አርጉስ

ከውክፔዲያ

አርጉስ (Ἄργος) በግሪክ አፈ ታሪክ የአርጎስ ከተማ-አገር ፬ኛው ንጉሥና ሞክሼ ነበር። የአርጎስ ስም ከዚሁ ንጉሥ አርጉስ እንደ ተሰጠ በግሪኮች ይጻፍ ነበር።

ካስቶር ዘሩድን የሚጠቅሱት ጸሃፊዎች ጄሮምአውሳብዮስ እንደሚሉ፣ አርጉስ የአርጎስ ንጉሥ ሆኖ በአገሩ «አርገያ» ለ70 ዓመታት ነገሠ፣ የዚውስና የኒዮቤ ልጅ ይባላል። ኒዮቤም የፎሮኔዎስ ልጅ ነች። ከፎሮኔዎስና ከአርጉስ ዘመናት መካከል ግን የአፒስ ግዛት መሆኑን ይላሉ።

ቢብሊዮጤኬ የሚባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ «ኒዮቤ ግን ከዚውስ ልጁን አርጉስን ወለደች፣ ደግሞ አኩሲላዎስ እንደሚል፣ ልጁንም ፔላስጎስን ወለደች፣ የፔላስግያውያን ብሔር የተሰየሙለት ነው።» በዚህ መጽሀፍ የአርጉስ ሚስት ኤዋድኔ ተባለች፣ ይችም የስትሩሞንና የነያይራ ሴት ልጅ ነበረች። የአርጉስና ኤዋድኔ ልጆች እነዚህ ናቸው፦ ኤክባሶስ (ወይም «ያሶስ» በአንዳንድ ምንጭ) ፣ ፒራስ፣ ኤፒዳውሮስ እና ተከታዩ ክሪያሶስ ይባላሉ።

ፓውሳኒዮስ እንደሚጽፍ፣ የአርጉስ ልጆች ፔይራሶስና ፎርባስ ነበሩ፤ ይህ ፎርባስ በካስቶር ዝርዝር ግን የክሪያሶስ ተከታይና ልጅ ነው። በሌላ ቦታ ቲሩንስ የሚባል ከተማ ስለ አርጉስ ሌላ ልጅ ቲሩንስ እንደ ተሰየመ ይላል። እስከ ፓውሳኒዩስ ዘመን ድረስ (2ኛው መቶ ዘመን ዓ/ም) የአርጉስ መቃበር በአርጎስ ከተማ እንደ ታየ ይለናል።

ቅዱስ አውግጢኖስ የእግዜር ከተማ በተባለ መጽሐፍ እንዲህ ጻፈ፦ «በአርጉስ ዘመን፣ የፍራፍሬ ጥቅም በግሪክ አገር ጀመረ፤ እንዲህም የእህል ሰብል በታረሰ እርሻ ውስጥ - ዘሩን ከውጭ አገር አምጥተውት። አርጉስ ደግሞ ከመሞቱ በኋላ እንደ አምላክ ይቆጠር ጀመር፤ በቤተ መቅደስና በመስዋዕትም ተከበረ። ይህ ክብር ለእርሱ ሳይሰጥ፣ በዘመኑ ውስጥ በሬ ወደ ማረሻ መጀመርያ ለጣመደው ግለሰብ ተሰጥቶ ነበር፤ ይህም በመብራቅ የተመታው ሆሞጊውሮስ ነበረ።»

በሌላ ትውፊት አርጉስ ፓኖፕቴስ (አርጉስ «ሁሉ-ዓይኖች») የሚባል ትልቅ ሰው አለ። ይህ ትልቅ ሰው የኤክባሶስ ልጅ ልጅ ይባላል። በአንዳንድ ምንጭ አርጉስ ፓኖፕቴስ ስለ አፒስ ግድያ ቂም ይበቅላል። የትውልድ ሓረጎቹ ቀደም-ተከተል ግን በየምንጩ በጣም ይለያያሉ። አንዳንዴም አርጉስ ፓኖፕቴስ በራሱ ላይ አንድ መቶ አይኖች ነበሩት ብለው ጻፉ።

ቀዳሚው
አፒስ
የአርገያ (አርጎስ) ንጉሥ
2034-1965 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
ኤክባሶስ