ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ጋር ተስማምቶ ለመኖር

ከውክፔዲያ

ከኤች·አይ·ቪ ጋር መኖር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ጋር መኖር ማለት ቫይረሱ በደሙ ውስጥ እንዳለ የተረዳ ሰው ራሱን አረጋግቶና ችግሩን እንደማንኛዉም የጤና ችግር በማየት ቫይረሱ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነሰ እና ለመከላከል በሕክምና፣ በአመጋገብ፣ እንዲሁም በባህርይ ላይ አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን በማምጣት ጥሩ ሕይወት መኖር ማለት ነው። አንድ ሰው ኤች·አይ·ቪ አለበት ማለት አሁኑኑ ታሞ ይተኛል ወይም በቅርቡ ሕይወቱ ያልፋል ማለት አለመሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች የእድሜ ማራዘሚያ መድሀኒቶችን (ፀረ-ኤችአይቪ መዳኒቶች) በመጠቀም ለረጅም ዓመታት ጤናማ ሆነው ለመኖር ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች የበሽታዉ ምልክት ጨርሶ ሳይታይባቸው ከ15 ዓመት በላይ ከቫይረሱ ጋር መኖር እንደሚችሉ አንዳንድ ጥናቶችም ያመለክታሉ። ኤች·አይ·ቪ ቫይረስ በደም ውስጥ በመኖሩ ምክንያት ሊሰማ የሚችለዉን ስሜት አውነታውን መቀበል መቻል በጣም አስፈላጊ ነው። ጥሩ ያልሆኑትን ስሜቶች ለማስወገድ የሚከተሉትን ምክሮች መቀበልና መተግበርም ተገቢ ነው።

 • ሁኔታዎች እያደር የተሻሉ እንደሚሆኑ ተስፋ ማድረግ፦ ፈታኝ የሆነ ሰሜት ሲሰማ ሁኔታዎች ሁሉ ከጊዜ ጋር እየተሻሻሉ እንደሚሄዱ ማመን በጣም ጠቃሚ ነው። የተሻለ ሁኔታ እንደሚኖር ተስፋ የሚሰጡ ብዙ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ የራስን ጤንነት መጠበቅና የቀድሞውን የተረጋጋ ህይወት እንደገና መጀመር አንዱ መንገድ ነው።
 • ከኤች·አይ·ቪ ጋር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር መመካከር፦ ማንኛውንም የሚሰማን ስሜት ወይም የህመም ምልክት፤ ሌሎችም ምናልባት ተመሳሳይ ስሜት እና ምልክት ሊኖራቸው ስለሚችል ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር መመካከር ወይንም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ወደመሠረቷቸው ማህበራት በመሄድ የምክር እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ ነው።
 • ሁሌም የሚያስደስቱን ነገሮች ከማድረግ አለመቆጠብ፦ አንድ ሰው ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደሙ ውስጥ መኖሩን ካወቀ በኋላ የደረሰበትን ድንጋጤ ለማስወገድ ቀደም ሲል ያደርጋቸው የነበሩትን አስደሳች ስራዎችን በመቀጠል አሁን የተፈጠሩበትን የኀዘንና የብስጭት ሰሜቶችን መርሳት መቻል ይገባዋል። ዘወትር ሲያደርገው ያስደስቱት የነበሩትን ሥራዎች በቀጣይነት ማድረግ ኀዘን ወይም ጭንቀት ላይ ብቻ እንዳያተኩር ይረዳል።
 • አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፦ ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖር ሰው ድካም ሊሰማዉና ሊጫጫነው ይችላል። በዚህ ጊዜ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ብርታትና ጥንካሬ ይሰጣል። ከፍተኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ባይሆንም እንኳን ቀላል እርምጃዎችን ማዘውተር ለአእምሮና ለሰውነት ጤንነት በጣም አስፈላጊ ነው።
 • ጎጂ የሆኑ ቅፅበታዊ ለውጦችን በህይወት ላይ አለማድረግ፦ ሥራን አለመተው፣ ዘመድ ወዳጆችን አለመራቅ፣ ንብረቶችን አለመሸጥ። በእርግጥ አንድ ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖር ሰው የወደፊት እቅዱን ሊለውጥ ይችላል፤ ይህ ለውጥ ጫና ያልበዛበትና ውጤቱም ጠቃሚ መሆኑን አስቀድሞ መለየት ያስፈልጋል።
 • ባለሞያን ማማከር፦ ስለ ኤች·አይ·ቪ/ኤድስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመኖሪያ አካባቢያችን እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ማህበራትን ወይም ድርጅቶችን ማወቅ ጠቃሚ ነው። አንድ ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖር ሰዉ የጭንቀት እና የመከፋት ስሜት ካለቀቀው የህክምና ባለሞያዎች ወይንም አማካሪዎችን በስልክም ሆነ በአካል ማግኘትና ማማከር ያስፈልገዋል።
 • ያስታውሱ! ብቻዎን አይደሉም ፦ኢትዮጵያ ውስጥ ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን ተኩል በላይ ሰዎች አሉ። በአሁኑ ጊዜ 12 በመቶ ገደማ የሚሆኑ ከኤች·አይ·ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ይኖራሉ። በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ዕድሜያቸው በ15 እና በ49 መካከል የሚገኙ ከ4 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ጋር ይኖራሉ። አንድ ኤች·አይ·ቪ ቫይረስ በደሙ ውስጥ ያለበት ሰው በቫይረሱ ለመያዝ ሆን ብሎ የሰራው ስህተት ስለሌለ ራሱን መውቀስ እና መጨነቅ የለበትም። ማድረግ ያለበት ነገር ቢኖር ለሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች እንዳይጋለጥ ራሱን እንዲጠብቅ ትምህርት ማግኘት እና ከኤች.አይ.ቪ ነፃ የሆኑ ሰዎች ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ስብዓአዊነት ተስምቶት ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግና፣ ከተቻለም ማስተማር።

ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸዉ አውቀው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያሉበትን የጤና ሁኔታ ተቀብለው ራሳቸውን በማረጋጋት ወደፊት በተሻለ መንገድ ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማሰብ ይጀምራሉ። እራሰን አረጋግቶ ለመኖር ከዚ በታች የተጠቀሱት ጠቃሚ መመሪያዎች በዝርዝር ጠንቅቆ ማወቅ አጥጋቢ የሆነ የፀባይ እና የአኗኗር ለውጥ ለማምጣት ይረዳል፦

 • ኤች·አይ·ቪ ቫይረስ በደም ዉስጥ መኖሩን በታወቀበት ጊዜ ሊገጥም የሚችለውን የጭንቀት እና የፍርሃት ስሜት እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል፤
 • አጋጣሚን ጠብቀው የሚመጡ የበሽታ ስሜት/ምልክቶች በሰውነት ላይ ሲታዩ መወሰድ ያለባቸውን ህክምና እና ጥንቃቄ፤
 • የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ የራስን ንፅህና መጠበቅ እና የሰውነት እንቅስቃሴ የማድረግ አስፈላጊነትን፤
 • ጥንቃቄ ስለተሞላበት የግብረ ሥጋ ግንኙነት እና ስለወሊድ።

ተስፋ እና የወደፊት ህይወት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከኤች.አይ.ቪ ጋር ኑሮን በሠላም ለረጅም እድሜ መምራት እንደሚቻል መገንዘብ አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ህጋዊ መብታቸውን የሚያከብሩ ህግጋት እንዲደነግጉ ድጋፍን በመስጠት የራስን አስተዋፅኦ በማድረግ ተስፋን እውን ማድረግ። በተጨማሪም የዕለት ዜናዎችን በመከታተል፣ባለሞያዎችን ወይንም አማካሪዎችን በመጠየቅ በኤች.አይ.ቪ ላይ ያሉ አዳዲስ የህክምና እና የመድሀኒት ግኝቶችን መከታተልና ማወቅ ተስፋን ይሰጣል። ስለ ኤች.አይ.ቪ ዕውቀትን ማዳበርና ይበልጥ ማወቅ ራስን በደንብ ለመንከባከብ ይረዳል። አንድ ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖር ሰው ልጆች ካሉት ህመም ሲጠና ልጆችን የሚንከባከብ ሰው ቀድሞ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

