Jump to content

ፍትሐ ነገሥት

ከውክፔዲያ

ፍትሐ ነገሥት1140 አካባቢ በግብጽ አገር ቅብጡ አቡል ፋዳዒል እብን አል-አሣልአረብኛ የጻፉት ሕገ መንግሥት ነው። እብን አል-አሣል ሕጎቹን የወሰዱት በከፊል ከሃዋርያት ጽህፈቶችና በከፊል ደግሞ ከድሮ ቢዛንታይን ነገስታት ሕጎች ነበር።

አንደኛው ክፍል ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ሲሆን የቤተክርስቲያን ስነሥርዐትና ምስጢራትን ይገልጻል። የተለቀሙት መጻሕፍት መጽሐፍ ቅዱስ የአበው ለምሳሌ የአቡሊድስና የባስሌዮስ ጽሕፈቶችና በኒቂያ ጉባኤ ወይም አንጥያኮስ ጉባኤ የተወሰኑ ሥርዓቶች ናቸው።

ሁለተኛው ክፍል ተራ ምዕመናንን (ካህን ያልሆኑ) የሚነካ ጉዳይ ያስረዳል፣ ይህም ማለት የቤተሠብ፣ የእዳና የብሔራዊ አስተዳደር የመሳሰሉትን ሕገጋት ያጠቃልላል። ይህ ክፍል ደግሞ እላይ ከተጠቀሱት ምንጮች ቢለቀምም ሌሎቹ በብዛት የተጠቀሙት መጻሕፍት «4 የነገስታት ቀኖና» የተባሉት ናቸው። አንዳንድ ሊቃውንት እነዚህን መጻሕፍት በአርእስት አሳውቀዋል:-

  1. «ፕሮቀይሮስ ኖሞስ» - በ866 ዓ.ም. አካባቢ በባይዛንታይን ንጉሥ ባሲሌዮስ መቄዶናዊ የተዋጀ ሕግ መጽሐፍ
  2. 472 ዓ.ም. ያሕል በግሪክ የተጻፈ «የሶርያ-ሮማውያን ሕግ መጽሐፍ» (አረብኛ ትርጉም)
  3. «ኤክሎጋ» - በ718 ዓ.ም. በባይዛንታይን ንጉሥ ሌዮ ኢሳውራዊ እና በልጁ የተዋጀ ሌላ ሕግ መጽሐፍ (አረብኛ ትርጉም)
  4. «የብሉይ ኪዳን ደንቦች» - ስሙ ባልታወቀ ክሪስቲያን የተጻፈ የሕገ ኦሪት መግለጫና ትርጓሜ
ናቸው።

ከነዚህ መሃል ሦስቱ ምንጮች የባይዛንስ ንጉስ የዩስጢኒያኖስ ሕገ መንግሥት ጽኑ ተጽኖ ስላላቸው የእብን-አሣል ሥራ በተለይ እንደ ሮማ ሕጎች ይመስላል። መጀመርያ «የቀኖና ክምችት» ተባሎ ዛሬ የአረብኛ እትም «የእብን አል-አሣል ቀኖና» ይባላል። ሲጽፉት ለቅብጦች ጥቅም እንዲህን አስበው እነሱም ትልቅ ሥልጣን እንዳለው ሰነድ አከበሩት።

መጽሐፉ በግዕዝ ተተርጉሞ ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ወቅት በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በ1450 ዓ.ም. አከባቢ እንደነበር የሚል ታሪካዊ መዝገብ አለ። ቢሆንም መጀመርያ እንደ ሕገ ምንግሥት መጠቀሙን የተመዘገበው በዓፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን (ከ1555 ዓ.ም. ጀምሮ) ነው።

የግእዝ ትርጉም በጴጥሮስ አብዳ ሳዒድ ስም ተደርጎ ለአረብኛው ሁልጊዜ ትክክለኛ አልነበረም፣ በአንዳንድም ስፍራ ቋንቋው ለአስተርጓሚው ሲያስቸግራቸው በፍጹም የተለየ ንባብ ይሰጣል። መጀመርያው ክፍል (ቤተክርስቲያን የሚነካ) ከዚህ በፊት ሲኖዶስ ተብሎ በኢትዮጵያ እንደታወቀ ሊቃውንት ገልጸዋል። ሁለተኛው ክፍል ብቻ ለኢትዮጵያ አዲስ ስለሆነ ስሙ «ፍትሐ ነገስት» የተወሰደው ከዚሁ ክፍል ነበር ይላሉ።

ፍትሐ ነገስት እስከ 1923 ዓ.ም. የብሄሩን ዋና ሕግ ሆኖ ቆየ። ያንጊዜ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት በአጼ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የታወጀ ቢሆንም ቀድሞ በ1922 ዓ.ም. በፍትሐ ነገሥት መሠረት አዲስ የወንጀል ሕግ ተሰጠ። ደግሞ በ1914 ዓ.ም. ንጉሥ ሳይሆኑ እንደራሴ በሆኑበት ወቅት በፍትሐ ነገስት የተገኙት ጨካኝ ቅጣቶች ሁሉ (ለምሳሌ ለስርቆት እጅ መቆረጥ) ፈጽሞ እንዲተዉ አስደርገው ነበር።

  • 810) «... በጣዕሙ ፡ በመዓዛው ፡ በአለሳለሱ ፡ በሚያስት ፡ መልኩ ፡ እንዳይደሰቱ ፡ መሆን ፡ ይገባቸዋል። ሥጋ ፡ ለጥቂት ፡ ወራት ፡ ይቆም ፡ ዘንድ ፡ ለሚበቃ ፡ ያህል ፡ ይመገቡ ፡ እንጂ። ለብዙዎች ፡ ሰዎች ፡ በዘመናቸውና፡ በቦታቸው ፡ የተገኘውን ፡ ይመገቡ ፡ እንጂ። ጌታችንም ፡ እንዲህ ፡ ብሏል ። በዚህ ፡ ዓለም ፡ ለብዙ ፡ ሥራ ፡ መዘጋጀትና ፡ መጨነቅ ፡ ምንድን ፡ ነው? ለእርሱስ ፡ የሚያሻው ፡ ጥቂት ፡ ነው። ያውም ፡ አንድ ፡ ነው ፡ አለ። (ማቴ ፡ ፲፮ ፡ ፳፮። ሉቃ ፡ ፲ ፡ ፵፩ ፡ ፵፪።)»