እማሆይ ገላነሽ አዲስ

ከውክፔዲያ


እማሆይ ገላነሽ አዲስ_፲፰፻፹፱᎗፲፱፻፸፰ ስለ አንዲት ስመ-ጥሩ ኢትዮጵያዊት መምህርትና ባለ ቅኔ ታሪክና ማንነት ስናስታውስ ‘ጽላሎ ይበልጣል አንቺ ያለሽበቱ‘ የተባለላቸውንና ሣር ቅጠሉ አድናቆቱ የቸራቸውን እማሆይ ገላነሽ አዲስን ከጽላሎ አማኑኤል ሳናነሳ አናልፍም።

ከቄስ ገበዝ ሐዲስ ኪዳናትና ከወ/ሮ ወርቅነሽ እንግዳ በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት በይልማና ዴንሳ ወረዳ በሚገኘው ደብረ ጽላሎ አማኑኤል በ፲፰፻፹፱ ዓ.ም ተወለዱ። በእናት አባታቸው ቤትም በንክብካቤ አደጉ። አባታቸው የሚያስተምሩትንም ቅኔ ሥራዬ ብለው ይከታተሉ ነበር።

የስምንት ዓመት ልጅ እያሉ አንድ ቀን ከእናታቸው ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ። በሴቶች መቆሚያ ከእናታቸው ፊት ተቀምጠው እንዳሉ በዚያው ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉት ከሥርዓተ ቅዳሴው በኋላ ቅኔ ይዘርፋሉ።

“በታቦርሂ አመ ቀነጸ መለኮትከ ፈረስ” ማለትም መለኮትህ ፈረሰ በደብረ ታቦር ተራራ በዘለለ ጊዜ ብለው ቄስ ገበዝ ለዓለሙን ሲጀምሩ፡ ገላነሽ ሐዲስ ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ከተቀመጡበት ተነሥተው “ኢክሀሉ ስሂቦቶ ሙሴ ወኤልያስ” አሉና ነጥቀው እርፍ። ትርጉሙም ሙሴና ኤልያስ ሊስቡት አልቻሉም ብለው አባታቸውን በጉባኤ መካከል ነጥቀዋቸው መወድሱን ጨርሰውታል። አባታቸውም እዚያው ጉባኤ መካከል አዚምላት በማለት ተናግረዋል ይባላል። በኋላም መልሰው እንዲህ አሏቸው፡ “ወእንዘ ትትናገሪ ዘንተ በአድንኖ ክሳድ ወርእስ በከመ አነ ስማዕኩክ ኢይሰማዕኪ ጳውሎስ።“

ይህ ጳውሎስ በመልእክቱ ሴቶች በጉባኤ መካከል ገብተው እንዳያስተምሩ የተናገረውን ቃል በማስታወስ እኔ እንደ ሰማሁሽ ይህንን ስትናገሪ ጳውሎስ እንዳይሰማሽ ለማለት ነው።

ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የተሰባሰቡት ሊቃውንትና ሕዝብ ይህ ምስጢር እንደተገለጸላቸው ባዩ ጊዜ፤ በሁኔታው በመገረምና በመደነቅ ካህናቱ በወረብ፥ ጎበዛዝቱ በሆታ ሴቱ በእልልታ ገላነሽን እያመሰገኑ መንገድ ጀመሩ። እንደ ንግሥት ጉዞ በአልጋ ሆነው መጋረጃ ተጋርዶላቸው እቤታቸው ደረሱ። ሕዝቡም ከፍ ያለ የደስታ ግብዣ አድርጎ ሰነበተ።

ይህ ደስታ ብዙም ሳይቆይና ስሜቱ ሳይደበዝዝ ገላነሽ ሕይወት ላይ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጠረ። በለጋ ዕድሜያቸው ኩፍኝ በተባለ በሽታ ይያዙና ዓይኖቻቸው የማየት ብርሃናቸውን ያጣሉ። ይሄን ጊዜ አባታቸው የቤተ ክህነት ትምህርት እንዲጀምሩ በማድረግ ዳዊትን፣ ውዳሴ ማርያምን፣ ቅዳሴ ማርያምን፣ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን እንዲሁም ለዘመናት ሲያስተምሩት / ከሃምሳ ዓመታት በላይ የኖሩትን ቅኔን ከነ-አገባቡ በሚገባ እንዲያጠናቅቁ ያደርጋሉ። ለካ የዚያን ጊዜዋ ገላነሽ ሐዲስ ዐይናቸው እንጂ ልባቸው ብርሃን ነበረ።

