Jump to content

አኪቫ በን ዮሴፍ

ከውክፔዲያ
ረቢ አኪቫ ቤን ዮሴፍ፣ 1560 ዓ.ም. እንደ ተሳለ።

አኪቫ በን ዮሴፍ (32-129 ዓ.ም. ግድም) የአይሁድ ዋና ረቢ ነበረ።

ረቢ ኢየሱስ ከተሰቀለ በኋላ፣ ደቀ ማዛሙርቱም በኢየሩሳሌም መቅደስ በስሙ እንዳያስተምሩ ከተከለከሉ በኋላ (የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፭)፣ የክርስትና ትምህርት ግን በአሕዛብ ዘንድ እየተስፋፋ፣ የአይሁዶች ዋና ዒላማ መጻሕፍታቸውን ለማዘጋጀትና ለማስተካከል ሆነ። ይህን ሥራ በተለይ የፈጸመው ረቢ አኪቫ በዮሴፍ ሆነ። የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይ ኪዳን) አጻጻፍ ፈጽሞ ከማዘጋጀቱ በላይ ብዙ መጻሕፍት (አዋልድ መጻሕፍት የተባሉት) እንዲወግዱ ያዘዘው እርሱ ነው። እስካሁንም ድረስ እሊህ መጻሕፍት በዕብራይስጥ ሊገኙ አይችሉም።

የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ መልክ ከአኪቫ ለውጦች ቀድሞ የሚመስክሩ ምንጮች አሉ። ከነዚህም፦

  • ሳምራዊው ኦሪት - በ700 ዓክልበ. ግድም አይሁዶች የኦሪት (የሙሴ ፭ መጻሕፍት) ቅጂ ለሳምራውያን አቀረቡ። በዘመናት ሲወረስ ይህ ልማድ ከአኪቫ በፊት የነበረው የሙሴ አጻጻፍ ጠብቋል። ሆኖም እነዚህ ለውጦች በብዛት ጥቃቅን ናቸው።
  • ሴፕቱዋጊንት («ሳባ ሊቃውንት») - 300 ዓክልበ. ግድም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት መጀመርያ ወደ ግሪክኛ ተተረጎሙ። ይህ ትርጉም አንዳንድ ስኅተቶች ቢያስገባም፣ በአንዳንድ ቦታ ተጨማሪ ዓረፍተ ነገሮች እንደ ኖሩ ይመሰክራል። እንዲሁም ከአዋልድ መጻሕፍት ብዙ ይጨምራሉ።
  • የቁምራን ብራና ጥቅሎች (የሙት ባሕር ብራናዎች) - ከ150 ዓክልበ. እስከ 70 ዓ.ም. ድረስ ሲሠሩ ከብሉይ ኪዳንና ከአዋልድ መጻሕፍት አንዳንድ ክፍሎች ተገኙ።
  • የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ - አዋልድ መጻሕፍት እስካሁን በመኖራቸው በነዚህ የአኪቫ ለውጦች በአክሱም መንግሥት ወይም ኢትዮጵያ እንደ ደረሱ አይመስልም።
  • ሮሜ መንግሥት የሮሜ ቤተ ክርስቲያንንቅያ ጉባኤ (317 ዓ.ም.) የአኪቫ ቀኖና ካጸደቀ በፊት፣ ብዙ የአብያተ ክርስቲያን አበው ወይም ጳጳሳት ከአዋልድ መጻሕፍት በሰፊው ይጠቅሱ ነበር።

አኪቫ እነዚህን «አዋልድ» መጻሕፍት ከብሉይ ኪዳን ያስወገዳቸው ምክንያት የክርስትናን ትምህርት የደገፉት መጻሕፍት ስለ ሆኑ ነው ይባላል። በረቢ አኪቫ እምነት የመሲህ መታወቂያ በሮሜ መንግሥት ላይ ያመጸው አመጸኛ ባር ኮክባ ነበረ። ስለዚህ ስለ መሲህ የሚገልጹትን ብዙ መጻሕፍት አልተቀበለም። እንዳጋጣሚ የአኪቫ ቀኖና በኋላ በንቅያ ስለ ጸደቀ፣ አሁንም አብዛኛው የዓለም ክርስትያናት የሚያንቡት መጽሐፍ ቅዱስ ፷፮ መጻሕፍት ብቻ ሲጠቀልል ሌሎቹ ተከራካሪ ሆነዋል።

በአዋልድ መጻሕፍት ፈንታ አይሁዶች በአኪቫ ዘመን አዳዲስ ጽሑፎች ጀመሩ፣ በተለይ ተልሙድ የሚባለው ማለት ነው። በርካታ የአኪቫ ተረቶች ደግሞ በተልሙድ ይገኛሉ። የአኪቫ እምነት የተነሣ መሲህ በ«መጨረሻ ቀኖች» በምስጢር የሚታይ ሮማውያንን የሚያሸንፍ ለ፵ ዓመታትም ይሁዳን የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል የሚል ትንቢት ስላወቀ ነው። በዚህ ዘመን የመሲህ ጊዜያዊ ምስጢራዊ መንግሥት ለ፵ ዓመት ሳይሆን ፩ ሺህ ዓመት ይሆናል የሚያስተምሩ ሰዎች ሲነሡ አኪቫ ግን ለ፵ ዓመታት ይነበያል ብሎ እንዳስተካከላቸው በተልሙድ ይጻፋል።