ወደ ሮማውያን ፲፪
ወደ ሮማውያን ፲፪ | |
---|---|
አጭር መግለጫ | |
ፀሐፊ | ጳውሎስ |
የመጽሐፍ ዐርስት | ወደ ሮማውያን |
የሚገኘው | በአዲስ ኪዳን ፮ኛው መጽሐፍ |
መደብ | የጳውሎስ መልዕክት |
ወደ ሮማውያን በአዲስ ኪዳን የመጀመሪያው መልዕክት ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንጦስ እያለ በ፶ ዎቹ ዓ.ም. የጻፈው መልዕክት ነው ። ይህ ምዕራፍ ፲፪ ሲሆን በ፳፩ ንዑስ ክፍሎች ይከፈላል ። ጳውሎስ በዚህ መልዕክቱ ፣ ክርስቶስ ከኃጢያት ነፃ የሆነውን ሰውነቱን ስለኛ አሳልፎ እደሰጠ እኛም ከኃጢያት የነፃ ሥጋችንን መስዋት እናድርግ ብሎ ይጀምራል ።
ቅዱስ ጳውሎስ ለሮማውያን መልዕክቱን የጻፈበት ምክኒያት አይሁዳውያንና ሮማውያን በሰላም አንድላይ በሮም ለብዙ ዘመን ሲኖሩ ቆይተው ክርስትና በተመሠረተበት ወቅት ፣ አይሁዳውያን ክርስቶስ እኛን ነው የመረጠን ለመንግሥቱ እናንተን አይደለም... ሲሊ ሮማውያን ደግሞ እናንተ ሰቀላችሁት እንጂ ምን አረጋቹህለት... እየተባባሉ እርስበርሳቸው ጥል ስለፈጠሩ እነሱን ለማስታረቅ ጻፈው ።
የጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮማውያን ምዕራፍ ፲፪
1፤እንግዲህ፥ወንድሞች፡ሆይ፥ሰውነታችኹን፡እግዚአብሔርን፡ደስ፡የሚያሠኝና፡ሕያው፡ቅዱስም፡መሥዋዕት፡ አድርጋችኹ፡ታቀርቡ፡ዘንድ፡በእግዚአብሔር፡ርኅራኄ፡እለምናችዃለኹ፥ርሱም፡ለአእምሮ፡የሚመች፡ አገልግሎታችኹ፡ነው። 2፤የእግዚአብሔር፡ፈቃድ፡ርሱም፡በጎና፡ደስ፡የሚያሠኝ፡ፍጹምም፡የኾነው፡ነገር፡ምን፡እንደ፡ኾነ፡ ፈትናችኹ፡ታውቁ፡ዘንድ፡በልባችኹ፡መታደስ፡ተለወጡ፡እንጂ፡ይህን፡ዓለም፡አትምሰሉ። 3፤እግዚአብሔር፡ለያንዳንዱ፡የእምነትን፡መጠን፡እንዳካፈለው፥እንደ፡ባላእምሮ፡እንዲያስብ፡እንጂ፡ማሰብ፡ ከሚገ፟ባ፟ው፡ዐልፎ፡በትዕቢት፡እንዳያስብ፡በመካከላችኹ፡ላለው፡ለያንዳንዱ፡በተሰጠኝ፡ጸጋ፡እናገራለኹ። 4፤ባንድ፡አካል፡ብዙ፡ብልቶች፡እንዳሉን፥የብልቶቹም፡ዅሉ፡ሥራ፡አንድ፡እንዳይደለ፥ 5፤እንዲሁ፡ብዙዎች፡ስንኾን፡በክርስቶስ፡አንድ፡አካል፡ነን፥ርስ፡በርሳችንም፡እያንዳንዳችን፡የሌላው፡ ብልቶች፡ነን። 6፤እንደ፡ተሰጠንም፡ጸጋ፡ልዩ፡ልዩ፡ስጦታ፡አለን፤ትንቢት፡ቢኾን፡እንደ፡እምነታችን፡መጠን፡ትንቢት፡ እንናገር፤ 7፤አገልግሎት፡ቢኾን፡በአገልግሎታችን፡እንትጋ፤የሚያስተምርም፡ቢኾን፡በማስተማሩ፡ይትጋ፤ 8፤የሚመክርም፡ቢኾን፡በመምከሩ፡ይትጋ፤የሚሰጥ፡በልግስና፡ይስጥ፤የሚገዛ፡በትጋት፡ይግዛ፤የሚምር፡ በደስታ፡ይማር። 9፤ፍቅራችኹ፡ያለግብዝነት፡ይኹን።ክፉውን፡ነገር፡ተጸየፉት፤ከበጎ፡ነገር፡ጋራ፡ተባበሩ፤ 10፤በወንድማማች፡መዋደድ፡ርስ፡በርሳችኹ፡ተዋደዱ፤ርስ፡በርሳችኹ፡ተከባበሩ፤
11፤ለሥራ፡ከመትጋት፡አትለግሙ፤በመንፈስ፡የምትቃጠሉ፡ኹኑ፤ለጌታ፡ተገዙ፤ 12፤በተስፋ፡ደስ፡ይበላችኹ፤በመከራ፡ታገሡ፤በጸሎት፡ጽኑ፤ 13፤ቅዱሳንን፡በሚያስፈልጋቸው፡ርዱ፤እንግዳዎችን፡ለመቀበል፡ትጉ። 14፤የሚያሳድዷችኹን፡መርቁ፥መርቁ፡እንጂ፡አትርገሙ። 15፤ደስ፡ከሚላቸው፡ጋራ፡ደስ፡ይበላችኹ፥ከሚያለቅሱም፡ጋራ፡አልቅሱ። 16፤ርስ፡በርሳችኹ፡ባንድ፡ዐሳብ፡ተስማሙ፤የትዕቢትን፡ነገር፡አታስቡ፥ነገር፡ግን፥የትሕትናን፡ነገር፡ ለመሥራት፡ትጉ።ልባሞች፡የኾናችኹ፡አይምሰላችኹ። 17፤ለማንም፡ስለ፡ክፉ፡ፈንታ፡ክፉን፡አትመልሱ፤በሰው፡ዅሉ፡ፊት፡መልካም፡የኾነውን፡ዐስቡ። 18፤ቢቻላችኹስ፡በእናንተ፡በኩል፡ከሰው፡ዅሉ፡ጋራ፡በሰላም፡ኑሩ። 19፤ተወዳጆች፡ሆይ፥ራሳችኹ፡አትበቀሉ፥ለቍጣው፡ፈንታ፡ስጡ፡እንጂ፤በቀል፡የእኔ፡ነው፥እኔ፡ብድራቱን፡እመልሳለኹ፡ይላል፡ጌታ፡ተብሎ፡ተጽፏልና። 20፤ጠላትኽ፡ግን፡ቢራብ፡አብላው፤ቢጠማ፡አጠጣው፤ይህን፡በማድረግኽ፡በራሱ፡ላይ፡የእሳት፡ፍም፡ ትከምራለኽና። 21፤ክፉውን፡በመልካም፡አሸንፍ፡እንጂ፡በክፉ፡አትሸነፍ።
- ቁጥር ፩
- ቁጥር ፪
- ቁጥር ፫
- ቁጥር ፭
- ቁጥር ፱ - ፳፩