Jump to content

ውክፔዲያ:እኛና የኛ ተራሮች

ከውክፔዲያ
(ከእኛና የኛ ተራሮች የተዛወረ)

እኛና የኛ ተራሮች

[ኮድ አርም]

ተራራ፤ የከፍታ፣ የበላይነት፣ የክብር … ምልክት ነው። ነገሥታት፣ ያገር ሽማግሌዎች፣ ታላላቅ ሠዎች፣… በተራራ ይመሰላሉ። በዚህ መጣጥፍ ውስጥ መሪዎቻችን፣ ምሁራኖቻችን፣ የፖለቲካ መሪዎቻችንና ራሳቸውን አንቱ ያሉ ምናምንቴዎቹንም እንቃኛለን።

የኛዎቹ ምሁራን ኢትዮጵያ ተራራማና ፕላቶአማ ናት ይለናል የሥነ-መሬት ተመራማሪው (ጂኦሎጂስቱ) የስነ ምህዳር አጥኚው (ኢኮሎጂስቱ) ደግሞ የኢትዮጲያ ተራራዎች ሐመልማል (ቬጅቴሽን) የሌለባቸው ምድረበዳና በረሀማ ናቸው ሲል ያትታል። እኔ በተራራ የመሰልኳቸው የኛዎቹ ተራሮች፣ የኛዎቹ ምሁራንስ?

አንዲት ኢትዮጲያዊት፣ ነርስነት ለማጥናት ዩኒቨርስቲ በገባች በሶስተኛ ወሯ የወንድ ጓደኛዋን “የተማረና ያልተማረ አብሮ ሊኖር አይችልም” ብላ ተወችው። ካሉኝ ወዲህ ምሁር የሚለው ፅንሰ-ሐሳብ የተዛባ ይመስለኛል።

ይህንን እሳቤ መልክ መልክ ለማስያዝ ይቻለኝ ዘንድ በምሁርና በባለሙያ መሀከል ያለውን የልዩነት መስመር አድምቄ ማስመር አለብኝ ። ከዚህ በፊት ግን ድሮ ትምህርት ወደ ሀገራችን ሲገባ ዓላማው ምን እንደነበረና ዛሬ ያለውን ትርጉም እንዴት እንደያዘ ላስረዳ።

ዘመናዊ ትምህርትን ወደ ሀገራችን ያስገቡት ዐጤ ሚኒሊክ ሲሆኑ ዘመኑም 1898 አካባቢ ነው። ዐጤ ሚኒሊክ ዘመናዊ ትምህርት ለማስተማር አስተማሪዎች ሲያስመጡ ሕዝቡ በፀጋ አልተቀበለውም ። እንዲያውም ከሀይማኖት መሪዎች ጋር ወግኖ ተቃዋሚ ሆነ።

ሚኒሊክ ግን በዘዴም፣ በማታለልም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት እንዲልኩ ቢያግባቡም፤ በተለይ ሹማምንቱ አሻፈረኝ አሉ። የሹማምንቱን እንቢታ የተመለከቱት ሚኒሊክ፣ በቤት ወከፍ አንድ ሰው በማይልከው ላይ መቀጫ ቢጥሉ፣ ሹማምንቱ የአሽከሮቻቸውን ልጆክ መላክ ጀመሩ። ነገሩ ከመቀጫው ለመዳን እንጂ የአሽከሮቻቸው ልጆች ዘመናዊ ትምህርትን እንዲቀስሙ አልነበረም። ሚኒሊክም ልጁን ወደ ትምህርት ቤት ለሚልከው አሽከር እህል መስፈር፣ ብርድ ልብስ መስጠት ስለጀመሩ ጭሰኛው ሁሉ በልጆቹ ለመጠቀም ከእረኝነትና ከእርሻ ስራ እያስቀረ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ጀመረ።

የመጀመሪያዎቹ የመሠረተ ትምህርት (የማንበብና መፃፍ) ምሩቃን በፅሑፍና በትርጉም ስራ መሰማራታቸውን ያዩ፤ ልጆቻቸው በንጉሡ ፊት እንዲታዩ ሲሉ ወደ ት/ቤት ላኳቸው። እነዛም አራተኝ ክፍል ሲደርሱ ሚኒሊክ ጭቃ ሹምና ምስለኔ እያደረጉ ሲሾሟቸው የተመለከቱ መኳንንት ሁሉ፣ “ልጄ እንዲህ ቦታ ፈራጅ ነው፣ ልጄ በንጉሡ ፊት ነው የሚውለው ለማለት የአሽከሮቻቸውን ልጆች እያስቀሩ ልጆቻቸውን መላክ ጀመሩ።

