ውክፔዲያ:እኛና የኛ ተራሮች ክፍል ሦስት

ከውክፔዲያ

እኛና የኛ ተራሮች[ኮድ አርም]

(ክፍል ሦሥት)


ተራራ፤ የከፍታ፣ የበላይነት፣ የክብር … ምልክት ነው። ነገሥታት፣ ያገር ሽማግሌዎች፣ ታላላቅ ሠዎች፣… በተራራ ይመሰላሉ። በዚህ መጣጥፍ ውስጥ መሪዎቻችን፣ ምሁራኖቻችን፣ የፖለቲካ መሪዎቻችንና ራሳቸውን አንቱ ያሉ ምናምንቴዎቹንም እንቃኛለን።

የኛዎቹ የሚሊኒየም ሰዎች (በስም ያልታወቁት ተራሮች)


ኢትዮጵያ የሚሊየም ሰው ማነው ሲባል ብዙዎች የሚሽከረከሩት በዐጤ ሚኒሊክ፣ በቀ.ኃ.ሥ.፣ በኃይሌ ገ/ሥላሤ፣ በአበበ ቢቂላ፣ በይድነቃቸው ተሰማ፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ ጣዪቱ ብጡል፣… ዙሪያ ነው ለምን ግን? ባለፈው አንድ ሺህ ዓመት ለሀገራቸው የሠሩ ሰዎች እነዚህ ብቻ ናቸው? ለምን እነዚህ ተመረጡ? በሚዲያ ስለበዙ ወይንስ ነጮች እውቅና ስለሰጧቸው ነው? የሚሊኒየም ሠው ስንል የሚሊኒየሙ “ባለዜና” (ኒውስ ሜከር) ማለታችን ነው?

ኢትዮጲያ ተራራማና ፕላቶአማ ናት። ለመሆኑ ስንቱን ተራሮች ያውቃሉ? ራስደጀን፣ ጭላሎ፣ ጨርጨር፣ ካካ፣ ደብሊው ማውንቴይንስ፣ ባቱ፣ ዝቋላ፣ ከዚህ በላይ የሚሄዱ ጥቂት ሠዎች ናቸው። እርስዎስ ምን ያህል የሀገርዎን ተራሮች ያውቃሉ?

ብዙ የማናውቃቸው ተራሮች እንዳሉ ሁሉ በተራራ የሚመሰሉ የማናውቃቸው የሚሊኒየሙ ሠዎች አሉን።

ዘውዱን የተነጠቀው ንጉሥ

ሽበት ዘውዱን ሳይነጠቅ የሀገራችን የውስጥ ችግሮች (የወሰን ግጭቶች፣ የድንበር ፀቦች፣ የቤተሰብ አለመግባባት፣ አፈርሳታ፣ አውጫጭኝ፣ ጉማ፣ አቤቱታ፣…)ን ለመዳኘት የሀገር ሽማግሌዎች ችሎት ይቀመጡ ነበር። በቀዬው የተከበሩ፣ በእኩዮቻቸው እንኳን አንቱ የሚሰኙ፤ ሸምጋይና ሸንጋይ፤ ዝግ ብለው የሚናገሩት ተራራ ጫፍ ድረስ የሚጮህ፣ ተው ብለው የማስተው ኃይል ያላቸው፤ በጭካኔያቸው ሳይሆን በሩኅሩህነታቸው የሚፈሩ፣ ተናግረው ሳይሆን አዳምጠው የሚያሳምኑ፤ እሺ ብቻ እንጂ እንቢ የማይባሉ፤ አዘው ሳይሆን ሰርተው የሚያስተገብሩ፣ በዋርካ የሚመሰሉ፣ በቀዬ አድባርነት የሚጠሩ፣ ያለምንም ቅስቀሳ ለመሪነት የሚመረጡ፣ ያለምንም ተቃውሞ የሚሾሙ፣ በሽበታቸው የነገሱ የሀገር ሽማግሌዎች ነበሩን አሉንም።

