የአሾካ አዋጆች
Appearance
የአሾካ አዋጆች በሕንድ ንጉሥ አሾካ (277-240 ዓክልበ. የገዛ) በ264 ዓክልበ. የተሰጡት ሕግጋት ናቸው። እነዚህ ሕግጋቱ በድንጋይ ላይ ተቀረጹና በግዛቱ በየቦታው በዐምዶችና በሐውልቶች ተደረጉ፤ ስለዚህ ለሥነ ቅርስ በደንብ ታውቀዋል። የሕገ መንግሥት ታሪክ ውስጥ ናቸው።
ሕግጋቱ እንደ ቡዲስም ሃይማኖቱ መርኆች የተመሠረቱ ናቸው።
- ፩፤ የእንስሳዎች መስዋዕት ይከለክላል። በተጨማሪ «...ቀድሞም በንጉሡ ወጥ ቤት አዕላፍ እንስሳት ወጥ ለመሥራት ይገደሉ ነበር። አሁን ግን በዚህ አዋጅ ጽሑፍ፣ ሦስት እንስሶች ብቻ፣ ፪ ጣዎስና ፩ አጋዘን፣ ይገደላሉ፣ አጋዘንም ሁልጊዜም አይሆንም። በጊዜም ላይ፣ እነኚህ ስንኳ አይገደሉም።»
- ፪፣ ሁለት አይነት ሕክምና ይለያል፤ የሰዎች ሕክምናና የእንስሶች ሕክምና ሲኖሩ ለነዚህ ጥቅም ንጉሡ በየቦታውና በየጎረቤት አገሩ ዕጽዋትን አስገብቶ አስተክሏል፤ በየመንገዱም ዳር የውሃ ጉድጓድና ዛፍ አስተክሏል።
- ፫፣ በየ፭ቱ ዓመት፣ አስተማሪዎች በግዛቱ በኩል ተጉዘው ቡዲስምን ያስተምራሉ። «እናትንና አባትን ማክበር መልካም ነው፣ ልግሥና ለባልንጀራ፣ ለዘመድ፣ ለቄስ፣ ለባሕታዊ መልካም ነው፤ ሕያው ነገርን አለመግደል መልካም ነው፤ በመክፈልና በመቆጠብ መካከል ጥንቃቄ መልካም ነው።»
- ፬፣ እነዚህ መርኆች (እናትን አባትን ማክበር፣ ልግሥና ለባልንጀራ፣ ዘመድ፣ ቄስና ባሕታዊ፤ ሕያው ነገርን አለመግደል) ከሁሉ በላይ ስለ ሆኑ፣ መልካም ተዓምራት ወደ አገሩ እንዲመልሱ፣ የንጉሥ ተከታዮች ለወደፊቱ ምንጊዜም ያስተምራቸዋል።
- ፭፤ ለሕዝቡ ደህንነት የቡዲስም ወኪሎች ለየክፍላገሩ ይሾማሉ።
- ፮፣ ቀድሞ የመንግሥት ጉዳይ ወይም መረጃ ለንጉሡ በተወሰነ ሰዓት ይቀርብ ነበር። አሁን ግን ንጉሡ መረጃ በማናቸውም ሰአት ወይም ቦታ ይቀበላል፤ በኋላም በጉባኤ ለቃሉ ክርክር ቢነሣ ወዲያውኑ ይነገር።
- ፯፣ ሃይማኖቶች ሁሉ የልቡና ንጽሕናን ስለሚፈልጉ፣ ሁላቸው ይፈቀዳሉ።
- ፰፣ ቀድሞ ንጉሦች ለደስታቸው በእንስሳ ማደን ጉዞዎች ይሄዱ ነበር። ከአሾካ ጀምሮ ግን የአገር ቤት ሰዎችን ይጎብኙ፣ የወርቅ ስጦታ ለሽማግለዎች፣ ስጦታ ለባሕታውያን ይስጡ፣ የቢዲስምንም መርኆች ያስተምሩ።
- ፱፤ አሕዛብ በሕማም፣ በጋብቻ፣ በልደት፣ በጉዞና በሌላ ምክንያት የሚያደርጉት ሥነ ስርዓቶች ሁሉ ከንቱ ቢሆኑም ይፈቀዳሉ። ነገር ግን ዋጋ ያለው የቡዲስም ሥነ ስርዓት ለአገልጋይና ለሠራተኛ ትግዕስት፣ ለአስተማሪ ክብር፣ ለሕያው ነገሮች ጥንቃቄ፣ ለባሕታዊ ልግሥና ማሳየት ይገባል።
- ፲፤ ንጉሥ አሾካ ክብር የሚፈልገው ብቻ በቡዲስም መርኆች መሠረት ሕዝቦቹ በሚከተለው ዓለም ደህና እንዲሆኑ ስለሚመራቸው ነው።
- ፲፩፤ ስለ ቡዲስም መርሆች - እነርሱም ትግዕስት ለአገልጋይ፤ ክብር ለወላጅ፤ ልግሥና ለባልንጀራ፣ ዘመድ፣ ቄስ ወይም ባሕታዊ፤ ሕያው ነገርን አለመግደል - እያንዳንዱ ሰው ለአባቱ፣ ለልጁ፣ ለወንድሙ፣ ለጌታው፣ ለባልንጀራው፣ ለጎረቤቱ «ይሁን፣ ይደረግ» ይበሉ።
- ፲፪፣ ሃይማኖቶች ሁሉ ስለሚፈቀዱ ማንም ሰው የሌላውን ሃይማኖት ወይም ትምህርት መታገሥና ማስተዋል ይገባዋል።
- ፲፫፣ ከነዚህ አዋጆች አስቀድሞ፣ ንጉሡ ግዛቱን ለማስፋፋት የካሊንጋ ብሔር በጭካኔ ወርሮ ቢሆንም፣ አሁን ትልቅ መጸጸት አለበትና ምንጊዜም ከተቻለ ይቅር በማለት ያምናል። ስለዚህ አሁን የቡዲስም መርሆችን ማስፋፋት ይመርጣልና ከአሁን ወዲያ ተከታዮቹም እንደዚያ ይምረጡ።
- ፲፬፣ እነዚህ አዋጆች በየክፍላገሩም በየቦታው ተቀርጸው ይጻፉ።
ከነዚህም በላይ አያሌ የአሾካ ጥቃቅን ደንቦች ይታወቃሉ።