ኡሩካጊና
Appearance
ኡሩካጊና (ሱመርኛ፦ 𒌷𒅗𒄀𒈾፤ ወይም ኡሩ-ኢኒም-ጊና? 2102-2095 ዓክልበ. ገደማ የነገሠ) በሱመር ውስጥ የላጋሽ ከተማ ገዢ ንጉስ ነበረ። የሉጋላንዳ መረን ግዛት በወደቀ ጊዜ፣ ኡሩካጊና በላጋሽ ንጉስ ሆነ።
ኡሩካጊና ያዋጀው ሕገ ፍትሕ (2098 ዓክልበ. ግ.) በታሪካዊ መዝገብ እስከምናውቀው ድረስ መጀመርያው የሕገ መንግሥት ሰነድ ነው። ሰነዱ እራሱ ገና አልተገኘም፤ ነገር ግን ለዜጎቹ አንዳንድ መብት እንደ ፈቀደላቸው ይታወቃል። ለምሳሌ ለመበለትና ለደሀ አደጎች ቀረጥ እንዳስቀረላቸው ድሆችንም ከሃብታሞች አራጣ እንደጠበቃቸው ይታወቃል። ከተማውም ለሞተ ሰው መቃብር ወጪውን ለመክፈል ተገደደ።[1] በተጨማሪ 1 ሚስት ቀድሞ ብዙ ባሎችን የምታገባበትን ልማድ (አእኑስያ ጋብቻን) ከለከለ።
አልፎ አልፎ ኡሩካጊና ከጎረቤት ከተሞቹ ጋር ተዋግቶ በመጨረሻ ግን ለኡሩክ ድል ሆነ። በዚህ ወቅት (2095 ዓክልበ. ግ.) ኡሩክ፣ ላጋሽና ሌሎቹ ከተሞች ሁሉ ለኡማ ገዢ ለሉጋል-ዛገ-ሲ ግዛት ተጨመሩ፤ ይህም በሱመር ሁሉ የገዛ መንግሥት ሆነ።
- «ቀድሞ ከጥንት ቡቃያዎች ጀምሮ የመርከብ ኃላፊ መርከብን ይወስድ ነበር፤ የመንጋ ኃላፊ አህያን ይወስድ ነበር፤ የመንጋ ኃላፊ በግን ይወስድ ነበር፤ የአሣ ኃላፊ አሣን ይወስድ ነበር። በአምባር ሠፈር ቄሶቹ የገብስ ቀለብ ይመዝኑ ነበር፤ የሱፍ እረኞች ለነጭ በግ በብር ይከፍሉ ነበር፤ የመሬት ቀያሽ፣ የአዝማሪዎች አለቃ፣ አስተዳዳሪ፣ ጠማቂና ካቦዎች ሁሉ፣ ለመሥዋዕት ጠቦት በብር ይከፍሉ ነበር። የአማልክት በሬዎች የገዢውን ነጭ ሽንኩርት እርሻ ያርሱ ነበር፤ የገዢውም ሽንኩርትና ኪያር በአማልክት እርሻ ይገኝ ነበር። ምርት የሆኑት አህዮችና በሬዎች ለቤተ መቅደስ አስተዳዳሪዎች ይታሥሩ ነበር፤ የገዢው ቅጥረኞች ግን የቤተ መቅደስ አስተዳዳሪዎች ገብስ ነበራቸው፤ የቤተ መቅደስ አስተዳዳሪዎችም ይገብሩ ነበር። አስተዳዳሪው በተራ ሰው እርሻ ላይ ዛፍ ሊያቋርጥ ወይም ፍሬውን ሊወስድ ይችል ነበር። ሬሳ በመቃብር ሲገባ፣ የመቃብር አለቃ ለራሱ 7 ጋን ቢራ፣ 420 ዳቦዎች፣ ግማሽ ጉር [3 ሊተር ያህል] ገብስ፣ አንድ የሱፍ ልብስ፣ አንድ ፍየልና አንድ አልጋ ይወስድ ነበር፤ አገልጋዩም አንድ ሩብ ጉር ገብስ ይወስድ ነበር። ... ባለ እጅ ጥበበኛም ለዳቦ ለምኖ በእጁ ይቀብለው ነበር፤ የሠራተኞች ጥንድ የከተማ በር ኬላ ግብር ለራሳቸው ይወስዱ ነበር። የገዢው መኖርያ በገዢው እርሻ፣ የሴቶችም መኖርያ በነርስዋ እርሻ፣ የልጆቹም መኖርያዎች በርሾቻቸው ሁላቸው አጠገብ አጠገብ ይገኙ ነበር። ከጠረፎቹ እስከ ባሕሩ ድረስ ባለሥልጣናት ይገኙ ነበር። የቀድሞ አስተዳደር እንዲህ ነበር።
- «ጣኦቱ ኒንጊርሱ ከአዕላፍ ሰዎች ለቅሞ የላጋሽ ገዢነቱን ለኡሩካግና በሰጠበት ጊዜ፣ ጥንታዊ ልማዶቹን ቀየረ። የመርከብ ኃላፊውን ከመርከቦች አስወገደ፤ የመንጋ ኃላፊውንም ከአህዮችና ከበጎች አስወገደ፤ የአሣ ኃላፊውንም ከአሦች አስወገደ። የእህል ቤት ኃላፊውን ከቄሶች ገብስ ቀለብ አስወገደ። ባለሥልጣናትን ከነጭ በግና ከመሥዋዕት ጠቦት ብር ክፍያ አስወገደ፤ የቤተ መቅደስ አስተዳዳሪዎቹንም ግብር የሚቀበለው ባለሥልጣን አስወገደ። የገዢው፣ የሴቶችም፣ የልጆቹም መኖርያዎችና እርሾች