ኅልውነት
አብዛኞች ሃይማኖቶችና ፍልስፍናወች የሰው ልጅ ኅይወት ትርጉም (አላማ) አለው ብለው ያምናሉ። ስለሆነም ይህን አላማ ወይም ለማስፈጸም ወይም ደግሞ ለማግኘት ሲጥሩ ይታያሉ። ከዚህ በተጻራሪ በኅልውነት ፍልስፍና የሰው ልጅ ህይወት ከመፈጠሩ (ኅልው ከመሆኑ) በፊት የተጻፈ ትርጉምም ሆነ አላማ የለውም። ስለሆነም የፍልስፍና አትኩሮት መሆን ያለበት «እያንዳንዱ ግለሰብ ለህይወቱ እንዴት ትርጉምና አላማ መስጠት አለበት?» የሚል ነው። የኅልውነት ፍልስፍና አባት ነው የሚባለው ሶረን ኬርከጋርድ እንዳስቀመጠው «እያንዳንዱ ግለሰብ ለህይወቱ ትርጉም የመስጠት እንዲሁም ይህን ህይወቱን በሃቀኝነትና በሙሉ ስሜት የመምራት ኃላፊነት አለበት።» ይህ ሲሆን ታዲያ ተስፋ መቁረጥ፣ የኅልውና ድንጋጤ፣ ባይተዋርነት፣ ድብርትና መሰረተ ቢስነት የተባሉ የኅልውና ቀውሶች የሰውን ልጅ ይጋረጣሉ፣ እኒህን እንቅፋቶችን የማሸነፍ ዘዴ መቀየስ የኅልውነት ፍልስፍና አይነተኛ አትኩሮት ነው።
የሰው ልጅ ህይወት ትርጉም የለሽና አላማውም የማይታወቅ ሲሆን ትርጉም አለው እምንለው እያንዳንዱ ግለሰብ ለህይወቱ በራሱ እጅ ትርጉም (አላማ) እስከሰጠው ድረስ ብቻ ነው። በሌላ አባባል ኅልውና ከምንነት ቀዳሚ እንጂ ተከታይ አይደለም። ይሄ የኅልውነት ፍልስፍና ዋና ቁልፍ ሃሳብ ነው፣ ትርጉሙም እንዲህ ነው፡ አንድ ግለሰብ ከመፈጠሩ (ኅልው ከመሆኑ) በፊት "ምንነቱ" አልተጻፈም ስለዚህ የግለሰቡ "ምንነት" ኅልው ከሆነ በኋላ በሚያደርጋቸው የኑሮ ምርጫወች ይፈጥራል፦ እያንዳንዱ ግለሰብ በንቃተ ህሊናው የራሱን ዋጋና የራሱን የህይወት ትርጉም ይጽፋል።
በዚህ ተቃራኒ አንድ ህንጻ ቢገነባ ህንጻው ለምን ግልጋሎት እንደሚጠቅም ከወደፊት ተጠንቶ ነው። ስለዚህም ህንጻው ኅልው ከመሆኑ በፊት "ምንነት" አለው እንላለን። አላማው/ግልጋሎቱ/ምንነቱ ከኅልውነቱ ቀደመ። እንዲሁ አንድ ቢላዋ ከመሰራቱ በፊት ለመክተፍ እንደሚያገለግል፣ ይህም የመኖሩ (ኅልውናው ) ዋና አላማ መሆኑ ይታወቃል። በኅልውነት ፍልስፍና የሰው ልጅ እንደዚያ አይደለም። የሰው ልጅ፣ ጀርመን አገርም ሆነ ሱዳን፣ ፊሊፒንስም ሆነ አሜሪካ፣ ከመፈጠሩ በፊት የህይወቱ "ምንነት" አይታወቅም። ከተፈጠረ በኋላ በሚያደርገው ምርጫወች ምንነቱ ይታወቃል። ከመፈጠሩ በፊት "ምንነቱ" አለመታወቁ የሰው ልጅ ለሰራው ስራ ሁሉ ሙሉ ነጻነት እንዲኖረው ያደርጋል፣ ስለዚህም ለያንዳንዱ ድርጊቱ ሙሉ ተጠያቂነት ይኖረዋል። ይህ ጉዳይ የኅልውና ድንጋጤ በያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ይፈጥራል።
ለምሳሌ አንድ ሰው ከገደል ጫፍ ላይ ቢቆም ሁለት ድንጋጤወች ይጋፈጡታል፣ አንደኛው «ወድቄ ብከሰከስስ» የሚል ሲሆን ሁለተኛውና ለምንነጋገርበት ርዕስ ጠቃሚ የሆነው ደግሞ «ምናልባት እራሴን ብወረውርስ» የሚል ፍርሃቻ ናቸው ። በዚህ አጣብቂኝ ግለሰቡ "ምንም የሚይዘኝ ነገር የለም" ወይም ደግም "በተፈጥሮየ እራሴን እንዳልወረውር የሚጠብቀኝ እንዲሁ በተቃራኒው እራሴን እንድወረወር የሚገፋፋኝ እድል እጣ ፈንታ የለኝም፣ ሁለቱም እራሴ በማደርገው ምርጫ የሚወሰን ነው" የሚለውን መሰረታዊ የሰው ልጅ ነጻነት ይረዳል። ይህ የመመረጥ ሙሉ ነጻነትና የሚያስከተለው ሙሉ ሃላፊነት በሰው ልጅ ላይ ድንጋጤን ይፈጥራል። የኅልውና ድንጋጤ እንደሌሎች የፍራቻ አይነቶች ሳይሆን አብሮ ከሰው ልጅ ሙሉ የመምረጥ ነጻነት ጋር ምንጊዜም የሚገኝ ነው።
ኅልውነት በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን በተነሱ የአውሮጳ (ፈረንጅ) ፈላስፎች የተጠና የፍልስፍና አይነት ነው። ለዚህ የፍልስፍና አይነት ከፍተኛ አስተዋጾ ካደረጉ ውስጥ ዶስቶቭስኪ፣ ኒሺ፣ ዦን-ፖል ሳርት፣ ኬርከጋርድ፣ ካሙ ይገኙበታል።