ማጅራት ገትር
ማጅራት ገትር በድንገት በመነሳትና የአንጎልንና የኀብለ-ሰርሰርን ሽፋን የሆነው ስስ አካል በመመረዝ የአእምሮ መታወክ ስሜት የሚያስከትል አደገኛ በሽታ ነው፡፡ ለዚህ በሽታ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ስያሜዎች ቢሰጠውም በስፋት የሚታወቁት ስያሜዎቹ ግን ማጅራት ቆልምም ፣ የጋንጃ በሽታና ሞኝ ባገኝ የሚባሉት ናቸው።
በሽታው በየትኛውም ክፍለዓለም የሚገኝ ሲሆን በአፍሪካም አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰትበት የመልክአ ምድር ክልል አለው። ይህም ክልል “የአፍሪካ ማጅራት ገትር መቀነት" በመባል የሚታወቅ ሲሆን የሚገኘውም ከሰሐራ ምድረበዳ በስተደቡብና ከምድር ወገብ በስተሰሜን ባለው ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያም በዚህ ክልል ውስጥ ትገኛለች። በአገራችን በሽታው አብዛኛውን ጊዜ የሚገኘው በጣም ሞቃታማና ደረቅ ያየር ጠባይ በሚታይበት ከጥር እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ሲሆን በማጅራት ገትር ወረርሽኝ የሚታወቁት ወራት ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት፣ ሚያዝያና ግንቦት ናቸው። ማጅራት ገትር ከ፰–፲፪ ዓመት በወረርሽኝ መልክ እየተቀሰቀሰ ጉዳት ማድረሱም ይታወቃል።
የበሽታው መንስዔዎች በዓይን ሊታዩ የማይችሉ ረቂቅ ተሕዋስያን ናቸው። በወረርሽኝ መልክ ለሚከሰተው ማጅራት ገትር መንስኤው በእንግሊዘኛው ቃል “ኔስሪየ ሜኒንጅቲዲስ" (Neisseria meningitides) ተብሎ የሚታወቀው ተሕዋስ ነው።
የበሽታው አምጪ ተሕዋስያን በሽታው ካለበት ወይንም ተሕዋስያኑ በሰውነት ውስጥ እያሉ የሕመም ምልክቶች ከማይታይበት ተሸካሚ ሰው አፍንጫና ጉሮሮ በትንፋሽ፣ በማስነጠስና በሚያስልበት ወቅት በመውጣት ከአየር ጋር ወደ ጤናማው ሰው አፍንጫና ጉሮሮ ይደርሳሉ።
ተሕዋስያኑም ከሁለት እስከ አሥር ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ የአፍንጫን የውስጥ ክፍልና ጉሮሮን በመውረር የጉንፋን ዓይነት ስሜት ያስከትላሉ። እርባታቸውና እድገታቸው ሲሟላ ወደ ደም ኡደት በመግባት በአካል ልዩ ልዩ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ። ተሕዋስያኑ አብዛኛውን ጊዜ የአንጎል ስስ ሽፋንን በከፍተኛ ደረጃ ያጠቃሉ። የአየሩ እርጠበት መጠን ዝቅተኛና ሞቃት በሚሆንበት ጊዜ በጠባብ ክፍሎች የሰዎች ተፋፍጐ መኖር፣ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ያለ ጥንቃቄ የቅርብ ግንኙነት ማድረግ፣ የግልንና የአካባቢ ንጽሕናን ያለመጠበቅና የመሳሰሉ ሁኔታዎች ለበሽታው መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።
በማጅራት ገትር በሽታ የተያዘ ሰው የሚከተሉት የሕመም ስሜቶችና ምልክቶች ይታዩበታል።
• በድንገትና በአጣዳፊ ሁኔታ የሚጀምር የጤንነት መታወክ፣ • ከፍተኛ ትኩሣት /በአዋቂዎች ላይ ይበረታል/፣ • ማቅለሽለሽና ማስታወክ /በሕፃናት ላይ ይበረታል/፣ • በጣም ከባድ ራስ ምታት፣ • ማቃዠትና አዕምሮ መሳት፣ • መወራጨትና የጡንቻዎች በተለይም የጀርባና የማጅራት አካባቢ መኮማተርና መገተር፣ • የዓይኖች ሙሉ ለሙሉ ብርሃን ለማየት ያለመቻል ናቸው፡፡
