Jump to content

ኩዱር-ማቡግ

ከውክፔዲያ
የኩዱር-ማቡግ ስም ያለበት በሴት ሠራተኛ ቅርጽ የሆነ መሠረት ችንክር

ኩዱር-ማቡግ (ወይም ኩዱር-ማቡክ) የአሞራውያን አለቃ በመስጴጦምያ ነበር። አባቱ ሰምቲ-ሺልሃክ ሲሆን የሁለታቸው ስሞች ኤላማኛ በመሆናቸው ኤላማዊ እንደ ነበሩ ይታስባል። ሆኖም ኩዱር-ማቡግ እራሱ አሞራዊ ወይም ግማሽ አሞራዊ ነበር የሚሉ መምህሮች አሉ። የኩዱር-ማቡግ ማዕረግ «የማርቱ አባት» ሲሆን፣ ከ1739 ዓክልበ. ጀምሮ «የያሙትባል አባት» ሆነ።

በ1745 ዓክልበ. ኩዱር-ማቡግ የላርሳን ድካም ንጉሥ ሲሊ-አዳድን ከዙፋኑ አስወግዶ የራሱን ልጅ ዋራድ-ሲን ዘውዱን አጫነው። እንዲሁም ኩዱር-ማቡግ ካዛሉን፣ ሙቲባልንና ኤሽኑናን እንዳሸነፈ ይመስላል። ሌላውም ልጅ ሪም-ሲን ወንድሙን በላርሳ ዙፋን በ1734 ዓክልበ. ተከተለ። የኩዱር-ማቡግ ሴት ልጅ ኤን-አነዱ ደግሞ የኡር መቅደስ ከፍተኛ ሴት ካህን ሆነች። ሌላም ወንድ ሊጅ ሲን-ሙባሊት ተባለ። እነዚህ ልጆች ስሞች ሁሉ አካድኛ እንጂ ኤላምኛ አይደሉም። ሌላ ሴት ልጁ ማንዚ-ዋርታሽ ግን ኤላምኛ ስም አላት።

ኩዱር-ማቡግ ምናልባት 1730 ዓክልበ. አካባቢ ዓረፈ።