Jump to content

ዛይሴ

ከውክፔዲያ
(ከዘይሴ የተዛወረ)

ዛይሴ ወይም ዘይሴኢትዮጵያ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኝ ብሔረሰብ ነው። የዛይሴ ብሔረሰብ በጋሞ ጎፋ ዞን በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኤልጎ፣ወዘቃ እና ዛይሴ ደንብሌ በሚባሉ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖር ሲሆን፣እነዚህ ቀበሌዎች ከጋሞጎፋ ዞን ርዕሰ ከተማ አርባ ምንጭ በ22 ኪ.ሜ. ርቀት ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ከአርባ ምንጭ ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ ኾንሶና ዲራሼ ልዩ ወረዳዎች የሚያቋርጠው አውራ መንገድ የኤልጎንና የወዘቃ ቀበሌዎችን አቋርጦ ያልፋል። ብሔረሰቡ በዋናነት የሰፈረባቸዉ ቀበሌያት የመሬት አቀማመጥ የጫሞ ሐይቅ ዳርቻን የጋሞ ሰንሰለታማ ተራሮችንና የመጨረሻ ጫፍ ኮረብታማ አካባቢን ይዞ የሚገኘውን ለእርሻና ከብት ርቢ ምቹ የሆነ ለም መሬትን ሲያካትት፤የአየር ንብረቱ ደጋ፣ ወይናደጋና ቆላማ ነው። በ1999 ዓ/ም በተደረገው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት መሠረት የብሔረሰቡ ሕዝብ ብዛት 17,884 ነው።

የብሔረሰቡ አባላት የኢኮኖሚ መሠረት ጥምር ግብርና ሲሆን ለፍጆታና ለገበያ የሚውሉ የተለያዩ ሰብሎችን ያመርታል። በቆላማው የአየር ንብረት ክልል በቆሎ፣ጥጥ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ማንጎ፣ አቦካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ሎሚ ለገቢ ምንጭነት የዝናብን ወቅት በመጠበቅና መስኖ በመጠቀም ያመርታሉ። “ሀለኮ” /ሽፈራው/ የተባለውን ተክል ለምግብነትና ለመድሐኒትነት ተግባር በስፋት ይመረታል። ንብ ማነብ ሌላው የብሔረሰቡ ተግባር ሲሆን ከቤት እንሰሳት የዳልጋ፣ የጋማ ከብቶችንና ፍየሎችን ያረባሉ። ከግብርና በተጨማሪ የዕደ ጥበብ ስራዎችን ለገቢ ምንጭነት ይጠቀሙባቸዋል።

የብሔረሰቡ ቋንቋ በብሔረሰቡ አባላት «ዘይሴቴ»ተብሎ ሲጠራ ሌሎች ደግሞ «ዛይሴኛ» ይሉታል። የዛይሴቴ ቋንቋ ከምሥራቅ ኦማዊ ቋንቋዎች ቤተሰብ ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፤ ከጋሞና ከኮሬቲቴ ቋንቋዎች ጋር ይመሳሰላል። ቋንቋው ከመግባቢያነት አልፎ ለሌላ ተግባር አልዋለም። ።