ይህ በሽታ በዚህ የዕድሜ ክልል ያሉትን ያጠቃል ባንልም በአብዛኛው ለበሽታ የተጋለጡት ከሁለት እስከ ሠላሳ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት የኀብረተሰብ አባላት ናቸው። የበሽታው ተሕዋስያን በጆሮና በዓይን ነርቮች ላይ ጉዳት ስለሚያደርሱ መደንቆርንና መታወርን ሊያስከትሉ ይችላሉ። በማጅራት ገትር የተያዘ ሰው የልብና የኩላሊት ሕመም ሊደርስበት ይችላል። የአጥንት መገጣጠሚያዎች ሕመምና የመዋጥ ችግር ይፈጥርበታል። አልፎ አልፎ በሳንባ ምች የተነሣ ይሞታል። በአጠቃላይ በማጅራት ገትር የተያዘ ሰው ከአካል መጉደል እስከ ሕይወት ማጣት የሚያደርሱ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ።
ማጅራት ገትር በሕክምና የሚድን በሸታ ነው። ፈጣንና ተገቢ ሕክምና የተደረገላቸው ሕመምተኞች ከመቶው ከዘጠና በላይ የሚሆኑት የመዳን ዕድል አላቸው። ሕክምና ካላገኙ ግን የሚገድል በሽታ ነው። ማጅራት ገትርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከምንጠቀምባቸው ዘዴዎች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
• በአንድ አካባቢ ማጅራት ገትር መኖሩ ጥርጣሬ ካለ በክልሉ የሚገኙ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች እንደዚሁም ግለሰቦች ፈጥነው በአቅራቢያው ለሚገኙ የጤና ድርጅቶች ማሳወቅ፣ • መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች ከጤና ተቋሞች ጋር በመተባበር ኀብረተሰቡ ስለበሽታው ምንነት እንዲያውቅ መቀስቀስ እንደዚሁም የተጠናከረ አሰሳ እንዲካሄድ፣ • መጠለያዎች እንዲሠሩና ከያሉበት ወደ መጠለያዎች እንዲወሰዱ ማድረግ፣ • የማጅራት ገትር ወረርሽኝ በሚነሳበት ወቅት ሕዝቡን ሊያሰባስቡ የሚችሉና በሽታውም እንዲዛመት የሚያግዙ እንደማኅበር፣ ሰርግ፣ ሰደቃና የመሳሰሉትን ወረርሽኙ ጋብ እስከሚል ድረስ ማቆየት። ይህም በሸታው እንዳይዛመት የሚረዳ መሆኑን ኀብረተሰቡ እንዲያውቅ ማድረግ፣በሸታው በገባበት ክልል በተለይም የሕዝብ ክምችት ባለባቸው ሥፍራዎች ለምሳሌ በትምህርት ቤቶች፣በወታደር ሠፈሮች፣ በመጠለያዎች፣ በወህኒ ቤቶችና በመሳሰሉት የመከላከያ ክትባት መስጠት፣ • የማጅራት ገትር ሕሙማንን በቅርብ ያስታመሙና የሚያስታምሙ ሰዎች የመከላከያ መድሃኒት እንዲውጡ ማድረግ፣ • ለሕሙማን ጊዜያዊ መጠለያ በማዘጋጀት ተገቢ የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ፣ • በሽታው በገባበት አካባቢ የሚገኝ ማንኛውም ሰው በሚያስነጥስበትም ሆነ በሚስልበት ጊዜ በመሐርም ወይም በጨርቅ አፍንና አፍንጫን መሸፈን በተጨማሪም ንፍጥንም ሆነ አክታን የትም እንዳይጣል ጥንቃቄ ማድረግ፣ በአጠቃላይም የግልንና የአካባቢ ንጽሕናን መጠበቅ።
በንግሥት ዘውዲቱ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ዓቢይ ኃይሉ «በማጅራት ገትር መያዙ በምርመራ የተረጋገጠው በሽተኛ ህክምና መውሰድ የሚችለውም በሆስፒታሉ ውስጥ በመተኛት በደምስር በሚሰጥ አንቲባዮቲክስ( ፀረ ባክቴሪያ) መድኃኒት ነው።» ይሉና በበሽታው የተያዘ ሰው በሆስፒታል ውስጥ ከሰባት እስከ አስራ አራት ቀናት ተኝቶ መታከም እንዳለበትም ይገልጻሉ።
- የኢትዮጵያ ጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ኢንስቲቲዩት፤ «ማጅራት ገትር»፤ http://ehnri.gov.et/Leaflet.pdf Archived ኦገስት 7, 2013 at the Wayback Machine
- አዲስ ዘመን፤ «ድንገተኛውና ተላላፊው ማጅራት ገትር»፤
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/society/337-2013-03-07-06-24-18