ጥንታዊ ግብፅ
ጥንታውያን የግብጽ ባለሥልጣኖች [ለማስተካከል]
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ከማየ አይኅ ቀጥሎ መጀመሪያ የአፍሪካ ሕዝብ የኖኅ ልጅ የካም ዘሮች ናቸው፤ ይህ አገር ሰናዖር ለሚሉት ቅርብ ስለ ነበር የባብል ግንብ ከተሠራ በኋላ ከዚህ ተነስተው ወደ ግብፅ ወረዱ።
የግብጽ ቀድሞ ዘመን መንግሥት ዋና ጥንታዊ ነው፤ የመሠረተውም ፈርዖን ሜኒስ የተባለው ነው። ጸሓፊው ጊዮርጊስ ስንቄሎስ (፰፻ ዓ.ም. አካባቢ የጻፈው) ይህ ፈርዖን ሜኒስ በዕውነት የካም ልጅ ምጽራይም እንደ ነበረ ገመተ።
ዳሩ ግን አባ አውሳብዮስ በጻፉት ዜና መዋዕል ዘንድ (፫፻፲፯ ዓ.ም. ተጽፎ)፣ የድሮ ግብጻዊው ባለታሪክ ማኔጦን (፫ኛው ክፍለ ዘመን ዓክልበ.) ስለ ኋለኞቹ ግብጻውያን ሲጽፍ፣ ይኮሩበት የነበረው የታላቁ ጥንት ዘመን ከማየ አይህ አስቀድሞ እንዳለፈ፣ በኋላም በዚያው አገር ዳግመኛ ከሠፈረበት ከካም ልጅ ምጽራይም በውኑ እንደ ተወለዱ ጽፎ ነበር። ተመሳሳይ ታሪክ በእስላም ጸሐፊዎች በግብጻዊው እብን አብድ ኤል-ሀከም እና በፋርሳውያን አል-ታባሪና ሙሐመድ ቈንዳሚር መጻሕፍት ሲገኝ፣ ፒራሚዶች፣ እስፊንክስ ወዘተ. ሁሉ የተሠሩ ከጥፋት ውኃ በፊት በኖሩት ክፉ ዘሮች ሆኖ፣ ከዚያ በኋላ ግን አገሩ ለካም ተወላጅ ለምጽራይም ('ማሣር' ወይም 'መሥር') ተሠጠ ብለው ጻፉ።
በግሪኩ ጸሐፊ ሄሮዶቶስ ዘንድ፣ የግብፅ ቀድሞ ዘመን የመጀመሪያው ፈርዖን ሜኒስ ነጭ አባይን ከመነሻው ወደ ጎን መለሰና ውሃው ይፈስበት በነበረው ላይ ሜምፊስ የተባለውን ከተማ ቆረቆረ። ታላቅ ንጉሥም ስለ ነበረ ከሞተ በኋላ ሕዝቡ እንደ አምላክ አድርገው አመለኩት። በዘመናዊ አስተሳስብ፣ ይህ ላይኛ ግብጽና ታችኛ ግብጽ ያዋሐደው መጀመርያው ፈርዖን መታወቂያ ለሥነ ቅርስ ከሚታወቀው ፈርዖን «ናርመር» ከተባለው ጋር አንድ ነው።
ናርመር (ሜኒስ) አገሩን ካዋሐደ አስቀድሞ ሌሎችም ነገሥታት (ለምሳሌ ንጉሥ ጊንጥ) በአገሩ ክፍሎች ብቻ ላይ እንደ ነገሡ ከተገኙት ቅርሶች (የመንደሮቹ መኳያ ሰሌዳ እንደሚያሳይ) ይታወቃል።
የሃይሮግሊፍ ቅርሶችና መዝገቦች ለማንበብ ችሎታው አሁን ስላለ፣ ሜኒስ ከነገሠ በኋላ የግብፅ ታሪክ በጥቂት መጠን ተገልጾአል። መጀመርያው ሥርወ መንግሥታት (፩ኛው እስከ ፮ኛው ድረስ) የቀድሞ ዘመን መንግሥት ይባላሉ። በ፩ኛው ሥርወ መንግሥት ሰባአዊ መስዋዕት በሰፊ ይደረግ ነበርና ከፈርዖኖቹ ጋራ ብዙ ሎሌዎች አብረው ይቀበሩ ነበር። የሔሩ ወገን በሴት ወገን ላይ ይበረታ ነበር። በ፪ኛው ሥርወ መንግሥት የፈርዖኖች መቃብር ከተማ ከላይኛ ግብጽ ወደ ታችኛ ግብጽ (ስሜኑ) ተዛወረ። በኋለኛ 2ኛው ሥርወ መንግሥት ዘመን የሴት ወገን ወኪል ፈርዖን ፐሪብሰን ተነሣና ያንጊዜ ትግሎች እንደ በዙ ይመስላል። በ፫ኛው ሥርወ መንግሥት መጀመርያ የሔሩ ወገን ለሥልጣን ተመልሶ፣ ነጨሪኸት የተባለው ፈርዖን የመጀመርያውን ሀረም (ፒራሚድ) አሠራ። ከርሱም በኋላ የተነሡት ታላላቅ ፈርዖኖች በጊዛ ሜዳ ላይ ፒራሚዶቻቸውን እንዲሁም የጊዛ ታላቅ እስፊንክስን ሠሩ። በ፬ኛውም ሥርወ መንግሥት የፈርዖኖች ዝሙት የገዛ እኅቶቻቸውን እስከሚያግቡ ድረስ ደረሰ። በ፭ኛው ሥርወ መንግሥት መጨረሻ ፈርዖኖች በሀረሞቻቸው ውስጥ የሀረም ጽሕፈቶች ያስቀረጹ ጀመር፤ እነኚህ ጽሕፈቶች የሔሩ ተከታዮች ወገን (ወይም «ደቂቃ ሔሩ») በሴት ተከታዮች ወገን ላይ የፈጸሙትን ጨካኝ የጭራቅነት ሥነ ስርዓት ይመሰክራሉ። ይህም አስጨናቂ ሁኔታ በ፮ኛው ሥርወ መንግሥት እየተቀጠለ ፈርዖኖቹ ዓለማቸውን ሁሉ ከነጎረቤቶቻቸውም ጋር በጽናት ይገዙ ነበር።
፮ኛው ሥርወ መንግሥት ከነገሠ በኋላ የግብፅ ታሪክ እጅግ ግልጽ ሆኖ አይታይም። በታሪክ ጸሐፍት እንደ ማኔጦን ዝርዝሮች በኩል፣ ለ፯ኛው-፰ኛው ሥርወ መንግሥታት በርካታ ስሞች ቢመዘገቡም፣ ከጥቂቶቹ ብቻ በስተቀር አንዳችም ሥነ ቅርሳዊ ማስረጃ ከቶ ስላልተገኘላቸው፣ ስሞች ብቻ ቀርተው በእውነት እንደ ኖሩ ወይም ዝም ብለው በማስመስል እንደ ተፈጠሩ አይታወቀም። ከቀድሞውም ዘመን በኋላ በእርግጥኛነት የነገሡት መጀመርያ ፈርዖኖች የግብጽ መካከለኛውን ዘመን መንግሥት የመሠረቱት በስማቸውም ውስጥ «ታ-ዊ» (ሁለቱ አገራት ወይም በዕብራይስጥ ምስራይም) የተባሉት ናቸው።