እያደር ስምንተኛ ክፍል ካላጠናቀቁ ስራ ስለጠፋ፣ ስምንተኛ ክፍል ግራጁዌት ለማድረግ ሁሉም ትጉህ ተማሪ ሆነ። ስምንተኛ ክፍል ተማሪው በዝቶ ስራ ለመቀጠሪያ በቂ ባለምሆኑ 12ኛ ክፍል መጨረስ ግድ ሆነ። እስከ ቅርብጊዜ ድረስ የእከሌ ልጅ 12ኛ ክፍል ጨርሶ ስራ አጥቶ ቁጭ ብሏል እየተባለ ይነገር ጀመር። አሁን ደሞ ኮሌጅ የገቡ ናቸው የሥራ ተስፋ ያላቸው

ያኔ ዐጤ ሚኒሊክ ሕዝቡ ዘመናዊ ትምህርትን እንዲቀበል ያደረጉበት ዘዴ የትምህርት ዋናው ዓላማ ሆኖ ቀረ። በዚህም የተነሳ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀውም የቢሮ ጠረጴዛ መያዙን እንዳረጋገጠ የተማረውን ትምህርት ደህና ሰንብት ያለ ይመስላል። የተማረውም ያልተማረውም አሮጌውን እንዳለ ተቀብለው አስረጅተው ለተተኪው ሲያስተላልፉ እንጂ መጠነኛ ለውጥንኳ አያደርጉበትም።

እንዲህና እንዲህ ሆኖ እነሆ የትምህርት ዋና ዓላማው ራስን መቻል ከሚለው ማለፍ አቃተው። በዚህም ምክንያት ምሁሩም ምሩቁም ከድህረ ምረቃ በኋላ ልዩነት ስለማይታይባቸው፣ ምሩቃን ከምሁራን መደዳ ለመሰለፍ ትከሻ ግፊያ ጀመሩ። ታዲያ ምሁሩ ማነው?

ምሁር ለሚለው ቃል አቻ እንግሊዝኛ ትርጉሙ ኢንተለክቹዋል ነው። አማርኛችን ምሁር የሚለውን ቃል ከፍተኛ የሆነ የማሰብና የመመራመር ችሎታ ያለው ብሎ ይተነትነዋል። ፕሮፌሽናል (ባለሙያ የሚለውን ደግሞ በአንድ ነገር የሠለጠነ፣ ያጠና፣ ስልጠናን የተከታተለ ይለዋል። በዚህ ትርጓሜ መሠረት ምሩቃን ባለሙያ እንጂ ምሁራን አይደሉም። ስለዚህ ምሁር ነኝ ከሚለው ብዙ ነገር እንጠብቃለን። ምን? ኑሮአቸውን ለማሸነፍ ተቀጥረው ከሚሰሩት የበለጠ ነገን ለመቀየር፣ የሌላውን ኑሮ ለማሻሻል፣ የበለጠ የሚማሩ፣ ተምረውም የሚተገብሩ መሆን አለባቸው። ምክንያቱም ነፍሱን ይማረውና ታላቁ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ (አሪስቶትል) “በምናውቀው ነገር ካልሰራን ምንም አናቅም ማለት ነው።” ብሎ ብሒሉን ትቶልን አልፏል።

በዚህ መለኪያ የኛዎቹ ተራሮች (ምሁራን እንዴት ናቸው?) እዚህጋ ምሩቃኑም ምሁር ነን ብለው ነውና የሚያስቡት እንደ ሀሳባቸው ልጠቅልላቸው። ሆኖም ምሩቃኖቻችን ወደ ምሁርነት እንደማይሻገሩ እነሱም ያውቁታል። ምክንያቱም ሚኒሊክ ሕዝቡ ትምህርትን እንዲቀበል የተጠቀሙበትን ዘዴ የትምህርት ዋና ዓላማ አድርገው ወስደውት ተሸውደዋል። ለዚህም ጥሩ አብነት አለን። የአለማያ ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን

የአላማያ ዩኒቨርሲቲ ስሙን ያገኘው የዩኒቨርሲቲው ሕንፃ በተገነባበት ቦታ በዓለማያ ሐይቅ ነው። ዩኒቨርሲቲው ቀድሞ የእርሻ ኮሌጅ የነበረ ሲሆን አሁን ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እስከ 2004 ድረስ 512 ተማሪዎችን በማስተርስ ዲግሪ አስመርቋል። ከነዚህ ተማሪዎች ሲሶዎቹ የአካባቢ ጥበቃና ክብካቤ (ኔቸር ኮንሰርቬሽን) ምሩቃን ናቸው። ይህም ማለት የተፈጥሮ ሀብት እንደ ዉኃ፣ ደን፣ የዱር አራዊት፣ የባሕር እንሰሳት፣ የሰማይ አእዋፋት ጥበቃና ክብካቤ ቀጥታ የሚመለከታቸው ሰዎች ናቸው።

ዳሩ ከስልሳዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ከሰባ ሺህ ነዋሪ በላይ ያለውን የዓለማያ ሕዝብን በመጠጥ ዉኃ አቅርቦት ያገለገለው ሐይቅ ሲጠፋ ምሩቃኑ ቆባቸውን እየደፉ ሐይቁን የጎሪጥ እያዩ ወደ አዲስ አበባ ስራ ፍለጋ ይሄዱ ነበር። ምሩቃኑ ለዓለማያ ሐይቅ መጥፋት ምክንያት አንድ ሽህ ምክንያት ሊነግሩን ይችሉ ይሆናል። ሐይቁን አድነው ቢሆን ኖሮ በአድናቆት እናዳምጣቸው ነበር። የጠፋበትን ምክንያትማ የዓለማያ ገበሬም አይስተውም። ትልቁ ችግር ግን ምሩቃኑ ዋና ዓላማቸው ራሳቸውን መቻል ነውና ከምረቃ በኋላ ስራ መፈለጉ፤ ከዚያም ስራው ላይ ለመቆየት መታገል፣ ከዚያም የተሻለ ደሞዝ የሚያስገኝ ስራ መፈለግ ዋነኛ ተግባራቸው ሆነ።

አሁን የምሁራኑና የምሩቃኑ የልዩነት መስመር ደምቆ የተሰመረ ይመስላል። ማነው ምሑሩ? ምሩቃኑስ እነማን ናቸው? የስም ዝርዝሩን እናንተው ፃፉት።

እኛና ያደግንበት ኅብረተሰብ የተማረ እናከብራለን። ምክንያቱም እኛ ልናደርግ የማንችለውን ማድረግ ስለሚችሉ፣ ነገሮችን ከኛ በተሻለ ሁኔታ መስራት ስለሚችሉ ነው። አሁን፣ አሁን ግን የተማረ የሚባለው ከኛ ከአቡጊዳ ምሩቆቹ ብዙም የተሻለ ሲሰሩ አናይም። እርግጥ ነው ከኛ የተሻለ ያገኙ ይሆናል፣ ከኛ የተሻለ ይኖሩ ይሆናል። ግን ችግር በማስወገድ፣ በአመለካከት ብስለት፣ የሌላውን ኑሮ በመለወጥ ረገድ እኛ ሳንበልጣቸው አንቀርም። አንድ ኢትዮጲያዊ ሕፃን ከጎዳና አንስታችሁ ማሳደጋችሁን እኒህ ምሁራን ተብዬዎች ቢሰሙ ትክክል እንዳልሆናችሁ እንዲያውም ሕፃኑን ለከፋ ሁኔታ እንዳጋለጣችሁት ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ ያሳምኗችኋል። የምታደርጉት ሰብዐዊ ድርጊትን አውግዘው አፋችሁን ያስይዟችኋል። እሺ ታዲያ ምንድነው የተሻለው ስትሏቸው ግን የመፍትኄ ሀሳብ አይሰጧችሁም። ብቻ የምትሰሩትን ጥሩ ስራ ያስተውዋችኋል።

