ክዋሜ ንክሩማህ

ከውክፔዲያ
Kwame Nkrumah (1961)

ክዋሜ ንክሩማህ የተወለዱት በ1909 እ.ኤ.አ. ደቡባዊ ምዕራብ ጋና (ቀደም ሲል ጎልድ ኮስት) ንክሮፉል በምትባል ከተማ ነው። ንክሩማህ በካቶሊክ ሚሽነሪ ትምህርት ቤት ይማሩበት በነበረ ወቅት ብሩህ አዕምሮ እንደነበራቸው የተመሰከረላቸው ሲሆን ገና በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ እያሉ ነው በአቅራቢያቸው በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆኑት። ይሁንና ያለሥልጠና የጀመሩትን ትምህርት በ1926 እ.ኤ.አ.አክራውን አቺሞታ ኮሌጅ ተቃለቅለው የመምህርነት ምሥክር ወረቀት በማግኘት በተለያዩ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች አስተምረዋል። በ1935 እ.ኤ.አ. ወደ አሜሪካ በማቅናትም የፔንሴልቬኒያውን ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ተቀላቅለው በኢኮኖሚክስሶሲዮሎጂ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በ1939 የተቀበሉ ሲሆን በ1942ም በሥነ-መለኮት ሌላ ድግሪ ከዚሁ ዪኒቨርሰቲ አግኝተዋል። በ1942 እና በ1943ም የማስተርስ ድግሪያቸውን ከፔንሴልቬኒያ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ትምህርትና በፍልስፍና ሠርተዋል።

በአሜሪካ ቆይታቸውም በግራ ዘመም አሰተሳሰቦች በመማረከቸው የተነሳ በወቅቱ በሥርነቀል ለውጥ ፈላጊነታቸው ከሚታወቁ ምሁራን ጋር ቅርብ ግንኙነት መሥርተው ነበር። አፍሪካውያንን ያሰባሰበ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መሥራችና ግንባር ቀደም ተናጋሪ እንዲሁም የአፍሪካ አገራት ነፃ እንዲወጡና የአውሮፓ ቅኝ ግዛት እንዲያበቃ ቁርጠኛ አቋም ነበራቸው። ከዚሁ ጎን ለጎንም የተባበረች አፍሪካ አስፈላጊነትን በማመን አፍሪካውያንና የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው ሕዝቦች በአንድነት እንዲቆሙ የሚሰብከው ፓንአፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ነበሩ። በ1945 ወደ ለንደን ሕግና ኢኮኖሚክስ ለማጥናት ባመሩበት ወቅትም በማንችስተር እንግሊዝ የተካሄደውን 5ኛው የፓን አፍሪካን ጉባዔ እንዲካሄድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የአፍሪካን ከቅኝ ግዛት የመውጣት እንቅስቃሴ ለማስተባበርና ቅኝ አገዛዝን ለመቃውም የተደራጀው ጉባዔ ንክሩማህ ታዋቂ የጥቁር መብት ታጋዮችና የፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄ መሪዎች ጋር እንዲገናኙ ዕድል የሰጣቸው ሲሆን በ1946ም ጥናታቸውን ትተው በ5ኛው ጉባኤ የተቋቋመው የምዕራብ አፍሪካ ብሔራዊ ጽ/ቤት ዋና ጸኃፊና የምዕራብ አፍሪካ ተማሪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል።

ከዚያም በ1947 ወደ አገራቸው በመመለስ የጎልድኮስት ኮንቬንሽን ፓርቲ ዋና ጸኃፊ በመሆን በመላው አገሪቱ እየዞሩ ሕዝቡን ለፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሉ የሚያነሳሱ ቅስቃሳዎችን አድርገዋል። በ1948 የበለጠ ሥር-ነቀል ባህርይ ያለው ኮንቬንሽን ፒውፕልስ ፓርቲ የሚባል የፖለቲካ ድርጅት የበማቋቋም ተከታታይ አድማዎችንና ተቃውሞችን በማደራጀት ቅኝ ገዥው ኃይል የማሻሻያ እርምጃዎችን እንዲወስድ ማስገደድ ችለዋል። ንክሩማህ በእስር ቤት ሆነው የተሳተፉበትን የ1951 ምርጫም ከእስር ቤት ሆነው ማሸነፍ ሲችሉ ፓርቲያቸውም በርካታ ወንበሮችን ማግኘት ችሎ ነበር። በቅኝ አገዛዝ ሥር በተመሰረቱ አስተዳደሮች በምርጫ በማሸነፍ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ አገራቸውን በ1957 ጋና በሚል አዲስ ስያሜ ነፃ እንደትወጣ አደረጉ።

ንክሩማህ ከነፃነት በኋላም የተዋሃደና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ለመመሥረት አገሪቷ ያላትን ሃብት ሁሉ አስተባብሮ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ወደ መሞከር ነበር የገቡት። የፓንአፍሪካኒዝም ዋነኛ አቀንቃኝ በመሆናቸውም ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ የሚታገሉ የነፃነት ንቅናቄዎችን ለጋስ ድጋፍ ከመቸር ወደ ኋላ አላሉም ነበር። በ1960ዎቹ በርካታ የአፍሪካ አገራት ነፃ መውጣትን ተከትሎም አፍሪካውያን የተባበሩት የአፍሪካ መንግሰታት የሚባል አንድ መንግሥት እንዲመሠረቱ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። ይህ ፍላጎታቸው መሳካት ባይችልም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) እንዲመሠረት የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ንክሩማህ በመሪነት በቆዩበት ጊዜ ውስጥ ስኬታማ ሥራዎችን የሠሩ ቢሆንም ጠንካራና አምባገነናዊነት የተቀላቀለበት የአመራር ዘይቤያቸው የኋላኋላ በ1966 ቻይናን በመጎብኘት ላይ በነበሩበት ወቅት በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን እንዲወገዱ ምክንያት ሆኗል። ቀሪ ጊዜያቸውን በሳሞራ ሚሸሏ ጊኒ ያሳለፉ ሲሆን በ1972 ሕክምና ለማግኘት በሄዱባት ሮማኒያ ውሰጥ አርፈዋል።

በ2004 ዓም የአፍሪካ ኅብረት አዲሱ ሕንፃ በተመረቀበት ሥነ-ሥርዓት አፍሪካ ለአንድነቷና ለነፃነቷ ከታገሉላት ግንባር ቀደም መሪዎች መካከል አንዱ ለሆኑትን የጋናውን ክዋሜ ንክሩማህ ሃውልት በማሠራት አክብራለች።