ታሪካዊ አመጣጥና አሠፋፈር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የብሔረሰቡን ታሪካዊ አመጣጥና አሰፋፈር በተመለከተ በተለያዩ ሕዝቦች አካባቢ በተከሰቱ እንቅስቃሴዎች የተነሣ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ጎሳዎች በፈጠሩት የረጅም ጊዜ ማህበራዊ መስተጋብር የዛይሴን ብሔረሰብ እንዳስገኙ ይነገራል። እነዚህ ጎሣዎች ወደ አካባቢው ለምን እንደተንቀሳቀሱና እንደሰፈሩ በምክንያትነት የሚነገረው አካባቢው ለእርሻና ለከብት ርቢ ምቹ መሬት ለኑሮ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ያለው መሆኑ ነው። በብሔረሰቡ በርካታ ጎሣዎች እንዳሉ ሲነገር ከነዚህም መካከል “ቡቡር”፣”ብልዝና” “ማልዝ” ነባር ጎሣዎች ሲሆኑ የተቀሩት ከጋሞ፣ከደራሼ፣ ከሞሲዬና ከኮሬ በተለያዩ ጊዜያት መጥተው የተቀላቀሏቸው መሆኑን የብሔረሰቡ አዛውንቶች ይናገራሉ። ከእነኚህ በተጫማሪም ቀደም ባሉት መንግሥታት በሥራና በሰፈራ ምክንያት ከጋሞ፣ከኮንሶ፣ከዎላይታ፣ከጎፋና ከአማራ የመጡ ሕዝቦች ከብሔረሰቡ ጋር አብረው እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ባህላዊ አስተዳደር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዘይሴዎች የራሣቸው የሆነ ጥንታዊ ባህላዊ አስተዳደር አላቸው። የባህላዊ አስተዳደሩ ቁንጮ «ካቲ» ወይም ንጉሱ ይባላል፡፤ ካቲዎች የሚነግሱት አመጣጡ ከጋሞ-ኮሌ አካባቢ “ዝሄ” ከሚባል ሥፍራ “ከዙሌሣ” ጎሣ ነው። የካቲው ሥልጣን የዘር ሀረግን ተከትሎ ከአባት ወደ ልጅ በውርስ የሚተላለፍ ሲሆን ለመሪነት የሚያበቃው ገና ሲወለድ የእህል ዘር፣ እርጥብ ሣር ወይም የከብት እበት ይዞ ከእናቱ ማህፀን የሚወጣው ወንድ ልጅ ነው ተብሎ ይነገራል። ይህም በባህሉ “ኤቃ” ወይም /ገዳም/ የመልካም ገድ ተምሳሌት ነው ተብሎ ይታመናል። ከካቲው ልጆች መከካከል የመጨረሻ ወይም ታናሽ እንኳን ቢሆን ከኤቃ ጋር ከተወለደ የካቲው ወራሽ የሚሆነው እርሱ ይሆናል። ወራሽ ልጅ መሪው ወይም ካቲው በሕይወት እስካለ ድረስ ከአባትየው ርቆ እንዲኖር ይደረጋል። ለዚህም በምክኒያትነት የሚጠቀሰው ወራሹ ከአባቱ ጋር ከኖረ ለአባትየው ሕይወት አስጊ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው።

ከባህላዊ መሪው በታች አቻ ሥልጣን ያላቸው በሕዝብ የሚመረጡ «ማጋ» የተባሉ ሰባት የሕዝብ መሪዎች አሉ። የማጋዎቹ ሥልጣንም እንደ ካቲው ሁሉ የዘር ሐረግን ተከትሎ ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ነው። ከማጋዎች ቀጥለው የሚገኙት የሥልጣን አካላት «ሶሮፋዎች» ሲባሉ ዋና ተግባራቸው ለበላይ መሪዎች የማማከር አገልግሎት መስጠት ነው። የሚመረጡትም በሕዝብ ሸንጎ ነው። በወታደራዊ አመራር ረገድ “ቶራ ቃራ” የሚባሉ የጦር አዛዦች እንደነበሩ ይነገራል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ባህላዊ አስተዳደር አካላት በአስተዳደሩ ማዕከል በሆነው “ማርታ” /ቤተመንግሥት/ ዙሪያ በመሰባሰብ የፖለቲካ አስተዳደሩን ይመሩ ነበር። ንጉሡ የራሱ የጦር ሠራዊት አለው። በዚህ ጦር ውስጥ ዕድሜው 18 ዓመት የሞላው ወጣት ለካቲው ይሰጥና ወታደራዊ ሥልጠና ይወሰዳል። ከሥልጠናው መልስ ምሽግ በመቆፈር አካባቢውን በመጠበቅ ወታደራዊ ግዴታውን የመወጣት ኃላፊነት ይሰጠዋል።