ህክምና[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ክትባት ወይም ፈዋሽ መድኀኒት ባይገኝለትም ምርምሩና ሙከራዉ እንደቀጠለ ነው። የዕድሜ ማራዘሚያ መድሃኒቶች (ፀረ-ኤችአይቪ መዳኒቶች) ቫይረሱ በደም ውስጥ የሚያደርገውን የስርጭት ፍጥነት ለመግታትና ለማስቆም የሚወሰዱ መድሃኒቶች ናቸው። በሰውነት ዉስጥ የሚገኘውን የኤች.አይ.ቪ ቁጥር መቀነስ ይችላሉ፤ መድሃኒቶቹ ቫይረሱን ከናካቴው ማጥፋት አይችሉም። መድሃኒቶቹን ያለ ህኪም ትዕዛዘና ፍቃድ መውሰድ በጤንነት ላይ ትልቅ ችግር ያስከትላል። የመድሃኒቶቹ ተጠቃሚ ሰው አንድ በቅርብ ሆኖ የሚከታተለው ብቃት ያለው የህክምና ባለሙያ ያስፈልገዋል።

አመጋገብ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ሰውነታችንን እና የሰውነት የመከላከያ አቅማችንን እንደሚያጠነክር ሁሉ በቀላሉ ለበሽታ እንዳንጋለጥም ይጠቅመናል። ከኤች·አይ·ቪ ጋር የሚኖሩ ስዎች በምግብ እና ውኀ ውስጥ ለሚገኙ በሽታን ወይም ህመምን ሊያስከትሉ ለሚችሉ ጀርሞች በቀላሉ የተጋለጡ በመሆናቸዉ፤ በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ሲመግቡ ንጽህናውን የጠበቀ የአመጋገብ ሥርዓት መከተልና የሚጠጣው ውሃ ንጹሀ መሆኑን ማረጋግጥም በጣም ጠቃሚ ነው። ከኤች·አይ·ቪ ጋር የሚኖሩ ስዎች የተለያዩ ዓይነት ምግቦችን በመመገብ ያልተፈለገ የሰውነት ክብደት መቀነሰን ለመከላከል እና ጡንቻዎቻቸዉ እንደጠነከሩ እንዲቆዩ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው። ሁሉም የምግብ ዓይነቶች የተለያዩ ጥቅሞች አላቸዉ። የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች በሚከተለው መሰረታዊ ምድቦች ተከፋፍለው ሊታዩ ይችላሉ።

 • ገንቢ ምግቦች፦ ባቄላ፤ አተር፣ ምስር፣ እንቁላል፣ ሥጋ፣ አሣ፣ ዶሮ፣ ወተት፣ አይብ እና ለውዝ ሰውነትን ለመገንባት የሚያስችሉ የምግብ ንጥረ ነገሮችን ይዘዋል።
 • ኃይል ሰጪ ምግቦች፦ ለሰውነት የሚያስፈልገውን ኃይል ሁሉ የምናገኝባቸው የምግብ አይነቶች እንደ በቆሎ፣ እንጀራ፣ ዳቦ፣ ድንች፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ስንዴ፣ አጃ፣ ዳጉሳ፣ ማሽላ፣ ስኳር፣ ማርማላት፣ ማርጋሪን፣ ዘይት፣ ሲሆኑ በተጨማሪም እንደ ለውዝ እና አቮካዶ የመሳሰሉ የቅባት ምግቦችንም ያጠቃልላል።
 • የሰውነትን የመከላከል አቅም የሚያጎለብቱ ምግቦች፦ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ የሰውነታችንን አቅም በማጎልበት በሽታን በሚገባ ለመቋቋም ያስችላል፤ እንዲሁም እንደ ካሮት፣ ሰላጣ እና ጎመን የመሳሰሉ ምግቦችንም መመገብ ቫይታሚን ለማግኘት ይረዳናል።

