Jump to content

ኮንግ ጅያ

ከውክፔዲያ

ኮንግ ጅያ (ቻይንኛ፦ 孔甲) በጥንታዊ ቻይና የሥያ ሥርወ መንግሥት ዘመን ንጉሥ ነበር። እሱ የቡ ጅያንግ (1745-1687 ዓክልበ. የነገሠው) ልጅ ነበር።

የቀርከሃ ዜና መዋዕል በተባለው ጽሑፍ ዘንድ፣ ለዘመኑ የተዘገበው እንዲህ ነው፦ በመጀመርያው ዓመት በሆ ወንዝ ምዕራብ ኖረ። የጨወይ አለቃ ከቦታው አለቀቀ፣ ለው-ሉይ ደራጎኖቹን እንዲመገብ ሾመው። በሦስተኛው አመት (1659 ዓክልበ.) ንጉሡ በ«ፉ ተራሮች» አደነ። በ፭ኛው ዓመት (1657 ዓክልበ.) «የምሥራቅ ሙዚቃ» ፈጠረ። በ፯ኛው ዓመት ለው-ሉይ ወደ ሉያንግ ሸሸ። በአንድ ትውፊት ዘንድ፣ ለው-ሉይ የሸሸበት ምክንያት በአደራው ካሉት ደራጎኖች አንዲትዋ ስታርፍ ቅመም ጨምሮ ለንጉሥ አመገበው። ንጉሥም ወድዶት ስለ ጠፋች ደራጎን ሲጠይቅ ፈርቶ ሸሸ ይባላል።

ኮንግ ጅያ አጉል እምነት ያለውና መረን ንጉሥ ተባለ። በሌላው ትውፊት ዘንድ፣ በፉ ተራሮች እያደነ፣ ደብዛው ጠፍቶ ወደ አንድ ገበሬ ቤት ገብቶ ሚስቱ ስትወለድ አገኛቸው። ለእድሉ እንዲሆን ንጉሡ ሕፃኑን ለራሱ በጉዲፈቻ ወሰደው፣ በኋላ ታድጎ ልጁ በአደጋ በመጥረቢያ ተገደለ። ስለዚህ ንጉሡ «መጥረቢያውን ለመስበር» የሚባል ዘፈን ፈጠረ፣ ይህም «የምሥራቅ ሙዚቃ» የተባለው ነው።

የሢማ ጭየን ታሪካዊ መዝገቦች ደግሞ ስለ ኮንጅያ አስተዳደር ሙስና የቻይና መኳንንት ከዘመኑ ጀምሮ እስከ ሻንግ ሥርወ መንግሥት መሠረት ድረስ (1611 ዓክልበ.ግ.) ዓመጽ ያድርጉ ነበር በማለት ይጨምራል።

ቀዳሚው
ጂን
የሥያ (ቻይና) ንጉሥ
1661-1652 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ጋው