Jump to content

ደብረ ታቦር (ከተማ)

ከውክፔዲያ
ደብረ ታቦር
አጼ ቴወድሮስ እጅ የተሰራው ታቦር መድሃኔ አለም ቤ/ክርስቲያን
አገር  ኢትዮጵያ
ክልል አማራ ክልል
ዞን ደቡብ ጎንደር
ከፍታ 2,706
የሕዝብ ብዛት
   • አጠቃላይ 39,052
ደብረ ታቦር is located in ኢትዮጵያ
{{{alt}}}
ደብረ ታቦር

11°51′ ሰሜን ኬክሮስ እና 38°1′ ምሥራቅ ኬንትሮስ


ደብረ ታቦር (በሌላ ስሟ ጁራ ) በደቡብ ጎንደር አስተዳደር ከጣና ሓይቅ ሰሜናዊ ምስራቅ 50 ኪሎ ሜተር ርቃ የምተገኝ በተራሮች የተከበበች ከተማ ናት። በከተማይቱ ዙሪያ 48 ምንጮች መኖራቸው ለከተማይቱ እድገት ከፍትኛ አስተዋጾ ቢያደርጉም በ20ኛው ክፍለ ዘመን የባህር ዛፍ ተክል በከተማይቱ መሰራጨት ምንጮቹ እንዲደርቁ አድርጓል። የደብረታቦርን መሰረት የጣለው የ14ኛ ክፍለዘመን ንጉስ አጼ ሰይፈ አርድ (1327-1372) ነበር። በዚህ ንጉስ ዘመን የታቦር እየሱስ ቤ/ክርስቲያን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ታነጸ።[1] ራሱና ልጆቹ ለከተማይቱ መቋቋም አስተዋጾ ቢያበረክቱም ከተማይቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሰፊው የምትጠቀሰው አጼ ቴወድሮስ እና ከዚያም ቀጥሎ አጼ ዮሐንስ ፬ኛ እንደ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በማገልገል ነው። ከዚያም በዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ታላቁን እና ገናናውን ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንቁ ተደርጎ ተመስርቷል አሁንም ድረስ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ነው ። ዛሬ ከተማይቱ ስትነሳ ደብረ ታቦር ኢየሱስን የማያስብ ለጉብኝት የመጣም ሳይጎበኘው መሄድ አይታሰብም ። ደብረ ታቦር(ጁራ) የ19ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ዋና ከተማ በመሆን አገልግላለች። ተጭነው ስለተለያዩ የከተማይቱ ክፍሎች መርጃ የሚያገኙበት ካርታ እዚህ ይገኛል

አጼ ሰይፈ አርድ (1344-1372) በደብረታቦር ተራራ (እየሱስ ተራራ) ላይ የእየሱስ ቤክርስቲያንን መሰረቱ ይህ ቤ/ክርስቲያን አሁን ድረስ ከዚያ ዘመን የመነጩ ቅርጻቅርጾች ሲኖሩት ነገር ግን በ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ራስ ጉግሳ ሙርሳ በቤተክርስቲያኑ አጠቃላይ ለውጥ አድርገዋል። ስለሆነም በቤ/ክርስቲያኑ የሚገኙ ስዕሎች ባብዛኛው ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ዋዜማ የሚመነጩ ናቸው። ለደብረ ታቦር ከተማም ከደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ቀጥሎ የሚጠራ ደብርም ነው። [2]

የደብረታቦር ስም በአጼ ልብነ ድንግል ዜና መዋዕል ላይ ሰፈረ።

በ1700ወቹ መጨረሻ አካባቢ አሊ ጓንጉል (ትልቁ አሊ) የተባለ የየጁ ስርወ መንግስት መሪ በደብረ ታቦር አካባቢ ሃይለኛ መሪ በመሆን ከሱ በኋላ ለ80 ዓመታት ያክል የጸና ስርዓት በአካባቢው እንዳንሰራፋ ባህሩ ዘውዴ መዝግቧል [3] እንደ ታሪክ አጥኝው ሞርድካይ አብር አስተያየት የደብረታቦርን ከተማ የመሰረታት ይሄው ትልቁ አሊ ነበር። እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክኸርስት ግን ራስ ጉግሳ ሙርሳ ነበር።