ገላነሽ አባታቸው ካስተማሯቸው በኋላ በመምህርነት ይመርቋቸውና በአባታቸው ጉባኤ ውስጥ ተቀምጠው በየተራ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። ለአካለ-መጠን ሲደርሱ ወላጆቻቸው “እኛ ከሞትን ማን አላት? ባል ታግባና ልጅ ትውለድልን” ብለው በማሰብ በዚሁ ገዳም ጽላሎ አማኑኤል አካባቢ ተወልደው ያደጉ ነገር ግን የቤተ ክህነት ትምህርት ያልተማሩ አቶ ጥሩነህ በላይ የተባሉትን ሰው አጋቧቸው። ባል ያግቡ እንጂ ከወላጆቻቸው ቤት ሳይወጡ አብረው እየኖሩ ሲያስተምሩና አባታቸውን ሲረዱ በማኅበራዊ ክንዋኔዎችም ሲሳተፉ ኖረዋል። በዚህ ትዳራቸው አዳም ጥሩነህና መሠረት ጥሩነህ የተባሉ ወንድና ሴት ልጆች አፍርተዋል። ሦስተኛ ልጃቸው ግን በሕፃንነቱ ሞቶባቸዋል።

ገላነሽ በዚህ ሁኔታ ኑሯቸውን እየገፉ ባሉበት ጊዜ ፲፱፻፳፰ ዓ.ም የጣልያን ፋሽስት መንግሥት ሀገራችንን ኢትዮጵያን ወረረ። የጽላሎ ሕዝብ ገዳሙን ትቶ በመሸሽ ጫካ ገባ። ቄስ ገበዝ ሐዲስ፣ ባለቤታቸው፣ ልጃቸው ገላነሽ ከሊቃውንቱም ከመነኰሳቱም የተወሰኑት “ቤተ ክርስቲያናችንን እንዴት ትተን እንሄዳለን” በማለት በዚያው በገዳም ቀሩ። የጣልያን ጦርም በሚያሳዝን ሁኔታ እዚያ ያገኛቸውን ሊቃውንትና መነኰሳት የገላነሽን ወላጆች ጨምሮ በግፍ ገደላቸው። ገላነሽ ዐይነ ሥውር ሰለ ነበሩ ሳይገድሏቸው ከሞት አመለጡ። ወላጆቻቸውን በሞት በመነጠቃቸው ግን ሕይወታቸው ጎደሎ ሆኖ ነበር።

ገላነሽ የገጠማቸውን መከራ ተቀብለው በመመንኮስ ሀገር ሰላም ሲሆን ከዚያው ከአባታቸው ቦታ ላይ ጉባኤያቸውን አጠናክረውና አስፍተው የተጠሩበትን የቅኔ መምህርነት በመቀጠል ማስተማሩን ተያያዙት። ተማሪው ዝናቸውን ከየሀገሩ እየሰማ በእርሳቸው እየተደነቀ ለመማር ይጎርፍ ነበር። በቅኔ መምህርነት በቆዩባቸው ኅምሳ ዓመታት ውስጥ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከትግራይ፣ ከኤርትራና ከሸዋ ክፍላተ ሀገራት እንዲሁም ከላስታና ከላሊበላ የተሰበሰቡበትን አንድ ሺ ሰባት መቶ ሃምሳ ተማሪዎች አስተምረዋል። ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍላተ-ሀገር የመጡ ሠላሳ ስድስት መሪጌቶችን በቅኔ መምህርነት አስተምረው ብቁ መሆናቸውን በመመስከር አረጋግጠዋል።

እማሆይ በመማር ማስተማር ሥራ ላይ ሴቶች ከወንዶች እኩል መሆናቸውን ሁልጊዜ ይናገሩ ነበር። ይህንንም ቀሲስ ከፍያለው መራሒ “ሴቶች በኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸውት ይገኛል። እማሆይ “መማርም ሆነ ማስተማር ብርታትን እንጂ ጾታን አይመለከትም። ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ተሰልፈው መሥራት የኖረ እንጂ እንደ እንግዳ ደራሽ አይደለም” ይሉ ነበር። ለዚህም ማስረጃ ሲጠቅሱ መምህራችን ክርስቶስ ሴቶች ደቀ-መዛሙርቱን ሂዱና ትንሣኤዬን ንገሩ ብሏቸውላና ልዩነት የለም ይላሉ።