የኛዎቹ ምሩቃን (ምሁራን) አንድ የጋራ ነገራቸው እንደኔ አይነቱን የፊደል ምሩቅ ግራ ማጋባት ነው። አስተውላችሁ ከሆነ ኢትዮጲያዊ ምሁር ጋዜጣ ላይ የሚፅፈው ኢንግሊዝኛ አርቲክል በቀላሉ አይገባም። ቃላቶቹ እጅግ ከባባዶች ሲሆኑ ሰዋስዉ ደግሞ ጠንካራ ነው… እዚህ ሀገር በነጮቹ የሚፃፈውን ማንኛውንም አርቲክል አንብቤ በደንብ እረዳለሁ። የሀበሻ “ምሁር” የፃፈውን ግን ቀድሞም አልጀምረውም። አንድ ቀን አንድ “ምሁር” ሳያስበው ነገሩን እስኪነግረኝ ድረስ በኔ የቋንቋ ችሎታ ማነስ ነበር የሚመስለኝ

ነገሩ እንዲህ ነው፦ ለሕዝብ የሚቀርብ ፅሑፍ ፃፍኩና አንዱን “ምሁር” እስቲ እየው ብዬ ብሰጠው ብዙ ነገር አስተካክሎ ሰጠኝ። አስገራሚው ነገር አብዛኛው ቃላት ከባባድ ነበሩ። ለምን ብዬ ብጠይቀው ለሕዝብ የሚቀርብ ፅሑፍ ተራ ቃላት መሆን የለበትም ብሎኝ አረፈው። ግንኮ ብዙው ሰው የቋንቋ ችግር አለበት ስለው እሱ ያንተ ችግር አይደለም አንተ ፕሮፌሽናል ፅሑፍ ነው ማቅረብ ያለብህ አለኝ።

አንድ እኔ የሰማሁትን ቀልድ ሰምታችሁት ይሆናል። “አንዲት እንግሊዝ ሀገር ለሥራ ጉዳይ ሄዳ የተመለሰችን ኢትዮጲያዊት አንድ ጋዜጠኛ በእንግሊዝ ሀገር ቆይታሽ የገረመሽ ነገር ምንድነው? ብሎ ሲጠይቃት እንግሊዝ ሀገር ገና የስድስት ዓመት ሕፃን ልጅ በእንግሊዝኛ ይናገራል ብላ ግራሞቷን አጋርታናለች። እና ምሁራኖቻችን በቋንቋ ችሎታቸው ሊያስገርሙን ሲፈልጉስ?

እኔን የገረመኝ ግን ነጮቹ ለአንባቢዎቻቸው ግልፅ ለማድረግ ሲፈልጉ፣ የኛዎቹ ደግሞ አንባቢን ግራ ለማጋባት ይተጋሉ። ተወልደው ያደጉት የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው በንግሊዝ አናግሪያቸው እየተባለ፣ እንግሊዝኛ መኩሪያ እንደሆነ ከሚታሰብበት ማኅበረሰብ መሐል ነውና ቂም ልንይዝባቸው አይገባም።

ድሮ ለትምህርት ውጭ ሔደው ከተመለሱት አብዛኞቹ የተቀላጠፈ እንግሊዝኛና ቻቻ፣ ሳምባ፣ ሩምባ፣ ማሪንጌ፣ ቡጊ፣ዉጊ ... ይዘው መግባታቸው ነበር ማንም ሊያይላቸው የሚችለው ነገር። ዘመነኞቹ ደግሞ ኩራትና ክብር ፈላጊነት ነው ጎልቶ የሚታይባቸው።

እርግጥ ነው ኢትዮጲያዊ ምሁር ተሳስቶ የታየበት ሁኔታ ብዙም የለም። የኢትዮጲያዊ ምሁርን ስራ መተቸት አይቻልም። ምክንያቱም አይሳሳቱም። የማይሳሳቱት ስለማይሰሩ ነው። መሳሳት ይፈራሉ። የፈለገ ነገር ይቀራል እንጂ ተሳስተው ክብራቸውን አያስነኩም። አንድ ምሁር መፅሐፍ የፃፈ እንደሆነ ግን በብዕር ስም ይወርዱበታል። መተቸት አይፈሩም። መንቀፍ አይፈሩም። መሳሳት ግን ይፈራሉ። መሳሳት ክብረ-ነክ ነው። ለዚህም ዕውቀታቸውን ይዘው መቃብር ይወርዳሉ። ሌላውን ከማሳወቅ፣ በተማሩት ሌላውን ከመርዳት ኩራታቸው፣ ክብራቸው ይበልጥባቸዋል።

