ቲፎን

ከውክፔዲያ
ዚውስ ቲፎንን በመብራቅ ሊመታው ሲል

ቲፎን (ግሪክኛ፦ Τυφῶν /ቲውፎን/፤ ደግሞ ቲውፎስ፣ ቲውፈውስ፣ ቲውፋዖን) በጥንታዊ ግሪክ አፈ ታሪክ አስፈሪና አደገኛ ጠላት ፍጡር ነበረ።

በግሪኮች ትውፊት ዘንድ፣ ከወገቡ በላይ እንደ ሰው ልጅ ቢመስልም በራሱ ፈንታ አንድ መቶ የአርዌ (ደራጎን) ራሶች ከትክሻውና ከአንገቱ በቀሉ። (በሌላ ምንጭ ግን የሰው ልጅ ራስ ሲኖረው የደራጎን ራሶች ከጣቶቹ በቀሉ)። ከወገብ በታች ሁለንተናው የእፉኝት ነበር (ወይም ከወገቡ በታች መቶ እፉኝቶች ነበር)። ሰውነቱ ደግሞ በብዙ ክንፍ ተሸፈነ፤ እሳትም ከዓይኖቹ ወጥቶ አማልክት እንኳን ይፈሩ ነበር። በቲታኖማኪያ ጦርነት ዘመን ዚውስ ቲታኖችን ስለ አሠራቸው፣ ቲፎን ዜውስን ለማጥፋት ሞከረ። ከትግል በኋላ ግን ዚውስ መብራቅን በመጣል አሸነፈውና ከደብረ ኤትና በታች (ወይም በታርታሮስ፣ በግሪኮች ዘንድ ገሐነም የመሰለ ቦታ) አጠመደው።

ሄሮዶቶስ እንዳመለከተው፣ በጥንታዊ ግብጽ አፈ ታሪክ የሚታወቀው ሴት የተባለው ጣዖት ደግሞ በግሪኮች «ቲፎን» ይባል ነበር። ከሁሉ ጥንታዊ በሆነው ታሪካዊ ዘመን ከፈርዖኖቹ አስቀድሞ፣ እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ የሴት ዓላማ ወይም ምልክት «የሴት እንስሳ» (ምናልባት አዋልደጌሣ) ሲሆን ግሪኮች በኋላ ይህን ምልክት «ቲፎናዊ አውሬ» ይሉት ነበር። በትውፊቶቹ ዘንድ፣ ሴት ቀድሞ ወንድሙን ኦሲሪስን (ቄንቲያመንቱን) እንደገደለው ሁሉ፣ እንዲሁም ቲፎን ከቲታኖች (ጊጋንቴስ) ወገን አብሮ ዲዮኒስዮስን ወይም ኦሲሪስ አፒስን ገደለው። ሁለተኛውን ኦሲሪስ ስለ ገደለው ይህ ቲፎን ደግሞ እንደ ሴት (ጣኦቱ) ተቆጠረ።