እነዚህ የሀገር አድባሮች በችግር ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ማህበራዊ ጉዳዮች እጃቸው አለበት። ኮረዳና ኮበሌ ለጋብቻ መድረሳቸውን ለማረጋገጥ እነሱ ፊት ይቀርባሉ። ቤ/ክርስቲያን ሲተከል ቦታ የሚመርጡ፤ መስኪድ ሲሠራ ምሶሶ የሚያቆሙ፣ ልማት ሲጀመር የመሰረት ድንጋይ የሚያስቀምጡ በቀብር ጊዜ ጭብጥ አፈር በትነው ሟችን የሚያሰናብቱ እነሱ ናቸው።

የመንደሩ ሰውም በበዓላት ቀን የከበሬታ ስፍራ ይሰጣቸዋል። የመጀመሪያው መጠጥ የሚቀዳው ለነሱ ነው። እነሱም ሽክናውን ግጥም አድርገው አይጠጡም። ይቀምሱና ያስተላልፋሉ። ሌላውም በረከቱን ይቃመሳል። በሬ ሲጣል አንገቱን እንዲባርኩ ይጠራሉ። እነሱ ተነስተው ካልሔዱ ሸንጎው አይበተንም። እነሱ በበቅሎአቸው ተቀምጠው ጉዞ ሳይጀምሩ ጉባዔው ቤቱ አይሔድም።

እኒህ የቀዬ አድባሮች መንደርተኛው ይሄን ያህል እየተማመነባቸውንኳ ብቻቸውን አይፈርዱም። ይማከራሉ። ሕፃን ነው ብለው አይንቁም፣ ሴት ናት ብለው አያገሉም። ከዚህ ሁሉ በኋላ የተፈረደለትም ሆነ የተፈረደበት በሀገር ሽማግሌው ቅሬታ ሳያሳድሩ የአዛውንቱን መዳፍና ጉልበት ስመው ይሄዳሉ።

አስገራሚው ነገር ባልተፃፈ ሕግ፣ አስገዳጅ በሌለበት፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ በየትኛውም የኢትዮጲያ ክልል ያሉ እኒህ አረጋውያን ኃይሎቻቸው፣ አለቆቻቸው ሚስቶቻቸው ናቸው። ከችሎት ሲመለሱ ስልጣናቸውንም ሆነ ዘውዳቸውን ለሚስቶቻቸው ሰጥተው ሚስቶቻቸው ዘውዱን ይደፋሉ። አደባባይ ተራራ የሆኑት እኒህ ንጉሣን እቤት ሲገቡ ሜዳ ናቸው፤ ምንም ስልጣን የላቸውም። አንድ ጀግና እና የሚፈራ ንጉሥ የአምልኮ ስፍራ ሲገባ በፈቃዱ ራሱን ዝቅ አድርጎ ለፈጣሪው እንደሚንጓደድና እንደሚገዛ እኒህም አንቱ የተሰኙ ተራሮች አለቆቻቸው ሚስቶቻቸው ናቸውና በአክብሮት ለሚስቶቻቸው ይገዛሉ። በሚስቶቻቸው ላይ ማመፅ ባሕሪያቸው አይደለም።

ዛሬ ይህ የሽበት ዘውድ ከአረጋውያኑ ተነጥቆ ለነጂሚ ካርተር ተሰጥቷል። እኒህ የሀገር ሽማግሌዎች እያሉ የአውሮፓ ዩኒየን ተወካዮች እርቅ እንዲያወርዱ ይለመናሉ። በዘመናት የሸመገለ ሸምጋይ እያለን ለውስጥ ግጭታችን ባዕዳን ይጠራሉ። የኛ ታላላቅ ተራሮች እያሉ የአሜሪካና የአውሮፓ ኮረብታዎች ተዘፈነላቸው። የኛ ዋርካዎች ተቆርጠው እየተጣሉ የባሕር ማዶ ዛፎች ዋርካ ሆኑ። እናም መሬታችንን አደረቁት ችግራችንንም አባባሱት።

ቢሆንም ቢሆንም ላለፈው ሺህ ዓመት ሀገራችንን በንግሥና ገዝተዋልና አገልግለዋልና። ግንባር ቀደም የሚሊኒየም ሰዎቻችን ናቸው።

ጉበኛው (ፖስተኛው)

የፖስታ አገልግሎት ወደ ኢትዮጲያ ከመግባቱ ከ1880 በፊት መልዕክት ይተላለፍ የነበረው ጋራ ላይ ተቀምጠው ከከፍታ ወደ ከፍታ፣ ከጋራ ወደ ጋራ፣ ከተራራ ወደ ተራራ የጎሽ ቀንድን እንደ መለከት በመንፋትና በመጮህ ነበር። እነዚህ ሰዎች ጉበኞች (“በ” ሲነበብ ላላ ይላል።) በመባል ይታወቃሉ።