የሰዉነትን የመከላከል አቅም ለማጎልበት፦

 • የምግብን የመፍጨት ሂደት ሊያውኩ የሚችሉ እንደ ቃሪያ፣ በርበሬ ወይም ሚጥሚጣ የመሳሰሉ እና ሌሎች ቅመማ ቅመም የበዛባቸውን ምግቦች በብዛት አለመመገብ፣ ለስለስ ያሉ እንደ አልጫ ወጥ ያሉ ምግቦችን መመገብ፣ ከህይለኛ ቅመሞች ይልቅ የጥብስ ቅጠልን የመሳሰሉ የምግብ ማጣፈጫዎች መጠቀም ያስፈልጋል።
 • ፍራፍሬ እና የአትክልት አመጋገባችንን መጨመር፣ እነዚህን የሰውነት የመከላከል አቅም የሚያጎለብቱ ምግቦች በቫይታሚንና በማዕድን የበለፀጉ በመሆናቸው ሰውነታችንን ከበሽታ ይከላከላሉ። በመሆኑም እንደ ቆስጣ እና ጎመን የመሳሰሉ በጣም አረንጓዴ የሆኑ የቅጠላቅጠል ምግቦችን፣ እንደ ዱባ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ ማንጎ እና የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን በየቀኑ መመገብ ያስፈልጋል። በተጨማሪም ከጤፍ፣ ከጥቁር ስንዴ፣ ገብስ የተዘጋጁ ዳቦዎችን እና ሌሎች ምግቦችን መመገብ።

ዉኃ ለሰውነታቻን ከሚያሰፈልጉን ነገሮች አንዱ ነው። በየቀኑ ቢያንስ 8 ብርጭቆ ዉሃ መጠጣት ጠቃሚ ነው። የምንጠጣው ዉሃ ንፁህ መሆን አለበት። ከኤች. አይ.ቪ ጋር የሚኖር ሰው እንደ ተስቦ፣ ኮሌራ፣ ቢልሀርዚያ እና ጃርዲያ ለመሳሰሉት በተበከለ ውኃ አማካኝነት በሚተላለፉ በሽታዎች የተጋለጠ ስለሆነ በቀጥታ የህይቅ ወይም የምንጭ ውኃ ከመጠጣት ፈልቶ የቀዘቀዘ ውኃ መጠጣት በጣም አስፈላጊ ነው።

ሰዉነታችንን በጤንነት ለማቆየትና ቫይረሱ በጤና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ቫይታሚን ኤ፣ ቢ6፣ ቢ12፣ ሲ፣ ዚንክ፣ አይረን፣ ኮፐር፣ ማንጋኒዝ፣ ማግኒዥየም እና ሴሊኒየም ጨዉ የመሳሰሉትን ሁሉ መመገብ ይጠቅማል። የሰዉነትን የተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅም በማጎልበት ረገድ ቫይታሚን ኤ፣ ሲ፣ ኢ፣ እና ከማዕድናትም ዚንክ በጣም ጠቃሚዎች ናቸው። እነዚህ የምግብ ንጥረ-ነገሮች በተፈጥሮ ከተለያዪ ምግቦች ዉስጥ ይገኛሉ።


