ፎሮኔዎስ

ከውክፔዲያ

ፎሮኔዎስ (Φορωνεύς) በግሪክ አፈ ታሪክ የኢናቆስ እና የመሊያ ልጅ ሲሆን የአርጎስ ንጉሥ ሆነ።

ጸሃፊዎቹ ጄሮምአውሳብዮስ እንደሚሉ ፎሮኔዎስ የአርጎስ ንጉሥ ሆኖ ለ60 ዓመታት ነገሠ፣ በርሱ ዘመን ኦጊጌስ ኤሌውሲስን በአቲካ መሠረተ። ጄሮምም፦ «ፎሮኔዎስ የኢናቆስ ልጅ መጀመርያ ሕግጋት አወጣ። በ20ኛው አመት የቴልቂስና የካርያቲስ ወገኖች በፎሮኔዎስና በፓራሲዮስ ላይ ጦርነት አደረጉ» በማለት ጽፏል። ተከታዩ አፒስ በአንዳንድ ምንጭ ዘንድ ልጁ (ወይም የሴት ልጁ የኒዮቤ ልጅ) ይባላል።

ፓውሳኒዩስ፦ «እስከዚያ ጊዜ ድረስ ተበትነው እንደ ተለዩ ቤተሠቦች የኖሩትን ኗሪዎች መጀመርያው የሰበሰባቸው የኢናቆስ ልጅ ፎሮኔዎስ ነበር። መጀመርያ የተሰበሰቡበት ቦታ 'ፎሮኔዎስ ከተማ' ተሰየመ» ብሎ ይጽፋል። ፓውሳኒዩስ ደግሞ እንደሚጽፍ፥ በአርጎስ ሰዎች እምነት የእሳት ጥቅም መጀመርያ ያስተማረው ፕሮሜቴዎስ ሳይሆን ፎሮኔዎስ ስለ ሆነ፣ እርሱን ለማስታወስ የዘወትር ነበልባል በአርጎስ ሁልጊዜ ይጠበቅ ነበር። የፎሮኔዎስ ሚስት ስም «ከርዶ» ይላታል፣ ከልጆቻቸውም አንዱ «ካር» ተብሎ የሜጋራ ንጉሥ ሆነ ይላል።

ቢብሊዮጤኬ፦ «ኢናቆስ እና የውቅያኖስ ሴት ልጅ መሊያ ወንድ ልጆች ፎሮኔዎስና አይጊያሌዎስ ነበሯቸው አይጊያሌዎስ ያለ ልጅ አርፎ መላው አገር አይጊያሊያ ተባለ፤ ፎሮኔዎስም በኋላ ፔሎፖኔሶስ በተባለው አገር ሁሉ ነግሦ አፒስንና ኒዮቤን በሴት አድባሩ ቴሌዲኬ ወለዳቸው።» ሲለን ከሌሎቹ ምንጮች ቅድም-ተከተል ትንሽ ተዛብቶ ይመስላል።


ቀዳሚው
ኢናቆስ
የኢናቂያ (አርጎስ) ንጉሥ
2109-2059 ዓክልበ. ግድም
ተከታይ
አፒስ