በአጤ ሚኒሊክ ዘመነ-መንግስት የፖስታ አገልግሎት ፅንሰ-ሀሳብ ሲገባ መልዕክት ከጉበኞች ወደ ፖስተኞች ተላለፈ። ፖስተኞች ፖስታውን ሰንደቅ ጫፍ ላይ ሰክተው ሜዳውን በፈረስ ጋራውን በእግር ወንዙን በዋና እየተሻገሩ ይጓዙ ነበር። ፖስተኛ በመሸበት አቅራቢያ መንደር ካለ ከማንም ቤት ተጠግቶ ማደር ይፈቀድለታል። ባደረበትም ቤት እግሩን አጥበውት፣ መኝታ አንጥፈውለት፣ አብልተው አጠጥተው፣ ስንቅ አስይዝው ይሸኙት ነበር። መልዕክተኛ ነውና በመንገድ ሽፍታንኳ አያስቆመውም። የያዘውን መልዕክት እስኪያደርስ በየደረሰበት ሁሉ ይከበር ነበር።

ይህ ፖስተኛ ከፀሐይ ሐሩር፣ ከሌት ቁር እየታገለ፤ በባዶ እግሩ፤ ጭቃና አቧራ ነው ሳይል፣ ሸጥና ገደል ሳይመርጥ፣ ጋራ ና አቀበት ሳይበግረው፤ ደራሽ ወንዝ ሳይፈራ፤ የቆላ ቁስልና የበርሀ ንዳድ እየተኮሰው፤ የዱር አውሬና በራሪ ነፍሳት እየተተናኮሉት፤ ረሀብና ጥማት እየተፈራረቁበት፣ መልዕክት ወይንም ደብዳቤ ያደርስ ነበር። ዛሬ ያ ፖስተኛ በዘመናዊ ፖስታ አገልግሎት ተተክቷል። ሆኖም ሀገራችንን ከጠረፍ እስከ ጠረፍ በማገኛኘት አገልግለዋል። ታሪክ ስማቸውን አላስቀመጠልንምና እኒህ ያልታወቁት ተራሮች የሚሊኒየማችን ሰዎች ተብለው ሊጠሩ ይገባል።

መምሕሩ

ከቄስ ት/ቤቱ የኔታ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲው ሌክቸረር ድረስ ያለው የቲቪ ካሜራዎች ያላዩት ኢትዮጲያዊው መምሕር፤ ከቢሮ-ሻሻ እስከ ገላዲን፤ ከዛላምበሳ እስከ ሞያሌ፣ ከጎሬ ጫካ እስከ ገልደጎብ በረሀ፤ ከሰሜን ተራሮች እስከ ባሌ ረባዳ መሬቶች፤ ዛፍ ስር ከሚያስተምረው ጀምሮ እስከ አ.አ. ዩኒቨርሲቲ ሕንፃዎች ያለው መምሕር ላለፈው ሺህ ዓመት ኢትዮጲያን ያቀና ነው።

ከቅኔ ፣ዜማ፣ ድጓ፣ ፆመ-ድጓ ጀምሮ እስከ ዲፕሎም፣ ቢ.ኤ ፣ ኤም.ኤ ፣ዲግሪ ፣ አስመራቂው መምሕር፣ ያኔ የቆሎ ተማሪው ከቆሮንጮው ከፍሎ ከሚሰጠው ደሞዝ በላይ የማይጠይቀው መምሕር፣ ዛሬ ድረስ በዝቅተኛ ደሞዝ ያስተምራል። ሁለት ጊዜ ሁለት ይሆናል አራት ብሎ ያስተማራቸው አለቃው እየሆኑ ሲሾሙ፤ ሀ-ግዕዝ ብሎ ፊደል ያስቆጠረው ተማሪ ሀገር ሲመራ፤ እሱ ግን ከዓመታት ዓመታትም በኋላ የነገውን ሀገር መሪ ዛሬም ሀ-ግዕዝን ያስቆጥራል።

