Jump to content

ሓሊዞናውያን

ከውክፔዲያ

ሓሊዞናውያን (ግሪክ`Αλιζωνες) በግሪኩ ባለቅኔ ሆሜር ግጥም ኢልያድ የተገኘ መታወቂያው ግን ምስጢራዊ የሆነ ሕዝብ ነበር። በኢልያድ መሠረት በትሮያስ ጦርነት ጊዜ በትሮአስ ሠራዊት ውስጥ የዘመቱ ወገን ነበሩ። መሪዎቻቸውም ኦዲዮስኤፒስትሮፎስ ሲሆኑ እሊህ የመኪስቴዎስ ልጆች ተባሉ። ሆሜር እንደሚለው «ከብር ልደት አገር - ከሩቅ አሉቤ» ደርሰው ነበር።

በኋላ ዘመን የታሪክ ጸሐፊ ስትራቦን ጉዳዩን ለመፍታት ሲሞክር «ከሩቅ አሉቤ» በማለት ፈንታ «ከሩቅ ሓሉቤ» ሆሜር መጻፍ የፈለገ ይሆናል በማለት ግመቱን አቀረበ። ስለዚህ «ሓሊዞናውያን» የሓሉባውያን ስም እንደ ነበር መሰለው። በዚህ አጋጣሚ በሓሉባውያን አገር መካከል ሓሉስ (ሓሊስ) የተባለ ወንዝ ይፈሳል። ከስትራቦን ዘመን በፊት ከ1200ም ዓክልበ. በፊት ኅይለኛ መንግሥት የነበራቸው ኬጢያውያን ደግሞ በዚያው ወንዝ ዙሪያ የብር ማዕድን ሠርተው በዚያን ጊዜ የአገሩ ስም ሓቲ ተብሎ ነበር። ይህም በዛሬው ቱርክ አገር መሃል ይስፋፋ ነበር።

ሌሎች ግሪክ ጸሓፊዎች ግን (ፕሊኒ፣ ሄካታይዎስ ወዘተ.) ሓሊዞናውያን በትንሹ እስያ ውስጥ ለትሮአስ ቅርብ በሆነ ክፍል እንደ ኖሩ ይላሉ። ሄሮዶቶስም በእስኩቴስ መካከል (በዛሬው ዩክራይን) ስለሚኖሩ «ሓሊዞናውያን» ጽፏል።

ቅዱስ አቡሊዴስም በ226 ዓ.ም. በጻፉት ዜና መዋዕል ሓሊዞናውያን የሴም ልጅ ሉድ ተወላጆች እንደ ነበሩ አመለከቱ።