እማሆይ ገላነሽ አዲስ በጠባያቸው አስተዋይ ብልህና ንቁ እንዲሁም ቅን አሳቢ ሰው እንደነበሩ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ። ችኩልነትንና ሽንፈትን የማይወዱ የማስተማር ፍቅር የተሰጣቸው የዘመናችን ታላቅ ሴት ናቸው። እማሆይ ዐይነ-ሥውር ይሁን እንጂ ዐይነ-ሥውርነታቸው ሴቶች ከሚያከናውኗቸው ድርጊቶች አልገታቸውም። ልጅ ወልደው ያሳደጉ፣ በቀለም ያጌጡና የተሸለሙ ስፌቶችን ይሰፉ፡ ከዐይናማዎች እኩልም ፈትል ይፈትሉ ነበር። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ለሌሎች ከብደው እንዳይገኙ በዚህ ሞያቸው በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን ያስተዳድሩ ነበር።

ለብዙ ሰዎች ዐይነ-ሥውር መሆን ድቅድቅ ጨለማን ያህል ከባድ ነው። እንደ እማሆይ ያሉ መንፈሰ-ጽኑ ሰዎች የዐይን ብርሃን የላቸውም ግን ያያሉ፣ ጆሮአቸውም ላይሰማ ይችላል ግን ያዳምጣሉ፣ አንደበታቸውም ተዘግቶ ሊሆን ይችላላ ግን ዲዳ አይደሉም። እማሆይ ገላነሽ ዐይነ-ሥውርነታቸው ከማየት ከመመራመር ከማስተማር አልከለከላቸውም።

እማሆይ ገላነሽ ለብዙ ዘመናት ሊቃውንት በማፍራትና በጥሩ ሥነ-ምግባር ያሳለፉ፣ በአካባቢያቸው ሕዝብ ዘንድም ዝናን ያተረፉ ሊቅ እናት እንደሆኑ ታሪካቸው ምስክር ነው።

እማሆይ ገላነሽ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በባሕር ማዶ ሣይቀር ዝናቸው የታወቀ በመሆኑ ከውጭ ድረስ እየመጡ የተለያዩ ግለሰቦች ይጠይቋቸው እንደነበር ይነገራል።

የእማሆይ ገላነሽ ሐዲስ ሥራዎች ለግእዝና ለአማርኛ ቅኔዎች ዕድገት አስተዋጽዖ በርክተዋል። ለምሳሌ ያህል የአማርኛና የግእዝ ሁለት ቅኔዎቻቸውን ወስደን ብንመለከት የእማሆይ ገላነሽ ቅኔዎችን የምሥጢር ጥልቀትና ርቀት የቋንቋ ምጥቀት መገንዘብ ያስችለናል።

፩. ተርቢኖስ በኩር

እመ ኢበልዐ በልዐ

ምግበ ገድል ጸገብኩ

ኢይቤ ቤተ ሃይማኖት ጽኑህ

ትርጉም፡

ተርቢኖስ በኩር የተባለ አለቃ ጽኑ ከሆነ የሃይማኖት ቤት የተጋድሎን ምግብ ቢበላም ባይበላም በቃኝ ጠገብኩ አይልም።

ሰም፡

ሥት ያለበት አለቃ ሰው እንጀራን ቢበላም ባይበላም ጠገብኩ አይልም።

ምስጢር፡

ተርቢኖስ ማለት ጊዮርጊስ ነው። እሲም ሰማዕት ነው፡ የሰማዕታት አለቃ ነው። ስለዚህ ከሰባ ነገሥታት ጋር ሰባት ዓመት ተጋድሎ ሲያደርግ ከሃይማኖቱ ጽናት የተነሣ ደከመኝ ሰለቸኝ፣ ጠገብኩ ሳይል መከራን ስቃይን ተቀብሏል ሲሉ ነው።