የቫይታሚኖች እና የማዕድናት መገኛ:
ቫይታሚን 'ኤ' ጉበት፣ ቅቤ፣ አይብ፣ እንቁላል፣ ቆሰጣ፣ ቢጫና አረንጓዴ አትክልቶች ' ቫይታሚን ቢ12 ' ጉበት፣ ኩላሊት፣ አሳ፣ ሥጋ፣ ዕንቁላል፣ ወተት ቫይታሚን 'ሲ' ቲማቲም፣ ድንች፣ ማንጐ
ቫይታሚን 'ኢ'የአትክልት ዘይት ' አይረን ' የበሰለ ጉበት፣ ኩላሊት፣ እንጀራ፣ ቀይስጋ እና ዕንቁላል፣ ' ኮፐር ' ጉበት፣ ለውዞች፣ ባቄላ፣ ስጋ፣ አሳ፣ ዶሮ፣ እና የስንዴ ዳቦ፤
ቫይታሚን 'ቢ6' ከስንዴ የተዛመዱ ምግቦች፣ ጉበት፣ ሙዝ፣ ስጋ፣ ድንች፣ አትክልት፣ ዕንቁላል እና ለውዞች፤ ' ዚንክ ' የስንዴ ዳቦ፣ እንቁላል፣ ባቄላ፣ ሩዝ፣ አረንጓዴ ቅጠላማ አትክልቶች፣ ድንች ጉበት ስጋና ለዉዝ፤ ' ሴሊኒየም ' ጉበት፣ ኩላሊት፣ ልብ፣ ቀይ ስጋ፣ የወተት ምርቶች፣ አትክልት እና ፍራፍሬ
' ማግኒዥየም ' አደንጓሬ፣ ለውዞች፣ የስንዴ ዱቄት፣ ቡናማ ሩዝ፣ ደረቅ አተር፣ አትክልቶች፣ ሰጋ፣ ሙዝ፣ አረንጓዴ ቅጠላማ አትክልቶች፤ ' ማንጋኒዝ ' የስንዴ ዳቦ፣ ለውዝ፣ ፍራፍሬ ፣ አረንጓዴ ቅጠላማ አትክልቶች፣ ጉበት፣ የስራስር አትክልቶች፣ ስጋ እና አሳ

አንዳንድ ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ ባለመመገባችን ምክንያት የሚከተለውን ክፍተት ለማካካስ በፋብሪካ የተዘጋጁ ቫይታሚኖችን እንወስድ ይሆናል። ቅድሚያ መስጠት የሚገባን የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ ተፈላጊ የሆኑትን የምግብ ንጥረ ነገሮች ማግኘት ቢሆንም የቫይታሚን እንክብሎችን መውሰድ አስፈላጊ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ። በግምት ብዙ ቫይታሚኖችን መውሰድ ጤንነትን ስለሚያቃውስ የቫይታሚን እንክብ በሚወሰድበት ጊዜ በህክምና ባለሞያ ትዕዛዝ መሰረት መሆን አለበት።

በምግብ አዘገጃጀት እና አመጋገብ ምክንያት ሊከሰቱ ከሚችሉ በሽታዎች ራስን መከላከል[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከኤች·አይ·ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች በምግብ ምክንያት ለሚመጡ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸዉ። አንዳንድ ጎጂ የሆኑ ጀርሞች ከጥሬ ስጋ፣ ምግቡን ከሚያዘጋጁ ሰዎች ወይም አብረዉ እንጀራ ከሚበሉ ሰዎች አፍና እጅ ንክኪ ሊሸጋገሩና የምንመገበውም ሊበከል ይችላል። ከኤች·አይ·ቪ ቫይረስ ጋር የሚኖር ሰው በምግብ መመረዝ ሲታመም ለማዳን በጣም ከባድ ከመሆኑ ሌላ በሽታው በተደጋጋሚ ሊመላለስበት ይችላል። እንደ ኮሶ፣ ወስፋት እና አሜባ የመሳሰሉት በሽታዎች ከፍተኛ የጤና ችግርን እንዲሁም ሞትን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ከነዚ በሽታዎች አብዛኛዎቹ በቀጥታ በበሽታዎቹ ከተያዘ ሰው የሚተላለፉ ቢሆንም ባልበሰለ ወይም ንጽህናው ባልተጠበቀ ምግብ፣ በነፍሳት (ተባዮች) በተበከለ ምግብ፣ የምግብ አያያዝ ሥርዓትና ደንብን ባልተከተለ ሰው ተዘጋጅቶ በሚቀርብ ምግብ አማካይነት ሊተላለፉ ይችላሉ። ምግብን በደምብ ማብሰል ባክቴርያና ጀርሞች እንዲሞቱ ይረዳል። ከኤች·አይ·ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ጥሬ ሥጋ ወይም ጥሬ ክትፎም ሆነ ለብለብ ክትፎ ባይመገቡ ይመረጣል። በተጨማሪም ከቤት ውጭ በሆቴሎችና ቡና ቤቶች ውስጥ መመገብ ምግቡ እንዴት እንደተዘጋጀ ስለማይታወቅ ለህመም ሊያጋልጥ ይችላል። ከተቻለ ከቤት ውጭ አለመመገብ፤ ካልሆነም ምግቡ እንዴት እንደተዘጋጀ እና ጥሬ የሆኑ የምግብ ውህዶች ማለትም ያልበሰለ ሥጋ፣ እንቁላል ወይም አትክልት የሌለበት መሆኑን ጠይቆ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ዕፅ እና አልኮል[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዕፅም ሆነ አልኮል በብዛት መውሰድ የሰውነትን የተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅም ያዳክማል። ጤናማ ሆኖ ለመኖርም ሆነ ጤንነትን ለመንከባከብ አልኮልንም ሆነ ዕፅን መጠቀምን እስከመጨረሻው መተው አማራጭ መንገድ ቢሆንም ይህንን ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊያደርገው አይችልም። የሚወሰደው የሲጋራ፣ የዕፅ ወይም የአልኮል መጠንን በተቻለ መጠን መቀነስ ጤንነትን በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅም ይረዳል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የተሻለ ጢና እንዲኖር ከመርዳቱ ሌላ የመጨነቅ፣ እና የድካም ስሜትን ይቀንሳል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ራስን ዘና የሚያደርግና የልብን ምት እንዲጪምር ተደርጎ መሠራት አለበት እንጂ እስኪደክሙ መሆን የለበትም። ተገቢውን የየአካል ብቃት እንቅስቃሴ መጠን ለማወቅ ቢቻል የስፖርት ባለሞያዎችን አስቀድሞ ማማከር የተሻለ ነው። በየቀኑ ከ30 እስከ 60 ደቂቃ ያህል በእግር መጓዝ የተሻለ ጤና እንዲኖረን ከሚረዱት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች አንዱ ነው።