በ1800 አካባቢ ራስ ጉግሳ ሙርሳ የተባለው የበጌምድር መሪ (1803-25) ደብረ ታቦርን እንደ ጦር ቅጥር በተራሮች መካከል መሰረተ። በትውፊት ሲነገር ራስ ጉግሳ ደብረታቦርን የመረጠበት ምክንያት አንድ መነኩሴ «ሴት አቦ ሸማኔ አድነህ በምትገልበት ቦታ ከተማህን አሰራ» ብሎ ስላዘዘው ነበር ይባላል። ሮቢንሰን የተባለ የታሪክ አጥኝ ስለ ራስ ጉግሳ ሲናገር «በዚህ በ19ኛ ክፍለ ዘመን አጥቢያ ላይ ራስ ጉግሳ ከሁሉ የኢትዮጵያ መሳፍንት ይልቅ የአገሪቱን አንድነት የበለጠ የሚወክል ነበር። በዚህ ምክንያት ከሞተም በኋላ ደብረታቦር የአገሪቱ የፖለቲካ ማዕከል እና መምሪያ ልትሆን በቃች»[4] ራስ ጉግሳ 1825 ላይ ደብረታቦር ላይ ሲሞቱ እ.ኤ.አ ግንቦት 25፣ ሰኞ ዕለት እየሱስ ቤተ ክርስቲያን ቀብራቸው ሆነ። ዘመኑ በታሪክ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ የሚታወቀው ሲሆን ለ27 ዓመት ራስ ጉግሳ የአገሪቱ እንደራሴ በመሆን አገልግለዋል። በእየሱስ ቤ/ክርስቲያን የርሱ ተከታይ መሪወች ኢማምማርየ እና ዶሪ የተባሉትና የዶሪ የአጎት ልጅ ራስ አሉላ አሊ (ትንሹ አሊ) እንዲሁ ተቀብረዋል። እንደ ታሪክ አጥኝው ማቲወስ ለኒህ መሪወች ማስታወሻ በጎንደር ግንብ ዘዴ የተሰራ የእንቁላል ግንብ በእየሱስ ቤ/ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ቆሟል። ከቤ/ክርስቲያኑ አጠገብም ቤ/መንግስቱ ይገኝ ነበር። አሊ አሉላ (አሊ ትንሹ) በቤተመንግስቱ የውጭ ቆንጽላወችን ያስተናግድ እንደንበርና እስካሁን ድረስ ለፍርድ እርሱ ይቀመጥበት የነበር የሚባል የድንጋይ ዙፋን በአካባቢው እንደሚገኝ ማቲወስ የተሰኘ የታሪክ አጥኝ ይገልጻል። [5]

በ1830 ራስ ማርየድብረ አባይ ጦርነት ላይ ሲወድቅ የርሱ ወንድም ራስ ዶሪ ተተክቶ ስልጣን ላይ ወጣ። በ1830 መጨረሻ ላይ ከ ማይ እስላማይ ጦርነት መልስ ራስ ዶሪ በጸና ታሞ ደብረ ታቦር ላይ ሲደርስ በሞት አለፈ። የገዛበትም ዘመን 3 ወር ብቻ ነበር [6]። የደብረታቦር መሪወችና አለቆች የዶሪን የአጎት ልጅ የሆነው ትንሹ አሊን በ12 ዓመቱ ለመሪነት መረጡት። የአሊ አባት አሉላ በወቅቱ በህይወት አልነበረም። አሊ ሞግዚቶች የነበሩት ቢሆንም በርግጥ እናቱ ወይዘሮ መነን በርሱ ቦታ አገሪቱን ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት አስተዳድራለች።[7] ወይዘሮ መነን በተለይ በታሪክ የምትታወቀው አባ ገብረ ሐናን በተለያዩ ገዳማት እየላከች ስላስተማረች ነው። በነዚህ ዘመናት የከተማይቱ የህዝብ ቁጥር ማደግና ማነስ አሳይቷል፣ ይህም ከነበረው ከፍተኛ ጦርነት የተነሳ ነበር። ገንዘብ በ10% አራጣ የሚያበድር ኪዳነ ማርያም የሚባል ነጋዴ በከተማይቱ እንደነበር የፈረንሳይ ተጓዦች ሳይጠቅሱ አላለፉም [8]

የተወናበደው ጦርነት
[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በ1841 መጨረሻ ላይ የጎጃም አስተዳዳሪ ብሩ ጎሹ እና የሰሜኑ ራስ ውቤ ሃይላቸውን በማቀናጀት በራስ ዓሊ ትንሹ ላይ ዘመቻ አደረጉ። ራስ ዓሊ ለጦርነቱ መሰናዶ ስላላደረገ ስለሆነም የመዋጋት ፍላጎትም ስላልነበረው እጅግ የተመሳቀለውና በታሪክ የደብረ ታቦር ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው ውጊያ እ.ኤ.አ ታህሳስ 7፣ 1842 ተካሄደ። በመጀመሪያ ላይ የአሊ ሰራዊት ስለተሸነፈ አሊ ሽሽት አደረገ። በዚያኑ ቀን ማምሻው ላይ እነ ራስ ውቤ ድላቸውን በመጠጥ እያከበሩ በሚሳከሩበት መካከል የአሊ ዘመድ የነበረው ብሩ አሊጋዝ እጁን ለመሰጠት እጦር ካምፓቸው ገባ። ሆኖም ግን መሳከራቸውንና በቀላሉ ሊሸነፉ እንዲችሉ ስላተረዳ እጅ ከመስጠት ይልቅ ጥቂት ወታደሮችን በማነሳሳት ያለምንም ችግር ራስ ውቤን ማረከ። ብሩ ጎሹ የሁኔታውን አለማማር በመገንዘብ ወደ ጎጃም ሽሽት አደረገ። እኒህ ሁለት ሰራዊት በንዲህ ሁኔታ ቢሸነፉም ራስ አሊ ግን ለብዙ ቀናት ከሸሸበት ዜናው ስላልደረሰው ወደ ደብረ ታቦር ሊመለስ አልቻለም። ቆይቶ ግን መመለሱ አልቀረም። በአቡነ ሰላማ ተማጽኖ ራስ ውቤና ልጃቸው ከእስር ተለቀቁ። [9] [10]

