Jump to content

ቢልሃርዝያ

ከውክፔዲያ


ሺስቶሶሚያሲስ ወይም ቢልሃርዝያ (Bilharziasis) ሺስቶሶማ በሚባሉ የደም ወስፋቶች ደም ውስጥ መገኘት የሚመጣ የሰው በሽታ ነው። ሺስቶሶሚያሲስ በመባልም የታወቀውን በሽታ የሚያስከትሉ የተለያይ ዓይነቶችና ኣኗኗር ያሏቸው የእንስሳት ትናንሽ ትሎች ቢኖሩም ሺስቶሶማ ማንሶኒ በመባል የታወቀው ኣንደኛው ነው። ወንድና ሴት ትሎች ተገናኝነው በመጣበቅ የሰው ደም ውስጥ በመኖር ብዙ ሺህ እንቁላሎች ያፈራሉ። ከትሎቹም ጉዳት የተነሳ እንቁላሎቻቸው ከሽንት ጋር ሲወጡም ደም ሊያሸኑ ይችላሉ። እንቅላሎቹ ከሰገራና ከሽንት ጋር ከሰውነት ወደ ውጪ ከወጡ በኋላ ቀንድ ኣውጣ ውስጥ ገብተው ይራባሉ። ከእዚያም ከቀንድ ኣውጣው ወጥተው ውሃ ውስጥ በመቆየት የሰውን ቆዳ በስተው ወደ ደም ስር ይገባሉ። መድኋኒትና የማያስተማምን መከላከያ ክትባቶች ቢኖሩም በሽታውን ለመቆጣጠር ሰገራና ሽንት ማንኛውንም ዓይነት ውሃ እንዳይበክል መቆጣጠር ያስፈልጋል።

ሺስቶሶሚሲስ

በሽታው ሰውን የሚይዘው ሰርኬርያ የሚባሉት የትሉ ኣንድ ዓይነት ደረጃ ሰው ሲዋኝ ወይም በባዶ እግሩ ውሃው ውስጥ ሲሄድ ቆዳን በመብሳት ወደ ሰውነት ስለሚገቡ ነው። ውሃን በወረቀት በማጥለል ወይም አዮዲን ወይም ክሎሪን በመጠቀም ከቀንድ ኣውጣው ወጥተው ወደ ደም ለመግባት የሚጠባበቁትን ሰርኬርያ ዋኝዎች ሊገድል ስለሚችል ውሃውን በመጠጣት በበሽታው እንዳንያዝ ሊጠቅም ይችላል። ውሃን ማፍላት ሰርኬርያዎችን ከመግደሉም ሌላ እንዶድ ቋሚ ውሃ ኣካባቢ መትከል ሳይጠቅም ኣይቀርም ይባላል።

በዓለም ላይ ከወባ ቀጥሎ ከ፪፻ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማሰቃየት ሺስቶሶማ ሁለተኛ ጠንቅ ነው። በሽታው ኢትዮጵያም ኣለ። የግድቦች መሠራትና የመስኖ ኣጠቃቀም መስፍፋት ቀንድ ኣውጣዎችንና የወባ ትንኞችን ቍጥር ሊያስጨምር ስለሚችል ለሚያስከትሉት በሽታዎች ዕድል እንዳይሰጥ ውሃው እንዲንቀሳቀስና ሌሎች ኣስፈላጊዎች መከታተል ይጠቅማል። ለምሳሌ ያህል ሰርኬርያዎች ከቀንድ ኣውጣ ወጥተው በ48 ሰዓታት ሰው ውስጥ መግባት ካልቻሉ ስለሚሞቱ እነሱ ሊኖሩበት የሚችልን ውሃ ቀድቶ በትንሽ ዕቃ ከተቀመጠ በኋላ ሁለት ቀን እስካለፈው ለገላ መታጠቢያ ሊያገለግል ይችላል። ውሃ ኣጠገብ ሰገራ መውጣትና ሽንት መሽናት እንቁላሎቹ ተፈልፍለው ሚራሲዲያ የሚባሉት የቢልሃርዚያ ሌላው ደረጃ ወደ ቀንድ ኣውጣዎች ዋኝተው እንዲገቡ ስለሚራዳ ሽንት ቤት መጠቀም ኣስገላጊ ነው።

ዶ/ር አክሊሉ ለማ እንዶድ ቀንድ ኣውጣውን ለመግደል ስለሚችል በሽታውን ለመቆጣጠር እንደሚራዳ ስለደረሱበት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ዶ/ር ኣክሊሉ ለማም ስለ እንዶድ ጥቅምና የውሃ ትላትል ገዳይነት በማግኘታቸው በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. እና በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም. የዩናይትድ እስቴትስ የፈጠራ ባለቤትነት ወይም ፓተንቶች ኣግኝተዋል። እንዲሁም ስለ እንዶድ ምርምር ከዶ/ር ኣክሊሉ ጋር ለብዙ ዓመታት ስላደረጉት ኣስተዋጽዖ ዶ/ር ለገሠ ወልደዮሓንስ ዕውቅና ኣፍርተዋል።

የውጭ መያያዣዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]