ወሲብና ፍቅር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አንድ ከኤች·አይ·ቪ ጋር የሚኖር ሰው ስለራሱ ጤና በተመለከተ መብቱ የተሰጠዉ ለራሱ በመሆኑ ለፈለገው ሰው መንገር፣ ካልፈለገ ደግሞ ያለመናገርም ውሳኔው በእጁ ነው። ነገር ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ አለ። በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ የሰፈረ ድንጋጌ አንድ ሰው የሌላውን ሰው ጤንነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሆን ብሎ ይሁን በቸልተኝነት የሚጎዳ ተግባር ከፈጸመ እንደሚቀጣ ያስረዳል። ስለዚህ ከወሲብ ጓደኛ ጋር በሚኖር ግንኙነት ቫይረሱ ወደዛ ጓደኛ እንዳይተላለፍ ኮንዶም መጠቀም ያስፈልጋል ። ይህ ከሆነ ከኤች·አይ·ቪ ነፃ የሆነውን ወዳጅ ከቫይረሱ ለመጠበቅ ይረዳል። ከኤች·አይ·ቪ ጋር ነዋሪ መሆንን ለወሲብ/ፍቅር ጓደኛዎ አንዳንድ ጊዜ በቀጥታ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተዘዋዋሪ መናገር ይቻላል። ለምሳሌ ስለቅድመ ወሲብ ጥንቃቄ ወይም ስለ ኤች·አይ·ቪ እና መተላለፊያ መንገዶች በማንሳት መነጋገር ይቻላል።

ወሊድ ( ኤችአይቪ ያለባት እናት)[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አንዲት ሴት ኤች·አይ·ቪ በደሟ ውስጥ ቢኖርም እንኳን ልጆች ማፍራት ትችላለች። ተገቢውን ጥንቃቄ እና የህክምና ክትትል ካደረገች ከኤች·አይ·ቪ ነፃ የሆነ ጤነኛ ልጅ ሊኖራት ይችላል። ይሁን እንጂ ለኤች·አይ·ቪ የሚጋለጥም ልጅ ሊኖር ይችላል። ልጅ ለመውለድ እቅድ ካለ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ማለት እና የህክምና ባለሞያን ማማከር ያስፈልጋል