በባህላዊ አስተዳደሩ የሴቶች ተሣትፎ ዝቅተኛ ነው። በቤትና በሸንጎ የመስተንግዶ ስራን ከመምራት ውጪ የመዳኘት መብት የላቸውም። ይሁንና የካቲው ሚስት ባሏን በማማከር ትረዳዋለች። የሴቶች ምክርና ግሣፄ ይደመጣል። ምክንያቱም ግሣፄዋን የጣሰ ያሰበው አይሳካለትም ወይም አይሟላለትም ተብሎ ስለሚታመን ነው። በሌላ በኩል ከአጎራባች ሕዝቦች ጋር አለመግባባት ሲከሰት “ኦጌማጋ” በሚባል አገናኝ አማካይነት በመላላክ “ዱላታ” /የሕዝብ ሸንጎ/ ተካሂዶ የዕርቅ ሥርዓት ይፈፀማል። ጉዳዩ ጠንከር ያለ ከሆነ በካቲውና በማጋዎች አማካይነት በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ይፈታል። በዚህም የተነሣ የዛይሴ ብሔረሰብ ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር በርካታ ባህላዊ ጉዳዮችን ይጋራል። በአስተራረስ፣ በአለባበስ በሰርግና በለቅሶ ስርዓት አፈጻፀምና በሌሎችም ባህላዊ ወጎች ተመሣሣይነት አለው። ይሁንና ብሔረሰቡ ራሱን በራሱ ሲያስተዳድር ከነበረበት የቀድሞ ሁኔታ በውጫዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት ባህላዊ አስተዳደርሩም ሆነ ሌሎች ባህላዊ ዕሴቶቹ መዳከማቸው አልቀረም። በባህላዊ ሥርዓቱ ላይ ጫና ከፈጠሩበት ዓቢይ ምክንያቶች የአፄ ምኒልክ የመስፋፋት ዘመቻ እና የጣሊያን ወረራ ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው።

ባህላዊ ዕሴቶች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የጋብቻ ሥርዓት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በብሔረሰቡ የጋብቻ ሥርዓት የሚፈፀመው በአቻ ጎሣዎች መካከል ነዉ። በአንድ ጎሣ ውስጥ የሚመደቡ እርስ በርስ ጋብቻ አይፈፅሙም። በብሔረሰቡ ባሕል ሴቶች ፈፅሞ አይገረዙም፣ ወንዶች አልፎ አልፎ በስለት ወይም ቆንጨኮ /ወተት የሚወጣውን ተክል/ በመጠቀም ግርዛት ይፈፀማሉ። ለጥሎሽ ጥንት በዓይነት እስከ ሰባት ከብት፣ ለልጅቱ ወላጆችና ቤተዘመድ ይከፈል ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የጥሎሹ መጠን በጥሬ ገንዘብ ከ1,000-2,000 ብር እንደደረሰ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የበዓላት አከባበር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ብሔረሰቡ ከሚያከብራቸው መንፈሳዊና ባህላዊ በዓላት “ደሴከሶ”፣”ኤቃ”፣”አልሶ”፣” መስቀል”፣ “ገና” የተባሉት ተጠቃሽ ናቸዉ። ደሴ ከሶ (የእኩያሞች በዓል) በተመሣሣይ የዕድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ ወጣቶች በአማካይ ሥፍራ ተሰብስበው የብሔረሰቡ ባህል ወግና ታሪክ ለወጣቶች በብሔረሰቡ አዛውንቶች እየተተረከና እየተወሳላቸው እነርሱም የታሪክ ተረካቢ መሆናቸው እየተገለፀላቸው ለክብረ ባዕሉ በተዘጋጀው ድግስ ታድመው በጋራ እየበሉና እየተጫወቱ በአገሬው ሽማግሌዎች ተባርከውና ተመርቀው የአንድ ትዉልድ ስያሜ የሚያገኙበት በዓል ነው። ኤቃ /መስዋዕት የማቅረቢያ በዓል/ በዚህ የብሔረሰቡ ሃይማኖታዊ በዓል “ማጋዎች” ለአካባቢያቸው ሰላምና ብልፅግናን በመሻት ፈጣሪአቸው “ኢንአ”/ማካ/ በሚባሉ የባህላዊው ሥርዓተ አምልኮ ፈፃሚዎች አማካይነት ለብሔረሰቡ አምልኮት መስዋዕት በማቅረብ ፀሎት የሚያቀርቡበት ሥርዓት ነው። አልሶ በአካባቢው አሉታዊ ተፈጥሮአዊ ክስተቶች /ድርቅ፣የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ፣ ወዘተ... /ሲከሰት ከዚህ መቅሰፍት እንዲታደጋቸው ካቲውና ማጋዎች በፀሎትና በምልጃ ለፈጣሪያቸው መስዋዕት የሚያቀርቡበት ሥርዓት ነው። የመስቀል በዓል፡- ካቲውና ማጋዎች ለበዓሉ ተለይቶ በተዘጋጀ ሥፍራ ደመራ ደምረው ችቦ በማቀጣጠል የአካባቢው ሕዝብ እየበላና እየጠጣ በጭፈራ የሚያከብረው በዓል ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከክርስትና እምነት ጋር በተያያዘ የገናና የፋሲካ በዓላት በአካባቢው ብሔረሰብ በድምቀት ያከበራሉ።

