በር:ሳይንስ/መግቢያ

ከውክፔዲያ

ሳይንስ ከተጨባጩ ዓለም በሥርዓት መረጃ የሚሰበስብ፤ ከተሰበሰበው መረጃ ተነስቶ ዕውቀት የሚገነባ እና በተመክሮ ቢፈተኑ ጸንተው ሊቆሙ የሚችሉ ትንቢቶችንና ማብራሪያዎችን የሚያስገኝ የዕውቀት ዓይነት ነው።

በፍልስፍና አስገዳጅ ዕውነት (የአምክንዮ ዕውነት) እና አጋጣሚ ዕውነት (ሓቅ) የተባሉ ሁለት ዓይነት ዕውነቶች አሉ። የሳይንስ ዕውቀቶች በአጋጣሚ ዕውነቶች (ሓቆች)ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ይህም ሲባል ለሓቆች እንዲህ ሆኖ መገኘትና፣ እንደዚያ ሆኖ አለመገኘት አስገዳጅ አመክንዮ የለም። ለምሳሌ መሬት በላይዋ ላይ ያለን ማንኛውንም ቁስ ትስባለች፣ ይህ ግን ያለንበት ዓለም ዕውነታ ነው እንጂ መሬት ማንንም ባትስብ ምንም የአመክንዮ መጣረስ አይኖርም። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ሰው ከ ጥሩ መሪ ሃሳቦች ተነስቶ፣ በጥሩ አመክንዮ፣ «የመሬት ስበት የለም» እሚል ድምዳሜ ላይ ሊደርስ ይችላል። ድምዳሜው ስህተት መሆኑን በምንም ዓይነት በአመክንዮ ብቻ ማዎቅ አይቻልም ምክንያቱም የአመክንዮ መጣረስ ስለማይፈጥር። በአጠቃላይ መልኩ፣ ሓቆች በአዕምሮ ፍልስፍና ብቻ ሊደረስባቸው አይቻልም።

ሳይንስ በአመክንዮ ብቻ ሳይሆን በተጨባጩ አለም ውስጥ በመሞከር፣ ከተሞክሮውም ዕውነትና ውሸቱ እየጠራና እየተመዘገበ በሂደት እየተሻሻለ የሚሄድ የዕውቀት አይነት ነው። የመሬትን ስበት ሓቅነት ለመገንዘብ እሚፈልግ በማሰብ ብቻ ሳይሆን ዘሎ መሬትን ለማምለጥ በመሞከር ሊያውቅ ይችላል። ለዚህና ለመሳሰሉት ስራዎች፣ ዘመናዊው ሳይንስ የሳይንሳዊ ዘዴን ይጠቀማል።

ዘመናዊው ሳይንስ ፣ ሰፊ ዕውቀትን በመሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ይህን ዕውቀት በሥራ ላይ በማዋል ያለተወዳዳሪ የሰውን ልጅ ህይወት በማሻሻል ላይ ይገኛል። በሽተኞች መታከማቸው፣ የእርሻ ምርት መትረፍረፍ፣ የመገናኛ ብዙሃን መፈጠርና ማደግ፣ ወዘተ...እነዚህ ሁሉ የዚህን ዕውቅት ሥኬት የሚያሳዩ ናቸው።









ጨረቃ በመሬት ከፀሐይ ስትጋረድ