 • የጤንነት ሁኔታ- በእርግዝና ወቅት በብዛትም ሆነ በጥራት የተሻለ የምግብ አቅርቦት መኖር አለበት። ከኤች·አይ·ቪ ጋር የሚኖር ሰው ደግሞ ከፍ ያለ የምግብ መጠንና የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ማግኘት ያስፈልገዋል።
 • ፅንሱን ከቫይረሱ መከላከል- ኤች·አይ·ቪ በደም ውስጥ መኖሩን አውቆ ልጅን ከኤች·አይ·ቪ ለመታደግ አስፈላጊውን እቅድ ማዉጣትና ተገቢውን ህክምና መከታተል የልጅን በቫይረሱ የመያዝ አጋጣሚ ለመቀነስ ይረዳል።
 • በደም ዉስጥ የኤች·አይ·ቪ መኖር- ወደፊት አንድ ወቅት ላይ የኤድስ ታማሚ ሊሆኑ እና አልጋ ላይ የመዋል አጋጣሚ ሊመጣ ይችላል። ስለዚህ ልጅዎ ያለ ተንከባካቢ እንዳይቀር ቀደም ብሎ ሁኔታዎችን ማመቻቸትም ያስፈልጋል።

ኤች·አይ·ቪ እና ሰብአዊ መብት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከኤች·አይ·ቪ ጋር መኖር ከማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር አያሳንሰም። ኤች·አይ·ቪ በደም ውስጥ በመኖሩ በሰብአዊ ፍጡርነት ሊኖር የሚገባውን መብት ሊያጓድል የሚችል አንድም ምክንያት የለም። ይህም ማለት ከኤች·አይ·ቪ ጋር የሚኖር ማንኛውም ሰው እንደሌሎች

 • እንደማንኛውም ሰው ቫይረሱ በደሙ ያለበት ሰው የጤና አጠባበቅ አገልግሎት፣ ሥራ እና የትምህርት ዕድል የማግኘትና፣ በማህበራዊ ክንውኖች፣ ለምሳሌ፣ ዕድር፣ በዕምነት፣ በማህበራት ወይም የስፖርት ቡድን በመሳሰሉ ማህበራዊ ተቋማት አባል የመሆን መብት አለው።
 • ከኤች·አይ·ቪ ጋር የሚኖር ሰው ቤት የመከራየት ወይም ባለንብረት ለመሆን፣ የጤና፣ የህይወት ወይም የንብረት መድን የመግባት መብት አለው።

ከኤች·አይ·ቪ ጋር በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚደረግ መድልዎ ዋና ዋና መንስኤዎች አሉት፦ እነዚህም

 • ስለ ኤች·አይ·ቪ ቫይረስ መተላለፊያ መንገዶች ዝቅተኛ ወይም የተሳሳተ መረጃ መኖር፤
 • በቂ ግንዛቤ ካለማግኘት ወይም ከተሳሳተ መረጃ ላይ በመመርኮዝ የሚመጣ ፍርሃት፤
 • ስለግብረ ስጋ ግንኙነት በግልጽ መነጋገር እንደ ነውር ስለሚቆጠር፤

በሥራ ቦታ ላይ ስለሚደርስ መድልዎ ማወቅ፦ አንድ ሰው ከኤች·አይ·ቪ ጋር በመኖሩ ምክንያት መገለል ወይም አድልዎ ከደረሰበት ከቀጣሪው ጋር በመነጋገር ወይም በፍርድ ቤት በመክሰስ ፍትህ የማግኘት መብት አለው። ሕግም ከለላና ጥበቃ ያደርግለታል። የኢፌዴሪ የኤች·አይ·ቪ/ኤድስ ፖሊሲ ማግለልና አድልዎን በግልጽ ይከለክላል።


የውጭ መያያዣዎች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

1. አበሻ ኬር [1] Archived ኦገስት 20, 2008 at the Wayback Machine

2. የእንግሊዘኛ ውክፔዲያ [2]

3. [3] Archived ኤፕሪል 12, 2013 at the Wayback Machine

4. [4]