፪. የአማርኛ መወድስ ቅኔ

የአንተ ስጦታ ዓባይ

ዲካ የሌለው

ስለማይደርስበት ይብስት

ሞልቶ ፈሰሰ በዓለም

የልብህ ጥበብ ፈለግ

እየፈለቀ ከጎጃም

ማዕከለ ባሕር አልቆመ

ድልድይ ስመ እንቲአከ

ዘበየማን ወጸጋም

ይሻገሩ ዘንድ ወዳጆችህ

ሊቃውንተ ሥርዓት ወሕግ

የመረጥካቸው ቀደም

ለዓለም ወለዓለም

ጥበብስ እመ ተከልኮ

በማይናወጽ ገዳም

የፍሬ ምስጋናን አፈራልን ሁሉን የሚጠቅም

ቀርበን ብናየው በዓይን

እስከ ሥሩ ነው ለምለም

በቅዱስ እጅህ ተባርኳልና የእርሱ ልምላሜ አይጠወልግም።

ለአብነት ያህል ይህንን ጠቀስን እንጂ መምህርቷ በቅኔዎቻቸው ውስጥ ብዙ ጉዳዮችን አመስጥረው ይገኛሉ። በተቀኟቸው ቅኔዎች ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ቅኔዎች አመስጥረዋል። ከዚህ በመነሳት እማሆይ ሃይማኖተኛና መንፈሳዊነትን የተላበሱ እንደነበሩ እንዲሁም ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው በጥልቀት የተረዱ እናት እነደነበሩ ለማየት ይቻላል።

እማሆይ ገላነሽ እርጅና እየተጫናቸው ሲመጣ ቀድሞ የሚሠሩትን የእጅ ሥራ ለመሥራት ባለመቻላቸውን የምትረዳቸው ሴት ልጃቸው ትዳር በመያዟ የደረሰባቸውን ችግር በመስማት የካቲት ፴ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ.ም በባላምበርስ ዘገየ ገብረ ወልድ አሳሳቢነት በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሕንፃ በአንድ ጽ/ቤት ውስጥ ጊዜያዊ የርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ የበኩሉን ወገናዊ አስተዋጽዖ ተወጥቷል። እርሳቸውም በአንድ ወቅት “ከቤተ ክህነት ወይም ከሌላ የሚሰፈርልኝ ቀለብ የለም። በሥጋ የሚዛመዱኝ ጉልማ ያርሱልኛል። ተማሪዎቼም ተቀኝተው ለመምህርነት በቅተው ሲሄዱ የሰሌን ጥላና ምንጣፍ ሠርተው ያን ሸጠው ለበረከት ይሰጡኛል። የኔ ሕይወት ቅኔ ነው የቅኔ ዓይነት መዝረፍ፣ ሌላ ሕይወት የለኝም። ከተማሪዎቼ የተለየ ምቾት አላገኘሁም። በዚህም አላዝንም” በማለት በህልውናቸው በኑሯቸው በኩል ያለውን ጉዳይ በማቃለል ዘወትር ይናገሩ ነበር።

በዚህ ሁኔታ ከኖሩ በኋላ በተወለዱ በሰማንያ ዓመታቸው ባደረባቸው ሕመም ምክንያት የቅኔዋ ምንጭ እማሆይ ገላነሽ አዲስ ከነማይጠገብ ለዛቸው ሐምሌ ፲፪ ቀን ፲፱፫፸፰ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ባደጉበትና ባስተማሩበት በደብረ ጽላሎ አማኑኤል ገዳም ተፈጽሟል።

እማሆይ ገላነሽ ሐዲስ ቤተ ክርስቲያንና ታሪክ ሊዘክራቸው የሚገቡ የዘመናችን የአጥቢያ ኮከብ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሴቶች ቦታ ባላገኙበት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በቅለው ለዚያውም ዐይነ-ሥውርነት ተጨምሮበት ነጥረው የወጡ ስመ-ጥሩ ሴት ናቸው። ለዚህም ነው ዓለም የሃያኛው ክፍለ ዘመን አስገራሚ ከሆኑት ሴቶች መካከል አንዷ መሆን የሚገባቸው።

በአሁኑ ሰዓት በባሕር ዳር ከተማ በእኅት ልጃቸው በአቶ ተሾመ አዲስ አማካይነት መታሰቢያ ሙዝየም ተዘጋጅቶላቸው ሥዕላቸው በትልቁ ተስሎና አንዳንድ ቅኔዎቻቸው ተሰብስበው ተቀምጠዋል። ሙዝየሙን የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ በርናባስ ጥር ፳፫ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም መርቀው ከፍተውታል።

እማሆይ ገላነሽ አዲስ ሕይወታቸውና ቅኔዎቻቸው / ሥራዎቻቸው ሊጠኑ ከሚገባቸው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አንዷ መሆናቸውን ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል።]

[ምንጭ፡

ሰሎሞን ሐዲስ ፤ የእማሆይ ገላነሽ ሐዲስ ዘጽላሎ አማኑኤል የሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸው፥ ለመጀመሪያ ዲግሪ ከፊል ማሟያ የቀረበ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል፤ እ.ኢዮ ፲፱፻፺ ዓ.ም]