በ1848ና 49 ቆንጽል ፕላውዴን ከራስ አሊ ጋር የጋራ ስምምነት ውሎችን በደብረታቦር ከተማ ተፈራረመ።

የወደፊቱ አጼ ቴወድሮስ፣ የዛን ዘመኑ ደጃዝማች ካሳጣቁሣ ጦርነት ድል ጥላ ስር እ.ኤ.አ ሚያዝያ 1853 ወደ ደብረ ታቦር ዘመቻ ጀመረ። በመካከሉ ራስ አሊ ወደ አይሻል ሜዳወች በመንቀሳቀስ ደብረታቦርን ለቀቀ። ካሳ ግን ደብረታቦርን በእሳት ካጋየ በኋላ አሊን እስከ ቆራጣ ድረስ ተከተለው። [11] በ1854፣ አዲሱ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ቴወድሮስ ደብረታቦር ላይ መቀመጫቸውን ሲያደርጉ ራስ አሊ እንደገና ደብረ ታቦርን ለመቆጣጠር ዘመቻ አድርጎ ተሸነፈ። [12] ከዚህ በኋላ ንጉሱ በ1857 ወደ ጎጃም ሊያደርጉት ላቀዱት ዘመቻ ሃይላቸውን ደብረታቦር ላይ እንዳጠናክሩና መሰናዶ እንዳደረጉ ደብረ ታቦር መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እዳሳነፁ ሮቢንሰን ያትታል [13]

ደብረ ታቦር፣ 1850ወቹ እ.ኤ.አ
ደብረ ታቦር በ1860ወቹ

እምነት ማሪያም ክብረቱ የተባለ ሰው ሲጽፍ << ቋረኛ ካሳ በአሁኑ ጊዜ (ጥቅምት 7፣ 1860) ደብረታቦር ላይ ደጃች ውቤን ከእስር ለቆ የውቤን ልጅ አግብቶ ደብረታቦር ይኖራል" ብሏል[14] አጼ ቴወድሮስ በዚህ ዘመን መቀመጫቸው ደብረ ታቦር ሆኖ ከከተማው ትንሽ ራቅ ብሎ በሚገኘው የድሮው የእጅ ጠቢባን መናኽሪያ ( ጋፋት )የመድፍና የብረታብረት ማሰሪያ በአውሮጳ ሚሶኖችና በአካባቢው ቀጥቃጮች ሰራተኛነት አስከፈቱ። ሌሎች የአውሮጳ እስረኞች ከመቅደላ ወደ ቆራጣ ከተዛወሩ በኋላ ዘጌ ላይ ፍርድ ተበይኖባቸው ደብረ ታቦር ላይ እ.ኤ.አ ሰኔ 1866 ላይ እስር ቤት ገቡ። እ.ኤ.አ መስከረም 21፣ 1867 ላይ ታዋቂው ሴቫስቶፕል መድፍ ጋፋት ላይ ተሰርቶ ተመረቀ። በዚህ ቀን አጼ ቴወድሮስ ደብረታቦር ላይ እንደነበሩ አስጋኸኝ የተባለ የአይን እማኝ መዝግቧል [15] ከዘመቻ መልስና በየክረምቱ አጼ ቴወድሮስ መኖሪያቸውን በደብረ ታቦር ያደርጉ ነበር። ጥቅምት 3፣ 1867 ላይ የልጅቱ ማሪያምንና የእናቲቱ ማርያም ቤ/ክርስቲያን ታቦቶችን አንድ ላይ በማድረግ በመጠበቂያ ንጉሱ እንዳስቀመጡ እምነተማርያም ክብረቴ የተባለ ጸሃፊ መዝግቧል። [16]

ንጉሱ ጥቅምት11፣ 1867 ላይ ፣ የእንግሊዞቹ ሰራዊት ምጽዋ ከማረፋቸው 10 ቀን ቀደም ብሎ ከደብረ ታቦር መቅደላ ጉዟቸውን ጀመሩ። የዚህ መንገድ ርቀት ከምጽዋ መቅደላ ካለው ርቀት 3 እጥፍ ቢሆንም ከእንግሊዞቹ ቀድመው ለመድፋቸውና ሰራዊታቸው በአስቸጋሪ ተራሮችና ገደሎች ጥርጊያ ሰፊ መንገድ እያሰሩ መቅደላ ለመድረስ ቻሉ።[17] ከጉዞው በፊት ግን የደብረ ታቦርን ህዝብ ከከተማው አስለቅቀው አብዛኛውን ክፍል (ከታቦር መድሃኔ አለም ቤ/ክርስቲያን ውጭ) በእሳት አጋይተውት ነበር። ታቦር መድሃኔ አለም በራሳቸው በአጼ ቴወድሮስ እጅ በቤተ መንግስታቸው ምትክ የተሰራ ነው። በዚሁ ቤ/ክርስቲያን እጅግ ትልቅ ደወል አለ። ከክብደቱ የተነሳ ሊሰቀል ስላልቻለ መሬት ላይ ወድቆ ይገኛል። ይሄ ደወል ከደጃዝማች ውቤ ቤ/ክርስቲያን በአጼ ቴወድሮስ ተወስዶ ለመድሃኔ አለም ቤ/ክርስቲያን የተበረከተ ነው። ደወሉ በ1844 የሮማው ፓፓ ግሪጎሪ 16ኛ ለደጅ አዝማች ውቤ በስጦታነት የተላከ ነበር። በጣሊያን ወረራ ደወሉን ለመስቀል ግንብ ቢሰራም ግንቡ በመብረቅ ተመቶ በመፍረሱ አሁንም ደወሉ መሬት ላይ ይገኛል። [18]