ዛሬን በትላንት፣ ነገን በዛሬ የሚገነባው ላለፈው ሺሕ ዓመት ኢትዮጲያን ያቀና ነውና ፣ያ ስሙ ያልታወቀው ኢትዮጲያዊው ተራራ የሚሊኒየማችን ሰው ነው።

በጦር ሜዳ የወደቁት

ሀኒባል ሲሞካሽ፣ ካሌብ ሲወደስ፤ ለቴዎድሮስ ሲዘፈን፣ ለዮሐንስ ሲለቀስ፤ አሉላ ሲወደስ፤ ሲከበር ሚኒሊክ ፣ቀ.ኃ.ሥ. ሲመለክ፤ መንግስቱ ሲፈራ፣ መለስ ጅግና ሲባል አይተናል ሰምተናል ግን ግን ግን ሀኒባል በተሸለመ ዝሆን ላይ ሆኖ ሲያዋጋ፣ ያ በባዶ እግሩ ጦርና ጋሻ ይዞ ሲፋለም የነበረው ጥቁሩ ሀበሻ ስሙ ማነው?

ሚኒሊክ አድዋን አሸነፉ እየተባለ ሲከበር የመቀሌን ምሽግ ለማስለቀቅ፣ እሾሁ ላይ ጋሻውን እያነጠፈ ስባሪ ጠርሙሱ ላይ በባዶ እግሩ እየሮጠ የጣልያን ጥይት ማብረጃ የሆነው ስሙ ያልተጠራው በራሱ የቆረጠው ጀግና ስም አልነበረውም ይሆን?

ንጉሱ ወደ ለንደን ሲሸሹ ጣልያንን ገትሮ የያዘው አርበኛ ያልነው ባለመውዜር የነበረው ያልተሾመው ያልተሸለመው ኢትዮጲያዊን ወታደር ስሙን ማን ጠየቀው?

መቶ አለቃ ደምሴ ቡልቶ ጄኔራል ሲባሉና የ አ አ ሠ አዛዥ`ሆነው ሲሾሙ ካራማራ ተራራ ላይ እግሩን ጫማው ውስጥ ትቶ ያለፈውን የሚሊሺያ ስም ካራማራን እንጠይቀው ይሆን? ጭናክሰን ጋራ ላይ አጥንቱ ተለቅሞ መቀበር ያልተቻለው ያ ዘማች ወዛደር በታሪክ መዝገብ ላይ ስሙ ገብቶ ይሆን? ጅጅጋ፣ ዋርዴር፣ ገላዲን፣ ኦጋዴን የወደቀው ወዶ ዘማች ስሙን ማን እንበለው?

ጥላሁን ዋለልኝ ና ማርታ በስማቸው ሲዘፈንላቸው ለእናት ኢትዮጲያ ብልፅግናና ፍትርት ሲታገሉ በዓላማ ሳይሆን በሀይል የተሸነፉት ፣ምርጥ የአዲሲቷ ኢትዮጲያ የበኩር ልጆች ሞታቸው ሞት ሆኖ ደማቸው የማይደርቅ፣ ሕያው የትግል ቅርስ፣ በቀይ ሽብር እየተመቱ በየበራፉ ሲወድቁ ቢያንስ ስማቸውን በታሪክ አዕምሮ ልንፅፈው አይገባም ነበርን?

በከረን፣ በአፍ አበት፣ በናቅፋ፣ በእንደስላሴ፣ በሽሬ፣ በምፅዋ… ከሞቀ ቤቱ ወጥቶ ለሀገሩ የወደቀው የአሥራ ዘጠኝ ብር ከሀምሳ ደሞዝተኛው ስም ያለው ስም አልባ ብሔራዊ ወታደርስ?

ለሀየሎም ከበሮ ሲደለቅ፣ እነ ሥዩም መስፍን በአውሮፕላን ሲንሸራሸሩ፣ እነ ስዬ ቪላ ሲከፋፈሉ፣ የነመለስ ልጆች ከዲፕሎማቶች ጋር ውድ ት/ቤት ሲማሩ፤ የደርግን የቦንብ ድብደባ ለመሸሽ ከወንድሞቹና ከእህቶቹ ጋር የወየነው ብላቴናው ትግሬ ተጋዳላይ እከሌ ብለን እንጠራው ዘንድ ስም አለውን?