ባህላዊ ጨዋታዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በባህላዊ ጨዋታዎች ረገድ ሴቶችና ወንዶች በአንድነት ተሰባስበው ሴቶቹ በስነ ቃል ጎሣቸውን ሲያሞጋግሱ ወንዶች በጭብጨባና በክራር በታገዘ እንቅስቃሴ ሽቅብ እየዘለሉ ይጨፍራሉ። ከሙዚቃ መሣሪያዎች ዋሽንት (ሱልንጌ) ክራር/ዝንቤ/፣ ዛዬ የትንፋሽ መሣሪያ በራሣቸው ጥበብ በመሥራት ደስታቸውንና ሃዘናቸውን በሚገልጹበት ወቅት በማጀቢያነት ይጠቀሙባቸዋል።

የዘመን አቆጣጠር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ብሔረሰቡ የራሱ የሆነ የቀን፣ የወርና የዓመት አቆጣጠር አለው። የሰባት ቀናትና የአሥራ ሁለት ወራት የራሣቸው መጠሪያ ሲኖራቸው ወቅቶችንም ከሐምሌ - ሕዳር “ሴቴ”፣ ከታህሣሥ - የካቲት “ቦኔ”፣ ከመጋቢት - ሰኔ “ባርጎ” በሚል ስያሜ ከፋፍለው ይጠሯቸዋል።

ባህላዊ የቤት አሰራር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዛይሴዎች ሰፋ ያለ ዝግጅት በማድረግ ባለሦስት ማዕዘን ግድግዳ ቤታቸውን በአበሻ ፅድ በመገርገድና ጣሪያውን በጠንካራ ሰንበሌጥ በመክደን ይሠሩታል። ሣሩ በእበትና በጭቃ ስለሚነከር እሣት ቢነሳ እንኳን የመቋቋም ኃይል አለው። የቤቱን ጣራ ብዙውን ጊዜ ከስምንት እስከ አሥራ ሁለት በሚሆን የጥድና የወይራ ምሰሶዎች ከውስጥ ወደ ዉጪ በመወጠር ያቆሙታል። ዘይሴዎች የቤት ቁሣቁሦችን፣የእርሻ እና የሙዚቃ መሣሪያዎችን እንዲሁም ሌሎች መገልገያዎችን በባህላዊ መንገድ ሠርቶ የመጠቀም ባህል አላቸው። የሽመና ውጤት የሆኑትን ቡልኮ፣ጋቢ፣ ነጠላና ቆልኤ ከጥጥ ያዘጋጃሉ። የእርሻ መሣሪያዎችን ከእንጨትና ከብረት በመሥራት ሲገለገሉ ገበቴ/ጎንጌ/ ፣ሾርቃ(ሀሌ)፣ አርሣ(አልጋ)፣ መቀመጫ (ጽጎ) የተለፋ የቆዳ ምንጣፍ /ሽሬ/ ከተለያዩ ከአካባቢው ከሚያገኝዋቸው ቁሳቁሶች በመሥራት ይገለገሉባቸዋል።

ባህላዊ አመጋገብ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዛይሴዎች ባህላዊ ምግባቸውን ከተለያዩ የእህል ዓይነቶችና ከእንሰት ተዋፅኦ በማዘጋጀት ይመገባሉ። ወተት ቅቤና ማርን ለማባያነት ይጠቀማሉ። ባህላዊ መጠጣቸው ቦርዴ/መዶ/ ሲሆን የሚዘጋጀውም በቆሎ፣ማሽላ፣ጎመንና ቆጮን በመደባለቅ እና በመቀላቀል ደልዋዴ የተባለ እርሾ በማዘጋጀት ነው። ከዚያም ከተለያዩ የእህል ዓይነቶች ሰጋለ የሚባል ደፍድፍ ተዘጋጅቶ ከእርሾው ጋር በማዋሃድ በውሃ እየተበጠበጠ ይጠጣል። ከባህላዊ ምግባቸው ቂጣ/ቦራ/ ፣ሱልአ (ከጎመንና ከበቆሎ ዱቄት በመደባላቅ የሚሠራ) ቆዴ -(ከገብስ፣ከበቆሎና ከቡላ ዱቄት የሚሠራ) ገንፎ እና ባምኤ (-ከቦቆሎና ማሽላ ዱቄት የሚሠራ ኩርኩርፋ) ዋንኞቹ ናቸው።