መስከረመ 21 1867 ጋፋት ደበረታቦር የተመረቀው ሴባስቶፖል መድፍመቅደላ ላይ
አጼ ዮሐንስ ቤተመንግስት በሰማራ፣ ደብረታቦር፣ 1884

ዋግሹም ጎበዜ የጎጃም አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት የደብረታቦሩ ራስ አዳል ሃላቸውን በማጠናከር በመጨረሻ ል ላይ በ1870 ንጉስ ተክለ ሃይማኖት ተብለው ስልጣን ላይ ወጡ[19]። ከዚህ ዘመን በኋላ አጼ ዮሐንስ መኖሪያቸውን በደብረ ታቦር አደረጉ። አጼ ምኒልክም በ1877 ከሰራዊታቸው ጋር በደብረ ታቦር ለአንድ ወር እንደቆዩ ታሪክ ያትታል።[20] ስለኢትዮጵያ የባህር ወደብ ጥያቄ የእንግሊዙ በካርቱም ቆንጽላ ዊንስታንሊ እና አጼ ዮሐንስ ደበረ ታቦር ላይ በጥር 1879 ውይይት እንዳደረጉ ታሪክ ይመዘግባል።[21] ግንቦት 23፣ 1879 ላይ ጣሊያኖቹ ጊኮሞና ናሬቲ ለአጼ ዮሓንስ የጠመንጃና ድንኳኖች እንዲሁም አንዳንድ የጣሊያን ኢንዱስትሪ ውጤቶችን ስጦታ ይዘው ደብረ ታቦር ላይ እንዳቀረቡና አጼ ዮሓንስም ሁለት የአንበሳ ግልገል ስጦታወች በምትኩ እንደላኩ ታሪክ ያትታል። አጼ ዮሓንስ ናሬቲ የህሩይ ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን እንዲያንጽ ጠይቀውት ነበር። ይህ ቤ/ክርስቲያን በዚሁ በአጼ ዮሃንስ ዘመን ተሰራ። ከተላኩት ጣሊያኖች ጋር የመጡ ስዊድኖች ሃይማኖት ለመስበክ ከንጉሱ ፍቃድ ቢጠይቁም ሚስዮኖቹ ለእስላሞችና ለአይሁዶች ክርስትናን ከመሰበክ ይልቅ ለክርስቲያኖቹ ስለሚሰብኩ ወዲያውኑ ወደ አድዋ እንዲባረሩ አደረጉ። [22] በዚሁ ዘመን (1879) ወልደ ሚካኤል የተባለው የመረብ ምላሽ አስተዳዳሪ በራስ አሉላ ተይዞ ወደ ደብረታቦር ለፍርድ ቀርቧል። በኋላም አምባ ስላማ ላይ ከነልጆቹ እንዲታሰር አጼ ዮሓንስ አዘዙ [23]

የካቲት 1881 ላይ ራስ አዳል የጎጃም ንጉስ ሆነው ተክሊል በደብረ ታቦር ጫኑ [24] በ1883 ራስ ገብረ ኪዳንራስ አሉላ ከአጼ ዮሐንስ ጋር በመሆን ምዕራባዊ ወሎ ላይ ዘመቻ አድረጉ። በሗላም ወደ ደብረ ተቦር መጥተው ዕረፍት አደርጉ[25] በዚህ ዘመን ደብረ ታቦር ሳማራ በመባል ትታወቅ ነበር። በ80ወቹ ከመሃዲስቶች ጋር ከፍተኛ ጦርነት የተነሳበት ዘመን ነበር። መሃዲስቶች ንጉስ ተክለ ሃይማኖትን በሳር ውሃ ላይ አሸንፈው ለመቆጣጠር ሲሞክሩ አጼ ዮሐንስ ንጉስ ምንሊክ ወደ ሰሜን እንዲዘምቱ ላኩ። በዚህ ምክንያት አጼ ምንሊክ ደብረታቦር ላይ መጋቢት 10፣ 1888 አርፈው ወደ ጎንደር ዘመቻ አደረጉ። ነገር ግን መሃዲስቶቹ ወደ መተማ ስለሸሹ ጦርነቱ ሳይካሄድ ቀረ።[26][27] ሐምሌ7፣ 1888 አጼ ዮሐንስ ንጉስ ተክለሃይማኖትን ለመውጋት ወደ ደብረታቦርና ጎጃም እንደዘመቱ ታሪክ ይመዘግባል።[28] አጼ ዮሐንስ የአገሪቱን ዋና ከተማ መቀሌ ካደረጉ በሗላም ቢሆን የደብረታቦር ከተማ በጎንደርና በላሊበላ መካከል ለሚካሄደው ንግድ ዋና ማዕከላዊ ቦታ ነበረች። አላማኒ የተባለ ታሪክ ተመራማሪ እንደገመዘገበ በ1880 ወቹ መጨረሻ አካባቢ 70፣000 በሬወች፣ 8፣000 ላሞች፣ 14፣000 ፍየሎችና 8፣000 በጎች በከተማይቱ በየአመቱ ለገበያ ይቀርቡ ነበር [29]

ሼክ ዘካሪያስ የተሰኘ ሰው በደብረ ታቦርና ሰቆጣ ለሚገኙ እስላሞች ክርስትናን መስበክ ጀመረ። ስለዚህም ከምንሊክ 100 ጠመንጃወች እና 4000 ማሪያ ቴሬሳ ተሰጠው [30]

የእናቲቱ ማሪያም እንደገና መታነጽ
[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ራስ ጉግሳ ወሌ (ከ1918 - 1930 የበጌምድር አስተዳዳሪ) በደብረታቦርና አካባቢው ብዙ ቤ/ክርስቲያኖችን ያሠሩት በዚሁ ጊዜ ነበር። አስተዳዳሪው ከመጠን በላይ አዳዲስ ቤ/ክርስቲያኖችን የመገንባት አባዜ እንደነበረባቸው የእንግሊዙ ቆንጽላ ቺዝማን መዝግቧል። የእናቲቱ ማርያም ቤ/ክርስቲያን ከንደገና የታነጸው በዚሁ ዘመን በራስ ጉግሳ ወሌ ነበር [31] የ16 አመቱ ጀምበሬ ሃይሉ እና አጎቱ አለቃ አለሙ የእናቲቱን ማሪያምን ቤ/ክርስቲያን ምስሎች እንዲስሉ ተጠይቀው ራስ ጉግሳ እስካመጹበት 1930 ድረስ ያለምንም ማቋረጥ እንደሳሉ ታሪክ የመዘግባል።

የደብረ ታቦር ሆስፒታል መመስረት
[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

1928 ላይ በራስ ካሳ አማላጅነት የ7 ቀን አድቬንቲስት ሚሲዮኖች በከተማይቱ ላይ ሆስፒታል እንዲሰሩ ተፈቀደ። ይህም ከኢትዮጵያ መንግስት ሰፊ መሬትና 30፣00 ማሪያ ቴሬሳ ያስወጣ ስራ ነበር። ራስ ካሳም ለድሃ ታካሚወች የሚውል ህንጻ በሆስፒታሉ ግቢ እንዲሰራ ከራሳቸው 10፣000 ማሪያ ቴሬሳ በእርዳታ ሰጡ። የስዊድኑ ጉድሙንድሰንአዲስ አበባ ደብረታቦር አስፈላጊ እቃወችን ጭኖ በገበያ ቀን ደረሰ። የከተማይቱ አስተዳዳሪ ደጃዝማች ወንድወሰን ካሳ ለሚስዮኑ ጉድሙንድሰን በአውሮጳውያን የምግብ አይነት የተዘጋጀ እራት በዚያው ቀን ጋበዘው። ጉድመንድሰን የሆስፒታሉን ስራ ለ2 ቀን በሃላፊነት ተቆጣጥሮ 7 ህንጻወችን አቆመ። ለዚህ ስራ 88 አህዮች፣ 45 በቅሎወች፣ 4 ግመሎች እቃወችን ለማመላለስ ሲጠቅሙ ከአካባቢው ኖራን ( lime) ለማምጣት 8 ቀን ይወስድ ነበር። አዲስ አበባ በቴሌግራም ለመገናኘት 40 ቀናት ይወስድ ነበር፣ መልዕክተኛ ደግሞ 4 ሳምንት። ኤሪክ ፓልም የተሰኘ ሚስዮን ከህንጻው መጠናቀቅ በኋላ የሚስዮኑ አላፊ ሆኖ አገለገለ። ለዚህ ሆስፒታል መሰራት አነሳሽንተን ወስደው አስተዋጾ ያደረጉ ጉድሙንድሰን፣ ዶክተር አንደርሰን፣ ቄስ ስትራህል እና ገንዘብ ሃላፊ ፔደርሰን ነበሩ [32]

ሙሶሊኒ ጥቁር ሽሚዝ ሰራዊቶች ጉዞ ወደ ደብረታቦር .. ከፊት ለፊት ታዋቂው የአሞራ ገደል ቋጥኝ

ራስ ጉግሳ ወሌ ከደብረ ታቦር አጠገብ በአንቺም ጦርነት መጋቢት 31፣ 1930 ላይ ወደቁ። [33] በወቅቱ ብዙ ጅቦች በደብረታቦር ዙርያ ይኖሩ እንደነበር ተጓዦች መዝግበዋል። [34]

የባንክ መከፈት
[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ኢትዮጵያ ባንክ በ1931 ሲፈጠር ደብረታቦር ውስጥ ቅርንጫፍ ቢሮ በሁለት ተቀጣሪወች በዚያኑ አመት ተከፈተ። በዚህ ጊዜ የደብረ ታቦር ፖስታ ቤት ሃላፊ አቃቢ ክፍሌ ይባል ነበር።

ከራስ ጉግሳ ሞት በኋላ የበጌምድር አስተዳዳሪ የነበሩት ራስ ካሳ ልጃቸውን ደጃዝማች ወንድ በወሰን የደብረታቦር አስተዳዳሪ አድርገው ሾሙ። እንግሊዛዊ ቺዝማንን በዚህ ወቅት ደብረታቦር የተቀበላቸው ግራዝማች አበበ የሚባል የወንድ ወሰን ሹም ነበር። [35]

