Jump to content

5ኛው አብጋር

ከውክፔዲያ
ንጉሥ አብጋር 'ያለ እጅ የተሠራ' የክርስቶስን ስዕል ሲይዙ፤ 10ኛው ክፍለ ዘመን ተሠራ፣ በደብረ ሲና ገዳም

5ኛው አብጋር ወይም 5ኛው አብጋሮስ ዘኤደሣ (42 ዓ.ም. የሞቱ) ከ12 ዓክልበ. እስከ 1 ዓክልበ. (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) እና እንደገና ከ5 ዓ.ም. እስከ 42 ዓ.ም. በኦስሮኤና ግዛት (በዛሬው ሶርያ) ላይ የነገሡ ንጉሥ ነበሩ። ዋና ከተማቸው ኤደሣ ነበረ። በታሪካዊ ሰነዶች ደግሞ «አብጋር ኡካማ» (አረማይክ፣ «አብጋር ጥቁሩ») ይባላል።

በአንድ ጥንታዊ ትውፊት መሠረት፣ እሳቸው መጀመርያው ክርስቲያን የሆኑ ንጉሥ ነበሩ። ከኢየሱስ 72 ደቀ መዛሙርት አንዱ ታዴዎስ (ወይም ዓዳይ) እንዳጠመቋቸው ያባላል።

የቤተ ክርስቲያን ጳጳስና የታሪክ ጸሐፊ አውሳብዮስ317 ዓ.ም. ገዳማ በጻፉት ታሪክ ዘንድ፣ ኢየሱስ በሕይወቱ ስብከት ሳለ፣ የጎረቤት አገር ንጉሥ አብጋር ከበሽታ ታምመውና ስለ ኢየሱስ ተአምራዊ ዝና ሰምተው፣ ኢየሱስ መጥቶ እንዲፈውሳቸው አንድን መልእክተኛ (ሐናን) ወደ ኢየሩሳሌም ልከው ነበር። በዚሁ ደብዳቤ ንጉሡ በኢየሱስ መለኰታዊነት አምነው ረድኤቱን ይለምኑና በቤተ መንግሥታቸው መጠጊያ እንዲያገኝ ይጠይቁታል። ኢየሱስ ወደ ኤደሣ ለመሔድ ጊዜ ስላልነበረው፣ መልሱን በሐናን እጅ ወደ ንጉሡ ላከ። በመልሱም እየሱስ ከዐረገ በኋላ አንድ ሃዋርያ እንዲልክላቸው የሚል ቃል ሰጣቸው።

አውሳብዮስ ሁለቱን መልእክቶች በኤደሣ ሰነዶች ቤተ መዛግብት አንዳገኙ ብለዋልና በጽሕፈታቸው ውስጥ አሳተማቸው። የደብዳቤዎች ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦

የንጉሥ አብጋሮስ መልዕክት ወደ ኢየሱስ
በእግረኛው በአናንዮስ (ሐናን) እጅ ወደ ኢየሩሳሌም ተላከለት።
«የኤደሣ ንጉሥ አብጋሮስ «ኡካማ»፣ በኢየሩሳሌም አገር ወደሚታየው በጎ ወደ ሆነው መድኅኔ ወደ ኢየሱስ፦ ሰላምታ፤
ስለ አንተ፣ ያለ ዕጽ ወይም ያለ መድኅኒት ስለሚደረገው ስለ ማዳንህ ሰምቻለሁ። በቃልህ ዕውሮች እንዲያዩ፣ አንካሶችም እንዲሄዱ፣ ለምጻሞችም እንዲነጹ፣ ደንቆሮችም እንዲሰሙ እንደምታደርግ፣ በቃልህም ርኩሳን መናፍስትንና አጋንንትን እንደምታስወጣ፣ የታመሙትን እንደምትፈውስ፣ እንዲሁም ሙታንን እንደምታስነሣ ይባላልና።
ይህን ሁሉ በሰማሁ ጊዜ ከሁለት ነገሮች አንድም ተረዳሁት፣ ወይም አንተ ከሰማይ ወርደህ እግዚአብሔር ነህ፣ ወይንም የእግዚአብሔር ልጅ ነህ።
ስለዚህ ነገር ጻፍኩልህ፣ ወዲህ እንድትመጣ ያለብኝንም በሽታ እንድትፈውስ በቅንነት እጠይቅህማለሁ።
አይሁዶችም በአንተ ላይ እንደሚነበነቡ በአንተም ላይ ተንኮል እንደሚያስቡ ተረዳሁ። የኔ ከተማ ትንሽ ብትሆንም፣ መልካም ናትና ለሁለታችን በሰላም ለመኖር ትበቃለች።»
የኢየሱስ መልስ ወደ ንጉሥ አብጋሮስ
በእግረኛው በአናንዮስ እጅ ተያዘ።
«አብጋሮስ ሆይ፣ ብጹዕ ነዎት፣ እርስዎ ያላዩኝን እኔን አምነዋልና። ስለ እኔ፤- ያዩኝ እንደማያምኑ፣ ያላዩኝም አምነው በሕይወት እንደሚኖሩ ተጽፏልና።
እኔ ወደርስዎ ጉብኝት እንዳደርግ ስለ ጻፉት መልእክትዎስ፣ ስለ እርሱ የተላኩትን ሁሉ በዚህ ምድር መፈጽም ይኖርብኛል፤ ከዚያም እንደገና ወደ ላከኝ አብ ላርግ ነው። ከዕርገቴም በኋላ ከደቀ መዛሙርቴ አንዱን ልኬ እርሱ በሽታዎን ፈውሶ ጤና እና ሕይወት ለእርስዎ ከእርስዎም ጋር ላሉት ሁሉ ይሠጣል።»

