የስብስብ ብዛት

ከውክፔዲያ

የስብስብ ብዛት የምንለው የአንድ ስብስብ አባላትን ብዛት ነው። ለምሳሌ የስብስብ B ብዛት በሒሳብ ምልክት እንዲህ ይወከላል፡ | B |። ለምሳሌ፡ ስብስብ B የፈረንሳይ ባንዲራ ቀለሞች ስብስብ ቢሆን፣ የ B ብዛት ሲሰላ | B | = 3 ነው፣ ምክንያቱም የፈረንሳይ ባንዲራ ቀለሞች 3 ናቸውና።

ባዶ ስብስብ የምንለው ልዩ ስብስብ በውስጡ ምንም አባላት የሉትም ስለሆነም ብዛቱ ዜሮ ነው እንላለን። ምልክቱም ይሄ ነው፡ ∅ ወይም { } ። ለምሳሌ ጎናቸው አራት የሆኑ ሶስት ማዕዘኖች ስብስብ ዜሮ አባላት ስላሉት ባዶ ስብስብ ይባላል።

በተጻራሪ አንድ አንድ ስብስቦች አእላፍ ብዛት አሏቸው። ለምሳሌ የቁጥሮች ስብስብን ብንወሰድ አእላፍ አባላት አሉት። አንድ አንድ አእላፋት ከሌሎች አእላፋት የሚበልጡበት ሁኔታ ይገኛል። ለምሳሌ የውኑ ቁጥር ብዛት ከመቁጠሪያ ቁጥር ብዛት ይበልጣል፣ ምንም እንኳ ሁለቱም ብዛታቸው አእላፍ ቢሆንም። በተጻራሪ አንድ አንድ እኩል የማይመስሉ አዕላፎች እኩል ሆነው ይገኛሉ። ለምሳሌ የመስመር ቁራጭ ና የተቆረጠበት መስመር እኩል ብዛት አላቸው፣ ማለት እኩል የነጥብ ብዛት አላቸው። እኒህንና እኒህ የመሰሉ እንግዳ የአእላፍ ጠባዮች የተጠኑት በጆርጅ ካንተር ነበር።

ርቢ ስብስቦች(ፓወር ሴት)[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የስብስብ S ርቢ ስብስብ የምንለው ማናቸውንም የስብስብ S ታህታይ ስብስቦች አቅፎ የሚይዝን ስብስብ ነው። ማለት ከ S አባላት የሚሰሩ ማናቸውንም ስብስቦችና ባዶ ስብስብን ይይዛል። አንድ ብዛቱ አእላፍ ያልሆነ (አባላቱ የሚያልቁ) ስብስብ ብዛቱ n ቢሆነ የርቢ ስብስቡ ብዛት 2n ነው። የርቢ ስብስብ እንዲህ ይወከላል P(S).

ለምሳሌ፡

{1, 2, 3} ስብስብ ቢሰጠን፣ ርቢ ስብስቡ ይሄ ነው {{1, 2, 3}, {1, 2}, {1, 3}, {2, 3}, {1}, {2}, {3}, ∅}. የመጀመሪያው ስብስብ ብዛት 3 ሲሆን የርቢ ስብስቡ ብዛት 23 = 8 ነው።