መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ጅሩ ቆላ ውስጥ እምባጮ መግደላዊት በሚባል ሥፍራ መጋቢት ፲፯ ቀን በ፲፰፻፺፩ ዓ/ም ተወለዱ።
በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ትምህርታቸውን እስከ ዳዊት ድረስ ካጠናቀቁ በኋላ የዜማ ትምህርት ተከታትለው ጾመ ድጓ እና ድጓን ዘልቀዋል። ቀጥሎም የቅኔ ትምህርታችውን አጠናቀው በ ፲፱፻፭ ዓ/ም በአሥራ አራት ዓመት ዕድሜያቸው በወንበር ፀሐፊነት የመጀመሪያ ሥራቸውን ጀመሩ።
የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ፤ የዮሐንስ አፈወርቅን ትርጓሜ፤ እንዲሁም የመቅድመ ወንጌልን ትርጓሜ ትምህርት ያጠናቀቁት እኝህ ታላቅ ሰው ብርሃንና ሰላም (ጋዜጣ) የተሰኘው ጋዜጣ ሲመሠረት የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ በመሆን፣ ቀጥለውም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የግዕዝና የአማርኛ አስተማሪ በመሆን አገልግለዋል። ከፋሺስት ወረራ በኋላ ከ፲፱፻፴፫ ዓ/ም እስከ ፲፱፻፷፫ ዓ/ም ድረስ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ሥነ ጽሑፍንና ታሪክን በተመለከተ፣ አሥራ ሦስት መጻሕፍትን የደረሱ ሲሆን፣ ሰባት መጻሕፍት ደግሞ ተርጉመው አቅርበዋል። እንዲሁም የተለያዩ ጽሑፎችን አሰባስበው ከማዘጋጀታቸው ባሻገር፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ሥራዎችም ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋር በትብብር አዘጋጅተዋል። ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ አንዱ የአማርኛ ቋንቋ አባት ተብለው ቢወደሱ ማጋነን አይሆንም። ይህም የተባለበት ምክንያት የአማርኛ ሰዋሰውን አስመልክቶ ባደረጉት ጥልቅ ምርምሮች እና በተቀናጀ መልክ የተዘጋጁ የአማርኛ ሰዋሰው መማርያ መጸሐፍትን በመጻፋቸው ነው። በተርጓሚነት፣ በአዘጋጓጅነት እና በደራሲነት ባገለገሉበት ጊዜ ከ፴፭ በላይ የሚሆኑ መጽሐፍትን ለህትመት እንዲበቁ አድርገዋል። በእዚህም መሰረት የአማርኛን ቋንቋ ከዘመናዊ እና ከኪነታዊ አነጋገር በማስማማት ላደረጉት የላቀ አገልግሎት ድርጅቱ በ፲፱፻፷፬ ዓ.ም. የአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ሽልማትን ሰጥቷቸዋል። ከእዚህም በተጨማሪ እንደ መምህር፣ ርዕሰ-መምህር ከማገልገላቸውም ባሻገር በብሪታንያ-ሶማሌላንድ እና በፈረንሳይ-ሶማሌንድ መካከል የተፈጠረውን የድንበር ግጭት ለመፍታት ለሦስት ዓመታት (ከ፲፱፻፳፬ እስከ ፲፱፻፳፯ ዓ/ም) ያገለገለው ኮሚሽን አባል እና ዋና ፀሐፊ በመሆን አገልግለዋል። የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ፤ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት እና አማካሪ በመሆንም ለሀገራቸው ሠርተዋል። ከለይ ከተጠቀሱትም ባሻገር የኢትዮጵያን ታሪክ በማጥናትና መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አማርኛ በመተርጎም ሥራ ላይ ያላሰለሰ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ለዛም ነው ብዙዎቹ ለሃቅና ለእውነት የቆሙ ዘርፈ-ብዙ ፈርቀዳጅ ምሁር የሚሏቸው።
- በ፲፱፻፴፭ ዓ/ም በወቅቱ የአማርኛ ሰዋስው ባለመኖሩ ተማሪዎች ተገቢውን የቋንቋ ትምህርት ለማግኘት ይቸገሩበት የነበረውን ሁኔታ እንዲቀረፍ የጎላ አስተዋጾዖ ያደረገው እና በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የታተመው “ያማርኛ ሰዋስው” የተሰኘው መጽሐፋቸው ነው። ይህ መጽሐፍ ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ጊዜ በ፲፱፻፵፪ እና በ፲፱፻፵፮ ዓ/ም ሎንዶን ላይ የታተመ ሲሆን አራተኛው ዕትም በ፲፱፻፵፰ ዓ/ም በአርስቲስቲክ ማተሚያ ቤት ታትሟል።
ከሌሎቹ ፦
- የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ። አዲስ አበባ ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ፣ ፲፱፻፶፩ ዓ/ም።
- የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣ 1999 ዓ.ም.
- ትዝታዬ ስለ ራሴ የማስታውሰው፣ አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት፣ አ/አ፣ 2002 ዓ.ም.
- የዘመናት ማገናዘቢያ፤ ኒው ዮርክ፣ 2004 ዓ.ም
- የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሶማሊላንድ የወሰን መካለል ታሪክ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣ 2007 ዓ.ም.
ይጠቀሳሉ።
- http://www.nale.gov.et/National%20Bibliography/BIBLIO.%20OF%20ETHIOPIAN%20WRITERS%2 Archived ጁላይ 20, 2011 at the Wayback Machine
- መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ድረ ገጽ
- በዘመናት ማገናዘቢያ መጽሐፍ የተመሠረተ የዘመናት ማገናዘቢያ ሶፍትዌር Archived ኤፕሪል 29, 2017 at the Wayback Machine
- በዘመናት ማገናዘቢያ መጽሐፍ የተመሠረተ በዓላትና አጽዋማት ማወቂያ ሶፍትዌር Archived ኦገስት 5, 2020 at the Wayback Machine