቸው ማብቂያ ወደ ሆነችው አርሜኒያ ገብተው ኖሩ[2]። የኤዎስጣጤዎስ የሰንበት አመለካከት የሚከተለው ነበር፡ ቅዳሜና እሁድ ፡ዝቅተኛውና ዋናው ሰንበት ፣ የቅዳሜው ለብሉይ ኪዳን ሲሆን የእሁዱ ደግሞ ለጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ለአዲስ ኪዳን ማለት ነው ። ይህንንም ከመጻሕፍ ቅዱስ ከአሥርቱ ቃላትና ከአዲስ ኪዳን ተረድተው እንጂ የገዛራሳቸው አመለካከት እንዳልነበር የሃይማኖት ታሪክ ዘጋቢዎች[3] ያስታውቃሉ ። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም የሁለቱንም ቀን ሰንበትነት አክብራ ትጠቀምበት ነበር ፣ በተወሰነ ጊዜ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ስሕተት ነው ብላ እንዲቀር እስካረገቺው ቀን ድረስ ማለትም ከኤዎስጣጤዎስ መነሳት በፊት ።
ኤዎስጣጤዎስ ከአረፉ በኋላ የሰንበቱን ሥርዓት ተከታዮቻቸው በሰፊው ማስተማሩን ቀጠሉ። አገራቸውን ኢትዮጵያን ሲለቁ መኃበረሰባቸው እንዳይበተን አንድ ባለአደራ የቅርብ ተከታያቸው የሆነ አብሳዲ የሚባል በቦታቸው አስቀምጠው ነበር የሄዱት ። ይህም የደብር አለቃ ለ፲፬ ዓመት ማለትም ኤዎስጣጤዎስ ከነደቀመዝሙራቸው ጋር አገር ለቀው ያለኤዎስጣጤዎስ እስኪመለሱ መኃበረሰቡን አንድ አርጎ መጠበቅ ትልቅ ፈተና ሆኖበት ነበር ። ከዚያ ግን ተመልሰው በመጡት ዱቀመዝሙሮች እርዳታ በደብረ ማርያም አዲስ መኃበረሰብ ለመመሥረት በቅቷል ። ቆይተውም እነዚህ ደቀመዝሙሮች ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ተበትነው የኤዎስጣጤዎስን የሰንበት አመለካከት በማስተማርና አዳዲስ ደብሮችን በመክፈት አልፈው የመንፈሳዊ ማዕረግ አሰጣጥ በራሳቸው ደንግገው ይተዳደሩ ነበር ። ይህ ጠንካራ አቋማቸው በሺ፬፻፵፪ ዓ ም በተጉለት በተደረገው የደብረምጥማቅ ጉባኤ ዓፄ ዘርአ ያዕቆብ የግብፁን መሪ የተጠቀሰውን የሰንበት ሥርዓት አምኖ እንዲቀበል አድርገዋል ።
- ^ ታሪካቸው በኢትዮጵያ ሥንክሳር በመስከረም ፲፰ የሰማዕታትና ቅዱሳን ታሪክ ውስጥ ይነበባል
- ^ ታሪካቸው በኢትዮጵያ የእንግሊዘኛ ሥንክሳር Archived ጃንዩዌሪ 2, 2019 at the Wayback Machine ወይም በEthiopian Synaxarium (ጉግል ፕሌይ ስቶር ላይ በሚገኘው አፕ.) በመስከረም ፲፰ የሰማዕታትና ቅዱሳን ታሪክ ውስጥ ይነበባል
- ^ ታደሰ ታምራት Church and State in Ethiopia (Oxford: Clarendon Press, 1972), page 209