Jump to content

ቱሩካውያን

ከውክፔዲያ
(ከቱሩኩ የተዛወረ)

ቱሩካውያን (ቱሩኩቱሩኩም) በጥንት በኡርሚያ ሐይቅ ዙሪያ (በአሁኑ ስሜን-ምዕራብ ፋርስ አገር) የተገኘ ብሔር ነበሩ። ምናልባት የሑራውያን ዘር ሊሆኑ እንደተቻለ ይታሥባል።

በ2036 ዓክልበ. ግድም «የቱርኪ ንጉሥ ኢልሹናኢል» ከሐቲ ንጉሥ ፓምባ ጓደኞች መካከል ሆኖ የአካድ ንጉሥ ናራም-ሲን እንዳሸነፋቸው በአንድ ጽላት ተዘገብ። የ«ቱርኪ» ትርጉም እዚህ «ቱሩኩ» እንደ ሆነ እርግጥኛ አይደለም።

በ1692 ዓክልበ. ግድም ቱሩካውያን የያምኻድ ንጉሥ የሱሙ-ኤፑኽ ጓደኞች ሆነው በ1 ሻምሺ-አዳድ ላይ ጠላትነት እንደ ጀመሩ፣ ሻምሺ-አዳድም እንዳሸነፋቸው በመዝገቦች እናነብባለን። ከዚህም ዘመን የሹሻራ (ተል-ሸምሻራ) ጽላቶች እንደገለጹ፣ ከቱሩካውያን ከተሞች ዋናው ኢታባልሁም ተባለ፤ ጉታውያንም ከደቡባቸው ጥቃት ጥለው ወደ ምዕራባቸው ያባርሯቸው ነበር።

በሻምሺ አዳድ ልጅ በ1 እሽመ-ዳጋን ዘመን መጀመርያ (1688 ዓክልበ.)፣ የቱሩኩ ጎሣ አለቃ ሊዳይ ጽኑ አመጽ በሹሻራ አገር አስነሣሣ። ክፍላገሩ በተለይ ተራራማ ስለ ሆነ፣ እሽመ-ዳጋን የአሦርን ሠራዊት ሹሻራን እንዲተው አደረገ።

በኋላ እሽመ-ዳጋን ከበፊቱ ጠላቶች ከቱሩኩ ሕዝብ ጋር የስምምነት ውል አደረገ። የቱሩኩ አለቃ ዛዚያ ሴት ልጅ ለእሽመ-ዳጋን ወንድ ልጅ ለሙት-አሽኩር ታጨች።

በዚህም ዘመን ግድም በተቀረጹት በማሪ ጽላቶች ዘንድ፣ የቱሩኩ ንጉሥ ዛዚያ የሲሙሩምን ንጉሥ ወደ ጉታውያን እንዳስረከበው ይገልጻል።

ባቢሎን ንጉሥ ሃሙራቢ ደግሞ በ1669 ዓክልበ. በቱሩኩ ሕዝብ ላይ ይዘመት ነበር። ከዚያ በኋላ የ«ቱሩኪ» አገር አንዴ ብቻ ይጠቀሳል፣ ከ1 አዳድ-ኒራሪ (1309-1278 ዓክልበ.) ክፍላገራት መካከል ይዘረዝራል።

በአንዳንድ በተለይም በቱርክ ወይም በአዘርባይጃን መምህሮች ዘንድ፣ ይሄ «ቱርክ» ለሚለው ስያሜ መጀመርያ ናሙና ሆኖ ለቱርኪክ ሕዝቦች ጥንታዊ አባቶች ነበሩ። በተረፈ ሌሎች የምዕራብ መምህሮች ግን ይህንን ሀሣብ አልተቀበሉም።