ባህላዊ አለባበስ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዘይሴዎች ከእድሜ እና ከፆታ አንፃር የተለያየ የአለባበስ ስርዓት አላቸው። ሕፃናት በእጅ የተሰፋ አቡጀዲ በአንገታቸው ይታሠርላቸዋል። በወጣትነት የዕድሜ ክልል የሚገኙት ደግሞ ሰፋ ያለ ቁምጣ ሱሪ ይታጠቃሉ። ሴቶች ከጥጥ ፈትል የተሠራ ቀሚስና ነጠላ ይለብሣሉ። በተጫማሪም ወፈር ያለ ነጠላ፤ ጋቢ ከወገባቸው በታች ሽንሽን እንዲኖረው አድርጐ በማሰር “ዳንጮ” በተባለ መቀነት ወገባቸው ላይ ሸብ አድርገው ይለብሳሉ። አዛዉንቶች ደግሞ ሰፋ ያለ ቁምጣ፣እጀ ጠባብ ሸሚዝና ኮት ለብሰው ከላይ ጋቢ ወይም ቡልኮ ይደርባሉ። ባህላዊ መሪዎች አለባበሣቸው ከአዛውንቶች ተመሣሣይ ሆኖ ለክብራቸው መለያነት ደበሎ የተባለውን ከአውሬ ቆዳ ተለፍቶና አምሮ የተሠራ መላባሻ ከላይ ይደርባሉ።በእጃቸው ደግሞ ጭራ ይይዛሉ።

የለቅሶና የሐዘን ሥርዓት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የዛይሴ ብሔረሰቡ የለቅሶና የሃዘን ሥርዓት እንደሟቹ የዕድሜ ክልል፣ እንዳላቸው የሀብት መጠንና የሥልጣን ደረጃ ይለያያል። ለህፃናት ሞት ብዙም አይለቀስም። ሃዘኑ መሪር የሚሆነው ወጣቶች ሲሞቱ ነው። ወጣት ሲሞት ቤተሰቦችና የቅርብ ዘመዶቹ በለጋ ዕድሜው መቀጨቱን በሥነ ቃል እየገለፁ በስለት ግንባርንና ፊታቸውን በመቧጨር እየዘለሉ በመውደቅና በመፈጥፈጥ እንዲሁም የሟችን ንብረት በማውደም ሃዘናቸውን ይገልፃሉ። በዕድሜ የገፋ ሰው ሲሞት ለቅሶው ቀልድና ጨዋታ በተቀላቀለበት መልኩ ይፈፀማል። ካቲው/መሪው/ ሲሞት ሕዝቡ ለለቅሶው ሥርዓት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርግ መልዕክት እንዲያስተላልፉ ለማጋዎች ይላካል። ለካቲዎች «ጋሬ» የሚባል ለየት ያለ የለቅሶና የሃዘን ሥርዓት ይደረግላቸዋል። በቅድሚያ በማጋዎች አማካይነት የካቲው ሞት በአዋጅ ለሕዝብ ይነገራል።የካቲውን የቀብር ሥርዓት የሚፈፅሙት "ኢናማካ" በሚል ስያሜ የሚታወቁ ጐሣዎች ናቸው።የግብዓተ መሬት ከተፈፀመ በኋላ ጉድጓዱ የሚሞላው በአፈር ሣይሆን በጥሬ እህል ነው። የካቲው ለቅሶና ሐዘን ከ15-30 ቀናትን ይወስዳል። በካቲው ሞት የተሰማቸውን መሪር ሃዘን ለመግለፅ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ቅንድባቸዉንና ፀጉራቸውን ይላጫሉ። አመድ፣ጥላሸትና ጭቃ ይቀባሉ። እርጉዝ ሴት ደግሞ በሆዷ ላይ ጭቃ ትቀባለች። ይህም በሆዷ የያዘችው ፅንስ ጭምር ሀዘኑን ለመሪው እንዲገልፅለት በሚል እምነት ነው። በዚህ የለቅሶ ስርዓት የብሔረሰቡ አባላት “ጋይሎ” በሚባል ሥነ ቃል ሟች በህይወት ዘመኑ የፈጸማቸውን ጀብዶችና ገድሎች እያነሱ በዜማ በማወደስ ሐዘናቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነው።