ባሕር-ዳር

ከውክፔዲያ
ባሕር ዳር
ከተማ
የቦታ ስፋት
   • አጠቃላይ 28 ኪ.ሜ. ካሬ
ከፍታ 1,800 ሜትር
የሕዝብ ብዛት
   • አጠቃላይ 348,429

ባሕር ዳር በድሮ ስሙ ባሕር ዳር ጊዮርጊስ በሰሜን-ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኝ ከተማ ስትኾን የአማራ ክልል ዋና ከተማ ናት። ከተማዋ በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር ውስጥ ከጣና ሐይቅ ደቡባዊ ጫፍ ላይ ተቀምጣ ስትገኝ ባሕር ዳር እንደ መቀሌደሴ የወረዳ ደረጃ ያላት ስፔሻል(ልዩ) ዞን ናት። በማእከላዊ ስታትስቲክ ትመና የ167,261 ሕዝብ ከነሱም መኻከል የ86,355 ወንዶችና የ80,906 ሴቶች መኖሪያ ከተማ ናት። 1700 ሜትር ከባሕር ወለል በላይ ትገኛለች።

መገኛ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ባሕር ዳር ከአዲስ አበባ 565 ኪ.ሜ ወደ ሰሜን-ሰሜን ምዕራብ ትገኛለች። ባህር ዳር ከጢስ አባይ በ30 ኪሎሜትር ስለምትርቅ ለጎብኚዎች አመቺ ቦታ ላይ ናት። ባሕር ዳር የአንድ የአስፋልት ንጣፍ ያለው ኤርፖርት የሰፊ ገበያና የተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች እና ታሪካዊ እና ጥንታዊ ግዳማት መግኛ ቦታ ናት።

ባሕር ዳር ከተማ የምትገኘዉ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል፣ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ከአዲስ አበባ በ 565 ኪሜ ርቀት ላይ ነው፡፡ አስትሮኖሚያዊ መገኛ ቦታዋ በ 11º 38’ በሰሜን ላቲቲውድ እና በ37º15’ ምሥራቅ ሎንግቲውድ ነው፡፡

አመሠራረት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አፈ ታሪክ እንደሚነገረው የባሕር-ዳር ስያሜን ያወጡት አፄ ሠርጸ ድንግል ሲሆኑ እሳቸውም ይሕን ታቦት የት እናስቀምጥ ተብለው በተጠየቁ ጊዜ "ከባሕሩ-ዳር" አድርጉ የተባሉ ሰወች ለመንደሩ ባሕር-ዳር ብለው ስያሜ አወጡለት ይባላል።

ባሕር-ዳር ከተማ የተቆረቆረችው በ1915 ዓ.ም ነው ፡፡ ባሕር-ዳር በክልሉ ከሚገኙ የሪፎርም ከተሞች አንድዋ ስትሆን፤ የከተማ አስተዳደር፣ 3 ሜትሮፖሊታን ክ/ከተማዎች፣ የከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት፣ 9 የከተማ ቀበሌዎችና 4 የገጠር ቀበሌዎች አሏት፡፡ ከተማዋ በ1998 ዓ.ም የተቀናጀ ልማት ፕላን አላት፡፡

የተቆረቆረችበትን ዓመት፣ የቆረቆሩትን ቀደምት ሠዎች፣ የሠፈሮችን ስሞች፣ ለባሕር-ዳር የተገጠሙትና የተዘፈኑ ታሪካዊ ግጥሞችና ስነ ቃሎች፣ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጎጆ ቤት ወደ አሁኑ ይዞታው አመጣጥ (ባሕር-ዳርን ስናስብ ጊዮርጊስን ሚካኤልን እና ገበያውን ከገበያው አካባቢ የነበረውን ፍርድ ቤት ነጣጥሎ ማየት አይቻልም የሚል አስተያየት ስላለ ነው)፣ ባሕር-ዳር እንደባሕር ዳርነቱ ከመቆርቆሩ በፊት በሚካኤል እና በሽመምብጥ ሠፈር አካባቢ ስለነበረው አሰፋፈር፣ ስለማዘጋጃቤቱ፣ ስለ አውቶቡስ ተራው፣ ስለ ድባነቄ ተራራ፣ እና ስለ መሳሉት፣ ስለፖሊቴክኒክ፣ ስለዓባይ ወንዝና ድልድዩ፣ ስለዓባይ ወንዝና ስለጣና ሐይቅ መገናኛ እና ስለሌሎችም ቁልፍ ነገሮችን ማቅረብ የሚችሉ አፈታሪኮች አሉ።