Jump to content

ካሩም

ከውክፔዲያ
መካከለኛ አናቶሊያ

ካሩም በጥንት (2150-1628 ዓክልበ. ያሕል) የአሦር ሰዎች በውጭ አገራት በተለይ በሐቲ (አናቶሊያ) ያቋቋሙት የንግድ ሠፈሮች ነበሩ።

ኤብላ ጽላቶች መካከል አንዱ ሰነድ ከኤብላ (በሶርያ) እና ከአሹር (ወይም ከአባርሳል?) መካከል የተዋወለ ውል ሲሆን በዚህ ውል አሹር በኤብላ ግዛት ውስጥ ካሩም ለማስተዳደር ፈቃድ አገኘ።

ከዚህ ጥቂት ዓመታት በኋላ የአካድ ንጉሥ ታላቁ ሳርጎን ኤብላን አጠፋ። ከኋለኛ ዘመን በኬጥኛ በተጻፈ ታሪክ ዘንድ፣ የቡሩሻንዳ ንጉሥ ኑርዳጋል በካሩሞች የነበሩትን አካዳዊና አሦራዊ ነጋዴዎች መደብ ስለ በደለ፣ ሳርጎን ደግሞ አናቶሊያን ወረረ። ይህም ድርሰት በአማርና ደብዳቤዎች መካከል በአካድኛ ተገኘ፤ ቅጂዎቹ ግን በሳርጎን ዘመን ስላልተጻፉ እንደ ታማኝ ታሪክ አይቆጠሩም።

በሐቲ እነዚህ የአሦራውያን ነጋዴ ሠፈሮች ከሐቲ ከተሞች አጠገብ ይመሠረቱ ነበር፤ ቀረጥም ለከተማው ገዢ ያስረክቡ ነበር።[1] አነስተኛ «መባርቱም» የተባሉት ጣቢያዎች ደግሞ ነበሯቸው። በተለይ 1880-1745 እና 1662-1628 ዓክልበ. በጠቅላላ የካሩምና የመባርቱም ቁጥር ምናልባት ፳ ያሕል ነበር። ከነዚህም ውስጥ ካነሽአንኩቫሐቱሳሽ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በዚሁ ዘመን መደበኛ ገንዘብ (መሀልቅ) ገና አልተፈጠረም ነበር። የአሦር ነጋዴዎች ወርቅ በጅምላ፣ ብር ለችርቻሮ ይጠቅማቸው ነበር። የወርቅ ዋጋ ከብር ፰ እጥፍ መሆኑ ተወሰነ። ሆኖም ሌላ የብረታብረት አይነት በአሦርኛ «አሙቱም» ሲባል ይህ ከወርቅም በላይ ውድ ነበር፤ ከብር ፵ ጊዜ ተላቀ። «አሙቱም» ምናልባት ያንጊዜ ትኩስ ግኝት የነበረ ብረት ሊሆን ይቻላል። እነዚህ የአሦር ነጋዴዎች በተለይም ቆርቆሮልብስ ለሐቲ ሰዎች ይሸጡ ነበር። ከሐቲ አገር ካስወጡአቸው ውጤቶች መካከል ከሁሉ አይነተኛ የሆነው መዳብ ነበረ።[2]

በሐቲ ዙሪያ ያሉት ከተማ-አገራት ሲወዳደሩ ሲታገሉ አንዳንዴ ለንግድ አስጊ ሁኔታ ይፈጥር ነበር። በ1745 ዓክልበ. ግድም ዋናው የካነሽ ካሩም ተቃጠለ፤ ይህን ያደረገው የዛልፓ (በጥቁር ባሕር ዳር) ንጉሥ ኡሕና ይታስባል። የኩሻራ ንጉሥ ፒጣና በ1662 ዓክልበ. አካባቢ ካነሽን ይዞ በልጁ አኒታ መንግሥት የአሦራውያን ነጋዴዎች ሊመለሱ ቻሉ። የአኒታም መንግሥት የኬጥያውያን መንግሥት መንስኤ ሆነ። በኋላ «የአላሕዚና ሰው ዙዙ» ተከተለው። [3] ከዙዙ በኋላ በአሦርም ብሔራዊ ጦርነት በደረሰው ወቅት ካሩሞቹ ከአናቶሊያ ጠፉ። ትልቁም ካሩም ካነሽ በ1628 ዓክልበ. ግብድ. በሻላቲዋራ ከተማ ንጉሥ እጅ ጠፋ።

  1. ^ Seton Lloyd : Ancient Turkey ( Translation: Ender Verinlioğlu) Tubitak, Ankara, 1998 p 18-19
  2. ^ Ekrem Akurgal: Anadolu Kültür Tarihi,Tubitak, Ankara,2000 ISBN 975-403-107-X p 40-41
  3. ^ The Oxford Handbook of Ancient Anatolia, 2011 p. 76, 588