በአውሳብዮስ ታሪክ ከዚህ ትንሽ በኋላ በ21 ዓ.ም. ሀዋርያው ቶማስ ታዴዎስን («ዓዳይ» የተባለውን) ወደ ንጉሡ እንዲያጠምቋቸው ላከው። በአውሳብዮስ ዘመን የኖሩ ኤፍሬም ሶርያዊ ደግሞ ስለዚሁ ታሪክ ጽፈዋል።

በ350 ዓ.ም. ገዳማ ትምህርተ ዓዳይጽርዕ (የሶርያ ቋንቋ) ታተመ። ይህ መጽሐፍ ተጨማሪ መረጃ አቀረበ፦ የእየሱስ ደብዳቤ ከመያዙ በላይ ይህ ሐናን የኢየሱስን ስዕል እንደ ሠራ ይህም ስዕል እስከዚያው ቀን ድረስ ቆይቶ በኤደሣ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተጠበቀ አወራው። በዚሁ መጽሐፍ ዘንድ የሆነበት አመት 24 ዓ.ም. ነበረ። የአርመን ታሪክ ጸሐፊ ሙሴ ቆረናጺ (450 ዓ.ም. ያህል) እንዲህም አይነት ታሪክ ይናገራሉ።

በ487 ዓ.ም. ግን የሮማ ፓፓ 1ኛ ገላስዮስ በጉባኤ ደብዳቤዎቹን 'የማይቀበሉ ጽሑፎች' አሏቸው። ሆኖም በሶርያ ቤተ ክርስቲያን እስካሁን በጣም የሚከብሩ ናቸው።

በ550 ዓ.ም. ያህል የኤደሣ ጳጳስ ኤዋግርዮስ እንደ ገለጹት ደግሞ ይህ የኢየሱስ ስዕል እንዲያውም በሐናን የተፈጠረው ሳይሆን፣ ኢየሱስ እራሱ መልኩን በተአምር በጨርቅ ላይ ያሳተመው እንጂ 'ያለ እጅ የተሠራ' ተብሏል። ይህ ቅዱስ ስዕል አሁን ያለበት ቦታ በእርግጥ ባይታወቅም፣ በአውሮፓ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ አንዳንድ ስዕል ለምሳሌ የጄኖቫ ቅዱስ መልክ ኦሪጂናል ቅጂ እንደሆነ የሚያምኑ አሉ።

ይህን ታሪክ ወይም ትውፊት የማይቀበሉት ሊቃውንት ግን፤ በኦስሮኤና ኋለኛው ክርስቲያን ንጉሥ በ9ኛው አብጋር ዘመን (200 ዓ.ም. ያህል) በማቃወስ እንደ ተፈጠረ ያስባሉ።

ምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አብጋር ቅዱስ ሆነው ይቆጠራሉ። የግብራቸው ማስታወሻ ዕለታት May 11 እና October 28 ናቸው። በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ቀኑ August 1 ነው። እንዲሁም በአርሜናዊ ሃዋርያዊ ቤተ ክርስቲያን በሁልቀን ቅዳሴ ይከብራሉ።

ዋቢ መጻሕፍት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
  • Walter Bauer, Orthodoxy and Heresy in Earliest Christianity, 1934, (in English 1971): On-line text Archived ኦገስት 18, 2000 at the Wayback Machine
  • Robert Eisenman, James the Brother of Jesus 1997 (Viking Penguin), especially ch. 24, pp 189ff.
  • Ian Wilson, Holy Faces, Secret Places 1991
  • Holweck, F. G., A Biographical Dictionary of the Saints. St. Louis, MO: B. Herder Book Co., 1924.

የውጭ መያያዣዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]