የፋሺስት ጣልያን ጦር መግባት
[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሚያዚያ 241936 እ.ኤ.አ. ላይ የሳርቼ ጦር ሁለት ባታሊዮን (የሙሶሊኒ ጥቁር ሸሚዝ የሚባሉትና 111ኛ ኔቲቭ) ድንገተኛ ጥቃት በከተማው ላይ አደረሱ። ራስ ካሳ በዚህ ጥቃት ጊዜ ከከተማው ርቀው የነበሩ ሲሆን ደጃች አያሌው ብሩ ግን ጣሊያኖቹ ከተማይቱን ሲቃረብ እርሳቸው ከታማይቱን ለውቀው ሄዱ።[36] ሚያዚያ 28 ላይ ከባህር ዳር ተነጥሎ የመጣው ይህ የጣሊያን ሰራዊት ደብረታቦርን ያዘ። ደጅ አዝማች አያሌው እጃቸውን እንዲሰጡ በዚሁ ወቅት ተደርጉ። ማጆር ዩጎሊኒ በተባለ የሚመራ 2 የጣሊያን ባታሊዮን ጦር በከተማይቱ በቋሚነት ሰፈረ። [37] በሚቀጥለው አመት የቴለግራፍና የጣሊያን ፖስታ ቤት ፋሺስቶቹ ሲያቋቁሙ ወዲያውም ከፍተኛ ጥቃት በደብረታቦርና በባህር ዳር በአንድ ጊዜ ከአካባቢው ህዝብ ደረሰባቸው። [38]

የመጀመሪያው መስጊድ መሰራት
[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በ1938 ፋሺስቶች ከደሴ ጎንደር የሚመላለስ መንገድ አሰሩ፣ የደብረታቦር የመጀመሪያ መስጊድም በዚህ ጊዜ ታነጸ። የባህር ዛፍ ተክልም በበለጠ እንዲስፋፋ ተደረገ። [39]

በጎንደርና ደብረታቦር አካባቢ የተሰማሩ የኢትዮጵያ አርበኞች (ስማቸው? )፡ አሜሪካዊው ፓይለት <<ቢል ዊልስ>> ከአውሮፕላኑ ሐምሌ፣ 1941 መከስከስ በኋላ ከጠላት የተከላከሉት

1941 ላይ ደብረ ታቦር በኮሎኔል ኢኛትሲዮ አንጀሊኒ በሚመራ 6000 የፋሺስት ወታደርና በ7 ማይል ዙሪያ በታጠረ ቅጥር ትጠበቅ ነበር። መጋቢት ወር ላይ ፊታውራሪ ብሩ፣ ሲሞኖድ የተባለ እንግሊዛዊና የበጌምድር ሰራዊት፣ በኋላም 180 ወታደሮችን ይዞ ከባህርዳር ተገንጥሎ ከመጣው ቢል ማክሊን ጋር ወደ ደብረ ታቦር ዘመቻ አደረጉ። 200 ወታደሮችን ይዞ ይታገል የነበረው የአካባቢው አርበኛ ዳኘው ተሰማ ከነሱ ጋር በመቀላቀል ሚያዚያ 1 ላይ ባደረሱት ጥቃት 100 ባንዳወች ተገደሉ። የዚህ ውጊያ ዋና አላማ በጄኔራል ዊንጌት እንደታቀደ፣ ከደሴ ሊሸሽ የሚችለውን የጣሊያን 10፣000 ሰራዊት የሰሜን ምዕራብ ጉዞውን ለመቁረጥ ነበር ። [40][41] [42]

ግንቦት 5፣ 1941 አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ አዲስ አበባ ይመለሱ እንጂ በዚህ ወቅት የኮሎኔል አንጀሊኒና የፊትዋራሪ ብሩ/ሲሞኖድ ሰራዊት ደብረ ታቦር ላይ እንደ ተፋጠጡ ነበር። ሆኖም ግን ወረራው መፈናፈኛ ስላልነበረው ኮሎኔል አንጀሊኒ ለፊታውራሪ ብሩ፣ ሲሞኖድ እና ማክሊን ሃይሎች ሐምሌ7፣ 1941 ላይ ከ4000 ወታደሮች ጋር እጃቸውን ሰጡ። [43][44][45]

1945 ላይ አርቲስት ሙሉጌታ እንግዳ ድንገት (1945-1986) በደብረ ታቦር ተወለደ። [46] በዚህ ወቅት፣ 1949፣ የደብረ ታቦር ሆስፒታል አንድ ዶከትረ እና 50 አልጋወች ነበሩት

ደብረ ታቦር ሆስፒታል፣ 1950ዓ.ም.

ተመራማሪው ሲሞን ስለደብረ ታቦር ጥናት በዚህ ዘመን አደረገ። በጥናቱ መሰረት በየቀኑ የሚክሄደው ገበያ በሳምንት አንድ ጊዜ ከሚካሄደው ግማሽ አይነት እቃን እንደሚያቀረብ፣ የየቀኑ ገበያ ምግብና ማብሰያ እንጨትን በብዛት እንደሚሸጥ፣ በጣሊያን ጦርነት በፈረሱት ድልድዮች ምክንያት ወደ ደብረታቦር እቃ በጭነት መኪና እንደማይመጣ፣ አብዛኛው ደብረታቦር የሚሸጠው እቃ ከከተማው 3 ቀን ጉዞ ርቀት በታች ካሉት መንደሮች እንደሚመነጭ ጨው፣ ቡናና ጥጥ ግን ራቅ ካሉ ቦታወች እንደሚመጡ፣ ደብረታቦር የሚበቅለው ድንች ከተቀረው ያገሪቱ ክፍል ከሚበቅለው በይዘቱ ትልቅ እንደሆነ፣ እዚህ አካባቢ የሚገኙ አህዮችም ከተቀረው ተለቅ እንደሚሉና ጠንካራ እንደሆኑ፣ ትንባሆ ለኢንደስትሪ ባይበቅልም ነገር ግን አንድ አንድ ገበሬወች ለእንስሳት ህክምናና በጌሾ ምትክ ለጠላ መጥመቂያ እንደሚጠቀሙበት፣ ጅቦችም በብዛትና በጥንካሬ እንደሚገኙ መዝግቧል። [47]

በ1858 ደበረ ታቦር ከሌሎች 27 የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር በመሆን አንደኛ ደረጃ ከተማ ተባለች። በ1958 የትክትክ ክትባት በከተማዋ ሲደረግ በ1959 የአውራጃው አስተዳዳሪ ደጃዝማች ሞላ መሸሻ ነበሩ።

1960 ላይ 15 የአጼ ቴወድሮስ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪወችና 2 የአድቬንቲስት ሚስዮኖች የ8ኛ ክፍልን ማትሪክ ፈተና አልፉ። በ1966 የከተማዋን አቀማመጥ ዋና አቅድ ተቋራጭ ሲይዘው በ67 በተደረገው ህዝብ ቆጠራ 6፣942 ሰወች እና 3 የስልክ ቁጥሮች ነበሩ። 1968 ላይ አጼ ቴወድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 82 ወንዶች፣ 40 ሴት ተማሪወች ክፍል 7 ና 8ን የሚወስዱ ነበሩት። 4 አስተማሪወች የነበሩት ሲሆን 2ቱ የውጭ አገርዜጋ ነበሩ። አድቬንቲስት ሚስዮንና ሚሲዮን ወደ አይሁድ ህዝቦች ተጨማሪ 52 ወንድና 32 ሴት ተማሪወችን ያስተናግዱ ነበር። [48]

አብዮቱ ፍንዳታ በኋላ በ1975 የአካባቢው ርስተኞችና ተከታዮቻቸው ደብረ ታቦርን መስከረም 1975 ላይ ተቆጣጠሩ። የአጠቃላይ በጌምድር አስተዳዳሪ በዚህ አመጽ ሲገደል መንገድ ሰሪ ቻይኖችና የሆስፒታል አስተዳዳሪ አድቬንቲስት ሚስዮኖች ተባረሩ። የዚህ አመጽ ቀስቃሽ መልዕክት ደርግ የአረቦች ሴራ ነው የሚል ነበር። [49] የክፍለ ሃገሩ አስተዳዳሪ በዛብህ ገብሬ( 43 ) ምንም እንኳ ደበረ ታቦር የተወለደ ሰው ቢሆም የደርግ ተወካይ ነው ተብሎ ስለታመነ በአመጹ ተገደለና በዚያው በመስከረም ተቀበረ። [50]አፋር በርሃወች የጥንት አጽሞችን ከሚፈልጉት ሰወች አስተዋጾ ያበረከተው ስለሺ ተበጀ በዚህ ወቅት በደብረ ታቦር የዘመቻ ተማሪ ነበር። [51]

መጋቢት 1989 መጨረሻ አካባቢ በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ኢሰፓ እና ኢህአዴግ ወታደሮች በተደረገው ጦርነት ደብረታቦር በኢህአዴግ ቁጥጥር ወደቀች። ከወር በኋላ የመንግስቱ ወታደሮች እንደገና ተቆጣጠሯት። «ህወሃት [በዚህ ወቅት] 8000 የመንግስት ወታደሮችን እንደገደለ ቢናገርም ገለልተኛ የሆኑ አይን እማኞች ግን አላጣሩትም» [52]

ጥር 20 1990 ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዜና ተቋም ( ENA news agency) ደብረ ታቦርን መንግስቱ እንደተቆጣጠረ አስታወቀ። የህወሃት ራዲዮ ጣቢያ ጥር 22-24፣ 1990 ደብረ ታቦር ላይ ከባድ ድል እንዳስመዘገበ አስታወቀ። ይሄው ራዲዮ ጣቢያ ኢሃዴግ 3፣914 የመንግስት ወታደሮችን እንደገደለና 270 ደግሞ እንደማረከ አስታወቀ። ጥር25፣ 1990 ላይ ከመንገድ ቦይ ስር ተጠልለው የነበሩ 15 ሰወች በአውሮፕላን ቦምብ ተገደሉ።

ከትንሽ ቀናት በኋላ የመንግስት ወታደሮች እንደገና ከተማይቱን ተቆጣጠሩ። ህወሃት ከ3 ቀን ጦርነት በኋላ ከተማይቱን መጋቢት መጨረሻ ላይ እንደተቆጣጠረ አስታወቀ።[53] መጋቢት 13፣ 1991 በደብረታቦር ላይ በተካሄደው የአውሮፕላን ድብደባ 2 ሰወች በቦምብ ሲገደሉ 10 ደግሞ ቆሰሉ። [54] በዚህ ወቅት እንግሊዛዊው ሃሞንድ ደብረታቦር በመሄድ ስለከተማው ሆስፒታል እና ሀወሃት አቋቁሞት ስለነበረው የሜዳ ሆስፒታል ቃለ ምልልስና ጥናት አካሂዷል። [55]

1994 ላይ የከተማው ህዝብ ብዛት 22፣500 መሆኑ ተዘገበ። 1996 ላይ 2 የእንግሊዝ ቱሪስቶች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ታፍነው ተወስደው ከ 2 ቀን በኋላ ተለቀቁ። በዚህ ወቅት የከተማይቱ አየር ማረፊያ ያልተጠረገ 1250 ሜትር መንደርደሪያ ነበረው።

መስከረም 2000 ላይ አንድ የኢለመንታሪ ትምህርት ቤት ታድሶ በካናዳ አምባሳደር ተመርቀ። ትምህርት ቤቱን ለማሳደስ ከወጣው 400፣000 ብር 230፣000ውን ካናዳ እንደሸፈነ አዲስ ትሪቢዩን መዝግቧል። [56] በ2001 የህዝቡ ቁጥር 27,600 ነበር። ጥቅምት 18፣ 2001 ላይ የእንግሊዝ ኢምባሲ 251፣444 ብር አውጥቶ ያሰራው የዳግማዊ አጼ ቴወድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቤተ መጻህፍት ተከፈተ።.

ሕዝብ ስብጥር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ተጨማሪ መጻጽፍ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
  1. ^ Jäger 1965 p 75
  2. ^ Éthiopie By Luigi Cantamessa, Marc Aubert ገጽ 181
  3. ^ ባህሩ ዘውዴ 1991 ገጽ 19
  4. ^ [Rubenson 1976 p 35]
  5. ^ Äthiopien 1999 p 318 + Mathew 1947 p 154
  6. ^ [Mansfield Parkyns vol II p 117]
  7. ^ S Rubenson, King of kings .., 1966 p 22
  8. ^ 3rd Int. Conf. of Ethiopian Studies 1969 p 184, 186
  9. ^ S Rubenson, The survival .., 1976 p 93-94
  10. ^ Abir 1968 p 112
  11. ^ Abir p 139
  12. ^ Äthiopien 1999 p 318
  13. ^ Rubenson 1966 p 75
  14. ^ Acta aethiopica II p 129
  15. ^ ditto II p 331
  16. ^ Acta aethiopica II p 335
  17. ^ Rubenson 1976 p 261
  18. ^ Rubenson 1966 + Äthiopien 1999 p 319-320
  19. ^ Greenfield 1965 p 89
  20. ^ G Bianchi 1896 p 136 foot note
  21. ^ Ehrlich 1996 p 24
  22. ^ 12th Int. Conf. of Ethiopian Studies 1994 p 914-196
  23. ^ [Ehrlich p 25]
  24. ^ A Ribera, Vita di Antonio Cecchi, Firenze 1940 p 133-134
  25. ^ Ehrlich p 36
  26. ^ [Ehrlich 1996 p 129]
  27. ^ [Marcus, Menelik II, (1975)1995 p 101]
  28. ^ Ehrlich p 130]
  29. ^ Alamanni
  30. ^ 13th Int. Conf. of Ethiopian Studies I 1997 p 132
  31. ^ Cheesman 1936
  32. ^ G Gudmundsen, Fjorton år .., Sthlm 1936 p 161-169
  33. ^ Mockler 1984 p 11
  34. ^ T A Lambie, Boot and saddle .., USA 1943 p 151
  35. ^ "There is no group that can be identified with the descendants of the Portuguese -- I have noticed that the faces of some women in Debra Tabor bear a resemblance to Portuguese features." Cheesman 1936
  36. ^ Mockler 1984 p 129
  37. ^ Nyström as above p 168-171, 178
  38. ^ Mockler 1984 p 183
  39. ^ G Puglisi, Chi è? .., Asmara 1952
  40. ^ Mockler 1984 p 355
  41. ^ Mockler 1984 p 375
  42. ^ Shirreff 1995 p 165-166
  43. ^ Mockler 1984 p 379, 382
  44. ^ [Shirreff 1995 p 231-232]
  45. ^ [R N Thompson 1987 p 190]
  46. ^ [Eth. Artists p 164-165]
  47. ^ [F J Simoons, Northwest Ethiopia .., Madison/USA 1960, mostly p 197-200]
  48. ^ [Dervla Murphy 1969 p 194-199]
  49. ^ [M & D Ottaway 1978 p 88]
  50. ^ [Eth.Herald 1975-09-25]
  51. ^ [J Kalb 2001 p 194, 212, 231-234, 277, 314-315]
  52. ^ [Swedish News]
  53. ^ [News]
  54. ^ [Hammond 1999 p 449]
  55. ^ [Hammond 1999 p 369, 370][Hammond p 372, 373]
  56. ^ [AddisTribune news]