ታይ ጅያ

ከውክፔዲያ

ታይ ጅያ (ቻይንኛ፦ 太甲) በጥንታዊ ቻይና የሻንግ ሥርወ መንግሥት ንጉሥ ነበር።

ቀርቀሃ ዜና መዋዕል እና በሢማ ጭየን ታሪካዊ መዝገቦችም ዘንድ ለ12 ዓመት የዳ ዲንግ በኲር ሲሆን ከዦንግ ረን ቀጥሎ ነገሠ፤ ልጁም ዎ ዲንግ ተከተለው። ዪ ዪን በዚህ ዘመን ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆን ቀረ። ከመሥራቹ ታንግ ልጅ-ልጆች ታላቁ ስለ ነበር ዪ ዪን ለዙፋን መረጠው፣ «ትምህርት ለታይ ጅያ» የተባለ የምክር ጽሁፍ በተለይ ለርሱ አዘጋጀ።

ታይ ጅያ ከሚኒስትሩ ዪ ዪን ጋር እንደ ታገለ ይመስላል። በሢማ ጭየን ዘንድ፣ ከሦስት አመት በኋላ ታይ ጅያ ረባሽና ትምህርቱን የማይከተል ንጉሥ ስለ ሆነ ዪ ዪን ለሚከተሉት ፫ አመት አሠሩትና እራሱ መንግስቱን አስተዳደረ። ከዚህ በኋላ ታይ ጅያ ንሥሐ ገብቶ ለማስተዳደሩ እንዲመለስ ተፈቀደለትና ዪ ዪን እስከ ዎ ዲንግ መጀመርያ ዓመት ሚኒስትር ሆኖ ተቀጠለ።

ቀርቀሃ ዜና መዋዕሎች ግን ዪ ዪን ታይ ጅያን ከ1ኛው እስከ 7ኛው ዓመት አሥሮት ታይ ጅያ ከዚያ አመለጠና ዪ ዪንን አስገደለው ይላል። ይህ ከሌላ መረጃ ጋር ስለማይስማማ በኋላ ወደ ዜና መዋዕሉ የተሰካ ይሆናል የሚል ነጥብ ደግሞ ተጽፎበታል።

በሥነ ቅርስ ከ1200 ዓክልበ. የተገኙት «ንግርተኛ አጥንቶች» ጽሑፎች ላለፉት ነገሥታት መሥዋዕት ሲዘረዝሩ፣ ታይ ጅያ በቀጥታ ከአባቱ ዳ ዲንግ ቀጥሎ ነገሠ፣ ዦንግ ረንን ወይም ዎዲንግን አይጠቅሱም፤ ተከታዩም ቡ ቢንግ (ዋይ ቢንግ) ሆነ ይላሉ። ሆኖም ዳ ዲንግ ሳይነግሥ እንዳረፈ፣ ዪ ዪንም ያለመቋረጥ ከታንግ ጀምሮ እስከ ዎ ዲንግ ድረስ (1628-1581 ዓክልበ.) እንደ ሻንግ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳገለገለ ትክክለኛ ስለሚመስል ቅደም-ተከተሉ ሢማ ጭየን እንዳለው መሆን አለበት።

ቀዳሚው
ዦንግ ረን
የሥያ (ቻይና) ንጉሥ
1593-1581 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ዎ ዲንግ