አሙን
አሙን (ደግሞ አመን፣ አሞን፣ ሃሞን) በጥንታዊ ግብጽ አረመኔ እምነት ዘንድ ከነበሩት ዋና አማልክት (ጣኦታት) አንዱ ነበር። ከዚህ በላይ በጥንታዊ ሊቢያ፣ ኩሽ እና ግሪክ አገሮች አረመኔ እምነቶች ከፍተኛ ሚና ያጫወት ነበር።
በግብጻውያን ሃይማኖት፣ አሙን ያልተወለደ ያልተፈጠረ ፈጣሪ መሆኑ ይታመን ነበር። ከ1550 ዓክልበ. የገዙት ፈርዖኖች በተለይ ያከብሩት ነበር። በጊዜ ላይ፣ የአሙን እና የፀሐይ ጣኦት ራ መታወቂያዎች አንድ ሆነው ስያሜው «አሙን-ራ» (ወይም «አሙን-ሬ») ይባል ጀመር። በ1360 ዓክልበ. ያህል ግን ፈርዖኑ 4 አመንሆተፕ የራሱን ስም ወደ «አከናተን» ቀይሮ የአሙን አምልኮት ከለከለው፤ በፈንታውም የአተን እምነት እንዳቆመ ይታወቃል። አከናተን በ1345 ዓክልበ. ግድም በሞተበት ወቅት፣ የአሙን-ራ ቄሳውንት ተነሥተው ሃይማኖታቸውን መለሡ፤ ስለዚህ የአከናተንም ልጅና ተከታይ ቱታንካተን ስሙን ወደ ቱታንካመን ሊቀይር ተገደደ።
በኩሽ መንግሥት፣ በኖባ እና በመርዌ አሙን «አማኔ» ተብሎ በተለይ ይወደድ ነበር። የአማኔ ቄሳውንት መንግሥትን በሙሉ ይቆጣጥሩ ነበር፤ ነገሥታትን መረጡ፣ ጦርነትንም አዋጁ። ዲዮዶሮስ ሲኩሉስ እንደሚለን እንኳን የአማኔ ቄሳውንት ንጉሥ ራሱን እንዲገድል ሊያዝዙ ይችሉ ነበር።
በሊቢያ የአሙን መቅደስ በበረሃ ውስጥ በሲዋ ኩሬ ይገኝ ነበር። ግሪኮቹም «ዚውስ ሃሞን» ሲሉት ወደ ሊቢያ ተጒዘው በየጊዜ ያማክሩት ነበር። የአሞን መቅደሶች ደግሞ በግሪክ አገር ሠሩ። ዲዮዶሮስ የሊቢያ አፈ ታሪክ ሲተርክልን፣ ሃሞን በአፍሪካ (በኒሳ ደሴት በትሪቶን ወንዝ) የገዛ ንጉሥ ነበረ፤ ሚስቱም ሬያ ነበረች። የሬያ ወንድም ክሮኖስ ግን ከቲታኖች ጋራ ወርሮ ሊቢያንም ሬያንም ከሃሞን እጅ ያዘ። ከዚህ በኋላ የሃሞን ልጅ ባኩስ ወይም ዲዮኒሶስ ክሮኖስን አሸነፈው፤ የክሮኖስና የሬያንም ልጅ ዩፒተር ኦሊምፑስን ማርኮ እርሱን የግብጽ አገረ ገዥ አደረገው።
ጣልያናዊ መኖኩሴ አኒዩስ ዴ ቪቴርቦ ባሳተመው ዜና መዋዕል ዘንድ (1490 ዓ.ም. የታተመ)፣ ሃሞን የሊቢያ ንጉሥ የትሪቶን ልጅና ተከታይ ነበረ። የካሜሴኑስ (ካም) እኅት ሬያን አገባ። ሬያም በሥውር የሃሞንን ዲቃላ ሕጻን ልጅ ዲዮኒስዮስን ከቁባቱ ከአልማንጤያ ወስዳ ወደ ኒሳ በአረቢያ እንዲታደግ ላከችው። ስለዚህ ነገር ሃሞንና ሬያ ለረጅም ጊዜ ብዙ ተጣሉ። በመጨረሻ ሬያ ወደ ወንድምዋ ወደ ካሜሴኑስ በሲኪልያ ሸሽታ እርሱ አገባትና ከቲታኖቹ ጋራ ሊቢያን ወረሩ፤ ሃሞንንም ወደ ክሬታ ደሴት አባረረው። ካሜሴኑስና እህቱ ሬያም ልጃቸውን ዩፒተር ኦሲሪስን ወለዱ። በኋላ ግን የሃሞን ልጅ ዲዮኒስዮስ ከኒሳ ተመልሶ ካሜሴኑስን አሸነፈው። ዲዮኒስዮስም የካሜሴኑስና የሬያን ልጅ ዩፒተር ኦሲሪስን ማርኮ የግብጽ ንጉሥ እንዲሆን አደረገው። በዚህ ዜና መዋዕል አቆጣጠር ሃሞን በሊብያ የነገሠ ምናልባት ከ2315 እስከ 2287 ዓክልበ. ግድም ነበር።
አለቃ ታዬ በ1906 ዓ.ም ከጻፉት የኢትዮጵያ የሕዝብ ታሪክ፣ ኅሩይ ወልደሥላሴ በ1913 ዓ.ም. ከጻፉት ዋዜማ፣ እና በ1919 ዓ.ም. ራስ ተፈሪ (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለቻርልስ ረይ ባቀረቡት የኢትዮጵያ ነገሥታት ዝርዝር ዘንድ፣ ከኩሽ መንግሥት መጀመርያ ነገሥታት አንዱ አመን የሚባል አለ።