እነዛ ሰባ ሺህ እያልን በቁጥር የምንጠራቸው በባድሜ፣ በሽራሮ የወደቁት፣ ወንድምና እህት ኢትዮጲያውያን ሰባ ሺህ ነው ስማቸው?

ላለፈው ሺህ አመት ለሀገራቸው ሕይወታቸውን መስዋት ያደረጉ በስም ማናውቃቸው በጦር ሜዳ የቀሩ ያልታወቁት ተራሮች እነሱ ናቸው የሚሊኒየም ሰዎች

ሰብዐውያን

ማዘር ቴሬሳ ሳይፈጠሩ፣ ፣ዩኒሴፍ ሳይታለም፣ የ sos (save our sons) መስራች ሔርሜይል ኢትዮጲያን ሳያውቃት፣ ቻቺ የጎዳና ሕፃናትን ሳትሰበስብ፤ ዕጓለ-ማውታንን ሰብሳቢ፣ የአካል ጉዳተኛ ሕፃናቶችን ተንከባካቢ እናቶች በየገጠሩና በየመንደሩ ነበሩ። አሁንም አሉ። NGO ሳይፈጠር፣ በሕፃናት ስም ዕርዳታ መሰብሰብ ሳይጀመር፣ ከልጆቻቸው አፍ እየቀነሱ አሳዳጊ የሌላቸውን ሕፃናት አሳድገው ለወግ ማዕረግ ያበቁ ።ከገጠር ወደ ከተማ ለመማር የሚመጡትን እየተቀበሉ የሚያኖሩ፣ የሚያስተምሩ ኢትዮጲያውያን ቁጥር ጥቂት አይደለም:: ፈረንጅ ያያቸውን በቲቪም እናያቸዋለንና እናውቃቸዋለን። ግን ላለፈው ሺህ ዓመት ያልወለዷቸውን ሕፃናት በፍቅር ያሳደጉ ምርጥ ኢትዮጲያውያን ምንምንኳ በስም ባንጠራቸው እነሱም ያልታወቁት የሀገራችን ተራሮች ናቸውና የሚሊኒየም ሰዎች ተብለው ሊጠሩ ይገባል።

የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቀልቡ ያላረፈባቸው፣ ለጋዜጠኞቻችን የሞቀ ዜና የማይወጣቸው ግን እኔ በደረስኩባቸው ያየሁዋቸውን የኔን የሚሊኒየም ሰዎች ላስተዋውቃችሁ።

አቶ ኑረዲን ከማል ይባላሉ። የሚኖሩት በሐይቆችና ቡታጂራ አውራጃ ከወሊሶ ወደ አገና ከሚወስደው መንገድ ወደ ግራ የሚገነጠለው መንገድ የጎንቸ ቤቴ የተባለ የቸሀዎች መንደር ያደርሳል። የመንደሬው ሰው ዳሞ ነው የሚላቸው፣ ጎጆ ሲቀለስ ይጠራሉ። ከርቀት አንድ አይናቸውን ጨፍነው ይቆሙና በሳቸው በተገለጠች አንድ ዓይን ምሶሶ ይቆማል። ለአካባቢው ሰው ዋርካ ናቸው። እንሰት መሐል ተቀምጠው አፈር ሲጭሩ ሲያዩዋቸው ከሌላው ገበሬ አይለዩም። ዳሩ ነዋሪው በፈቃዱ ያነገሳቸው ንጉስ ናቸው። አባት ሴት ልጅ ለትዳር መድረሷን ለማወቅ እሳቸው ፊት ትቆማለች። ምንጭ የሚያስጠርጉ፣ ዛፍ የሚያስተክሉ እሳቸው ናቸው። የመስኪድ መስሪያ ቦታ በሳቸው ነው የሚጠቆመው