ለጣኦታት ተመለሱ። ማንም ከጠረፎች እስከ ባሕር ድረስ ባለሥልጣን አይሆንም። ሬሳ ወደ መቃብር ለማስገባት፣ የመቃብር አለቃ 3 ጋን ቢራ፣ 80 ዳቦዎች፣ አንድ አልጋና አንድ ፍየል ይወስዳል፤ አገልጋዩም 1/8 ጉር ገብስ ይወስዳል። በጣኦቱ ዱር ውስጥ ቢሆን የመቃብር አለቃ 4 ጋን ቢራ፣ 240 ዳቦዎችና አንድ ሩብ ጉር ገብስ ይወስዳል፤ አገልጋዩም 1/8 ጉር ገብስ ይወስዳል። ሴት ቄስዮዋም አንድ የሴት ጥምጥምና መልካም ሽቶ ትወስዳለች። የጊርሱ አዝማሪዎች ቀለብ 420 ዳቦዎች ለአቀራረቡ፣ 40 ሙቅ ዳቦዎች ለመብላት፣ 10 ሙቅ ዳቦዎች ለገበታው፣ 5 ዳቦዎች ለአለቆች፣ ሁለት ማሰሮና አንድ ጋን ቢራ ይሆናል። የላጋሽ አዝማሪዎች ቀለብ 490 ዳቦዎች፣ 2 ማሰሮና 1 ጋን ቢራ ይሆናል። የሌሎች አዝማሪዎች ቀለብ 406 ዳቦዎች፣ 1 ማሰሮና 1 ጋን ቢራ ይሆናል፤ የሽማግሌዎች ቀለብ 250 ዳቦዎች፣ 1 ማሰሮ ቢራ ይሆናል፤ የጣኦት ሽማግሌዎች ቀለብ 180 ዳቦዎች፣ 1 ማሰሮ ቢራ ይሆናል። ለዕውሩ አገልጋይ አንድ ለመብላት፣ 5 ለዳቦ፣ [...] 1 ለእኩለ ቀን ዳቦ፣ 6 ለእኩለ ሌሊት ዳቦ። የጣኦታት ሐውልቶች ኃላፊ ቀለብ 60 ዳቦዎች፣ 1 ማሰሮ ቢራና 1/4 ጉር ገብስ ይሆናል። የከተማ በር ኬላ ግብር ለሠራተኞች ጥንድ ተሠረዘ። የቤተ መቅደስ አስተዳዳሪዎች በተራ ሰው እርሻ ላይ አይዘርፉም። ጥሩ አህያ ለአገልጋይ ቢወለድ፣ ጌታውም፦ «ካንተ እገዛለሁ» ቢለው፣ አገልጋዩም መልሶ «የምፈልገውን ብር ዋጋ ብትከፍለኝ» ቢለው፣ ካልገዛው በቁጣ አገልጋዩን አይመታም። የአገልጋይ ቤት ከጌታው ቤት አጠገብ ከሆነ፣ ጌታውም፦ «ካንተ እገዛለሁ» ቢለው፣ አገልጋዩም መልሶ «የምፈልገውን ብርና ገብስ ዋጋ ብትከፍለኝ» ቢለው፣ ካልገዛው በቁጣ አገልጋዩን አይመታም። እንዲህ አዋጀ ኡሩካግና። የላጋሽን ዜጎች ከዕዳ አወጣ፤ ወይም [...] በስርቆት ወይም በግዲያ ሲከሰሱ ወይም [...] ለዚህም ጉዳይ መፍትሄ መሠረተ። ድሃ አደግና ባልዋ ያረፈባት ለኃይለኞቹ አልተሰጡም። ...»
- ሰነዱ በሱመርኛና እንግሊዝኛ Archived ሜይ 26, 2017 at the Wayback Machine
ቀዳሚው ሉጋላንዳ |
የላጋሽ ኤንሲ 2102-2095 ዓክልበ. ግድም |
ተከታይ (ላጋሽ በሉጋል-ዛገሲ ተያዘ) |
- ^ "The Reforms of Urukagina". History-world.org. Archived from the original on 2011-08-09. በ2009-02-17 የተወሰደ.
- የኡሩካጊና መሻሻሎች ሰነድ (በሱመርኛ) A Archived ፌብሩዌሪ 12, 2012 at the Wayback Machine, B Archived ፌብሩዌሪ 12, 2012 at the Wayback Machine, C Archived ፌብሩዌሪ 12, 2012 at the Wayback Machine
- A partial translation in English Archived ኦገስት 9, 2011 at the Wayback Machine
- "Inscriptions from the Ancient Near East" - includes a complete translation of the reform document and the lament in Italian Archived ኦክቶበር 30, 2008 at the Wayback Machine