መኩራት ያለበትና ክብር የሚገባውኮ የሰራ ነው። ለዚህ አንድ አስረጅ ልጥቀስ

አክሱም ክዋን የቆመበትን ጊዜ የኋሊት 3000 ዓመት አሻግረን በምናብ የማየት ችሎታችንን መገመት ያስቸግራል። ቢሆንም ዘመናዊ መሳሪያዎች ባልነበሩበት ሁኔታ፣ የምሕንድስና ዕውቀት ከዩኒቨርሲቲ ባልተገኘበት ወቅት፣ እንደዛሬው በጥበብ ተፎካካሪ ኖሮ አንዱ ካንዱ በማይማርበት ሁኔታ 23 ሜትር ቁመት ያለውን የአክሱምን ክዋን (ሐውልት) ከአንድ ቋጥኝ ፈልፍሎ ለማውጣት ሀሳቡን ያመነጨውን ያን ጥቁር ሀበሻ አስቡት። ቋጥኙን የጠረቡበት መሳሪያ፣ መጠኑን የለኩበት መመተሪያ፣ ፀንቶ እንዲቆም የተጠቀሙበት ፊዚክስ፣ የስራ ክፍፍል፣ የሥራ ድልድል፣ የዛ ዘመን ቲም ዎርክ፣ ንድፉ ያረፈበት ነገር (አውቶ ካድ)፣ እርስ በርስ የሚግባቡበት ቋንቋ፣ ትጋቱ (ሞቲቩ) የስራ ንድፉን ያሰፈሩበት የፅሕፈት መሣሪያ፣ በጀት ምደባው፣ የዓላማው ፅናት፣ ወዘተ ወዘተ ወዘተ ወዘተረፈ አስቡት።

በአክሱም እኛ ልንኮራ ይገባናልንዴ? አክሱም በዛ ዘመን ለነበረው ኢትዮጲያዊ ስልጣኔ አሻራ እንጂ እኛ የምንኮራበት የኛ ስልጣኔ አይደለም። ዛሬ በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የምትገኙት ምሁራን ለ22ኛው ዘመን ሀበሻ የምታቆሙለት ሐውልት ምንድነው? በቴክኖሎጂ በመጠቀ ዘመን ተገኝታችሁ፤ መጪው ዘመን እናንተን የሚያስታውስበት ነገር ምን ሰራችሁ? ምንስ ልትሰሩ ነው? ኩራት? ባዶ ክብር? ይህ ጥያቄ የተማርኩ ነኝ ብሎ ለሚኮራውና መከበር ለሚፈልገው ሁሉ ነው። ምን ስለሰራችሁ እናክብራችሁ?

እርግጥ ነው ስማቸውን እስከነ አያታቸው የምናውቃቸው ጥቂት ምሁራን፣ በተሰለፉበት የስራ መስክ ለወገናቸው የሰሩትን ውለታ አንረሳም። ሆኖም በነሱ ስም አብዛኛው ምሁር ተብዬ እንዲወደስ ፍላጎቱ የለኝም። እነዛ ጥቂት ምሁራን ግን ሳይጠይቁኝ በፈቃዴ በክብር እጅ እነሳቸዋለሁ። በተረፈ ዲግሪያቸውን ሲቀበሉ የለበሱት ጥቁር ቀሚስ የሬሳ መገነዣ ለሆነባቸው ነፍስ ይማር ልል እወዳለሁ፤ እንጂ እነሱ ከኔ የተሻለ ደሞዝ ስላገኙና የተሻለ ኑሮ ስለሚኖሩ፣ ያሰፉትን ሆድ ስለሚሞሉ የማጨበጭብበት ምክንያት የለም።

ኢትዮጲያ ተራራማ ሀገር ናት፣ ተራሮችዋ ግን ምንም የሌለባቸው ባዶ ናቸው። ኢትዮጲያ ብዙ የተማሩ ልጆች አሏት፣ ግን ምንም አልሰሩላትም። እኛና የኛ ተራሮች ክፍል አንድ።

ጠመኔ Temenew@yahoo.ca

ከቶሮንቶ ካናዳ