ብጫ ሱማራ

ከውክፔዲያ

ብጫ ሱማራ (እንግሊዝኛ፦ Yellow Submarine /ዬሎው ሰብመሪን/) በ1960 ዓም ዘ ቢተልስ ሙዚቃ ቡድን የሠሩት ዝንኛና ተወዳጅነት ያገኘ የልጆች ካርቶን ፊልም ነበር። በርካታ ዘ ቢተልስ ዘፈኖች በካርቶኑ ሕልም ታሪክ ውስጥ ይሰማሉ።

በሕልሙ ታሪክ ዘንድ፣ «ፔፕርላንድ» («ቁንዶብርብሬ አገር») ከባሕር በታች የሚገኝ፣ ሙዚቃ ወዳጅ፣ ደስ የሚል አገር ነው። አገሩ በ«ሳርጀንት ፔፐርዝ ሎንሊ ሃርትስ ክለብ ባንድ» ጥብቅና ነው («የሀምሳለቃ ቁንዶበርበሬ ብቸኛ ልቦች ጉባኤ ቡድን»)፣ ይህም ዘ ቢተልስ ሙዚካ አልበም ስም ነበር። አንድ ብጫ ሱማራ በኮረብታ ላይ በአዝቴክ ፒራሚድ ላይ ይቀመጣል። በአገሩ ጫፍ ከፍ ያሉ ሰማያዊ ተራሮች አሉ።

ከተራሮች ማዶ የሚኖሩት፣ ሙዚቃን በጣም የጠሉት «ብሉ ሚኒዝ» (ሰማያዊ ጨካኞች) ድንገት ወረሩ። በጥቃቱ መጀመርያ፣ አንድ ታላቅ ሰማያዊ ብርጭቆ ሉል የሙዚቃ ቡድን አባላትን አሠራቸው። ከዚያ ጨካኞቹ በመድፍ ተኩሰው ፔፐርላንድን በፍላጻና ትልቅ አረንጓዴ ቱፋሕ ይደብደባሉ፣ እኚህም የፔፐርላንድ ኗሪዎች እንደ ድንጋይ አደረጋቸው፣ አገር ቤቱንም ሁሉ ከብዙ ቀለሞች ወደ ቡላ ቀየሩት።

የፔፐርላንድ ከንቲባ ሳይማረክ፣ «ፍሬድ» የተባለ መርከበኛ እርዳታ ለመፈልግ በብጫው ሱማራ በኩል ይልከዋል። ፍሬድ በሱማራው ወደ ሊቨርፑል፣ እንግሊዝ ተጉዞ፣ ዘ ቢተልስ አባላት - ጆን ሌኖንፖል መካርትኒጆርጅ ሃሪሰንሪንጎ ስታር - አገኛቸውና ወደ ፔፐርላንድ እንዲመልሱ አሳመናቸው። በመንገዳቸው ላይ፣ የሚያልፉባቸው ብዙም ጉዶች የሚታዩባቸው አገራት «የጊዜ ባሕር»፣ «የሳይንስ ባሕር»፣ «የአሰቃቂዎች ባሕር»፣ «የምንም ባሕር»፣ እዚህ የጥንቸል ጅራትና የተራቢ መልክ ያለውን ፍጡር «ጄረሚ ሂላሪ ቡብ» አገኝተው በሱማራ ጉዞ ይሸኛቸዋል። ከዚያም «የርዕስ ምድር ግርጌ ኮረብቶች» ደርሰው በጄረሚ ሳቢያ እሱና ዘ ቢተልስ ከሱማራውና ከፍሬድ ተለይተዋል። ቁንዶ በርበሬ የርዕስ ምድር ኗሪዎች እንዲያነጥሱ ያደርጋል፣ እንዳነጠሱም ዘ ቢተልስና ጄረሚ ወደ «ቀዳዳ ባሕር» ተነፉ። በዚህም ባሕር የብሉ ሚኒዝ ዘበኞች ጄረሚን ማረኩ፤ ዘ ቢተልስ በአንድ አረንጌዴ ቀዳዳ ገብተው «የአረንጓዴ ባሕር» ውስጥ ሆኑ፣ ከዚያ ወደ ፔፐርላንድ ከነሱማራው ይመልሳሉ።

አሁን ፔፐርላንድ ደስ የሚል አገር ሳይሆን አበቦቹ እሾህ ሆነዋል፣ ድንጋይ የሆኑት ኗሪዎች ቀለም በሌለው ወና በረሃ ውስጥ አሉ፤ ብሉ ሚኒዝ ያሳዝናቸዋል፣ ሙዚቃም ተከለክሏል። ዘ ቢተልስ ተደብቀው የሳርጀን ፔፐርዝ ባንድ ትርፍ ልብሶችና ሙዚቃ መሣሪያዎች አገኝተው ይወስዷቸዋል፤ እንደ ሳርጀንት ፔፐርዝ ተለብሰው በሙዚቃና በፍቅር ዘፈኖች በኩል ሲታገሉ ብሉ ሚኒዙን አሸነፏቸው፣ ኗሪዎቹም ወደ ስጋ፣ አገሩንም ወደ ብዙ ቀለሞች፣ እሾህም ወደ አበባ አስመለሱ። ኦሪጂናሉን ሳርጀንት ፔፐርስ ባንድና ጄረሚንም አዳኟቸው።

የብሉ ሚኒዝ ጨካኝ አለቃ ሳይሸሽ ጄረሚን ገደለ፣ ጄረሚ ግን በተዓምር ተመለሰ፣ አለቃውን በአበቦች ሸፈነው፣ ጸባዩንም ከጭካኔ ወደ ምኅረት ቀየረው። ከዚህስ በኋላ ሁላቸው በፍቅር አንድነት ሙዚቃን በመውደድ ይኖራሉ።