አቶ አቻምየለህ ባንጃው፣ በጅባትና ሜጫ አውራጃ የምትገኘውን ጀልዱ የተባለችውን ቀበሌ ከመሰረቱት አንዱ ናቸው። ቀልደኛና ተወዳጅ በመሆናቸው አዋቂዎች አቻሜ፣ ወጣቶችና ሕፃናት ጋሽ አቻሜ ብለው ነው የሚጠሩዋቸው። የተጣላ አስታራቂ፣ የልማት አስተባባሪ፣ ለችግር ደራሽ፣ ናቸው። ባለቤታቸው ወ/ሮ ፋናዬ የሁሉም እናት ሲሆኑ ከሀምሳ በላይ ሰዎች በስማቸው ይምላሉ። ወ/ሮ ፋናዬ ወለድ የማያስከፍሉ የቀበሌው ባንክም ናቸው። ባል የሀገር ዋርካ፤ ሚስት የሀገር መሬት ነበሩ። የሮሜዎና ጁሊዬትን ታሪክ የሚያስንቀው የእኒህን ባልና ሚስት አሟሟትን ታሪክ ልጆቻቸው እንደሚያስነብቡን ተስፋ አደርጋለሁ።

እማሆይ ተዋበች ወልደኪሮስና፣ ልጃቸው ወ/ሮ በላይነሽ ወርቅነህ በአዲስ አበባ ከተማ ሰባተኛ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ 39 የራሳቸው ያልሆኑ ልጆች አሳድገው አስተምረው ለወግ ለማዕረግ አብቅተዋል።

ወይዘሮ እልፍነሽ ከበደ፣ በጎጃም ክ/ሀገር በቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ በፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪ የነበሩ፣ ዕድሜ ልካቸውን ከገጠር የሚመጣ እንግዳ ተቀባይ ሲሆኑ ለዚህ አገልግሎታቸው ማንም አይከፍላቸውም ነበር። እኒህ ሴት ቤት ውስጥ (በኔ ስሌት) እስከ 1990 በቀን 36 እንጀራ ያልቃል።

አቶ ባሕሩ ወዳጄነህ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በአሥመራ መንገድ አካባቢ ለም ሆቴል እየተባለ በሚጠራው ቦታ ነዋሪ የነበረ ሲሆን በ1962 እንደ ኢትዮጲያ አቆጣጠር አለምን በሞተር ሳይክል ዞሮ ጨርሷል።

አቶ (መምሕር) ጣሠው ቸርነት፣ በአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ የካ ሚካኤል ቤት ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ስዕል በጠቅላላ ሲሰሩ ምንም አልተቀበሉም። በሚያስተምሩበት በዘርፈሽዋል ት/ቤት ከሥራቸው ውጭ ተማሪውን ኡሉ አንዳንድ ሚስማር እንዲያመጣ አዘው ለትምህርት ቤቱ የሳይንስ ማዕከልና ቤተ መፅሐፍት ይሰሩ ነበር።

የሱርማ ተወላጁ ብሔራዊ ወታደር ኦላራጌ በትግራይ ክ/ሀገር ሽሬ እንደስላሴ ሰኔ 9 1981 ዓ.ም. ሰራዊቱ በፈንጂ በታጠረ ክልል ውስጥ ገብቶ ሳለ በፈቃዱ ፈንጂው ላይ በመሮጥ ራሱን ሲሰዋ ሌላው ሰራዊት እሱ ሞቶ ባፀዳው መንገድ ማለፍ ችሏል።

ጀርመን ሀገር በፍራንክፈርት ከተማ ነዋሪ የሆኑት ፀጋዬ ወርቁ፣ እህቶቹና ወንድሞቹ ከኢትዮጲያ በስደት የሚመጡትን (ለደህንነታቸው ስል እዚህ ላይ መግለፅ በማልችለው መንገድ) ከመርዳታቸውም ሌላ ቤታቸው ወስደው አሳድረው፣ አገር እስኪላመዱ ድረስ ያስተናግዳሉ። እስከ 2000 እ.ኤ.አ. ድረስ 35 ኢትዮጲያውያንን ተቀብለው መርዳታቸውን አውቃለሁ።


እነሆ የኔዎቹ የሚሊኒየም ሠዎች፣ በሀገራችን ያሉት እነዚህ ብቻ አይደሉም። እናንተስ በኖራችሁበት አካባቢ ባለፋችሁበት ቦታ፤ ለሚሊኒየም ሰውነት የምታጯቸው የሉም? የናንተዎቹን ሰዎች አጠር ካለ ታሪካቸው ጋር ላኩልኝና የኛ የሚሊኒየም ሰው እናርጋቸው። ቢያንስ ለሚሊኒየሙ ዓመት ስማቸውን በድረ-ገፅ እንፃፍላቸው።


ጠመኔ ነኝ ቶሮንቶ ካናዳ

temenew@yahoo.ca