እንቆቅልሽ

ከውክፔዲያ
ለፊልሙ፣ እንቆቅልሽ (ፊልም) ይዩ።

እንቆቅልሽ፣ የአነጋገር ዘይቤና ፍቺ እንቆቅልሽ የምንጫወተው አካባቢን ለመመርመር ለማጥናት በነገሮች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት እና ልዩነት የምንፈትሽበት ባህላዊ የማስተማርያ ዘዴ ነው፣ ይሉናል ምሁራን።

እንቆቅልሽ ተጫዋቾች ከአራቱ የቋንቋ ክህሎቶች መካከል፣ የመናገር እና የማዳመጥን ችሎታቸውን በርግጥ ያዳብራሉ። እንቆቅልሾቻችን በተለይ ነባር የሆነውን ባህላችንን የመግለጽ ሁኔታም ይታይባቸዋል። ይህ ማለት ግን ሰዎች በአካባቢያቸው ያለውን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በእንቆቅልሽ መልክ አይጠቀሙባቸውም ማለት አይደለም። እንቆቅልሽ በአገራችን በተለይ ለህጻናቱ እውቀትን ለመገብየት የቋንቋ ችሎታን ለማዳበር ማህበራዊ ግንኘትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። ለምሳሌ እንቆቅልሽ የሚጫወቱ ሰዎች እንቆቅልሽ ሲጠይቁ ህግና ስርአትን አክብረው ነው። እንደ የህብረተሰቡ እምነትም ጨዋታው የተለያየ ስርአት እና ደንብ አለው። በአገራችን በተረት ውስጥ በሃሳብ ስንዝሮ ብለን የምናውቀው አይነት ምስል ጀርመናውያንም በባህላቸው ዛንድ ማን በሚል መጠርያ በጣም አጭር እና ረዘም ያለ ሪዝ ያንጠለጠለ ምስል እንዳላቸው በተለይ በህጻናት ዘንድ ታዋቂ እንደሆነ እና ባለፉት ሶስት ሳምንት ግድም ሃምሳኛ አመቱ እንደተከበረለት ባለፈው ሳምንት ዝግጅታችን አውስተን ነበር። ይህንኑ በማስታከክ በአገራችን በተለይ ስላለው ዘይቤያዊ አነጋገር ተረት እና እንቆቅልሽ ከምሁራን ጋር ያደረግነው ውይይት ዛሪም ይቀጥላል። እንቆቅልሽ የምንጫወተው አካባቢን ለመመርመር አካባቢን ለማጥናት በነገሮች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት እና ልዩነት የምንፈትሽበት ባህዊ የማስጠማርያ ዘዴ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በቋንቋ ጥናት ተቋም መምህር የሆኑት አቶ መስፍን መሰለ አንድ እንቆቅልሽ ልጠይቅሽ ሲሉ ቃለ ምልልሳቸውን ይጀምራሉ። «ላዩ በድን ታቹ በድን መሃሉ ነፍስ አድን የሆነ ነገር ምንድ ነው? ብለን ስንጠይቅ ላዩ በድን የሆነ ነገር ታቹ በድን የሆነ ነገር ምንድን ነው ብለን እንመረምራለን» እዚህ ላይ ታድያ ይላሉ መምህር መስፍን «የነገሮችን ልዩነት ተመሳሳይነት እንፈትሻለን እናወጣለን እናወርዳለን፣ ታድያ ስናስብ የማስታወስ ችሎታችን ይዳብራል የቋንቋ ችሎታ ይዳብራል እናም ታቹ በድን ላዩ በድን ነፍስ የሚያድነው መሃል ያለው ነገር ምንድ ነው ብለን ስንጠይቅ ታቹ በድን ምጣድ ነው ላዩ በድን አክንባሎ ሲሆን ነፍስ የሚያድነው ደግሞ እንጀራ ሆኖ እናገኘዋለን» ሲሉ ያስረዳሉ። እኔም ልጠይቅ በተራዩ! እንቆቅልህ ምን አውቅልህ - ዙርያው ዘንዶ ማህሉ ብርንዶ ምንድ ነው? እወቁልኝ! ዙርው ዘንዶ ማለት እንደ ዘንዶ ተጠቅልሎ የተኛው፣ የምድጃ ከተር ሲሆን፣ መሃሉ ብርንዶ፣ እንደ ብርንዶ ስጋ የቀላው ደግሞ ፍም ነው። አብዛኞቹ እንቆቅልሾቻችን እና ወጎቻችን በግጥም መልክ የሚቀርቡ ሲሆን ዘዩ ጠቀስም ናቸው። ታድያ ፍቻቸውን ለማወቅ ባህሉን የህብረተሰቡን አኗር ጠንቅቀን ማወቅ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ይላሉ መምህር መስፍን መሰለ በመቀጠል «ጉድ መጣ ጉድ መጣ ከምድር ውስጥ ልቃቂት ወጣ!» ተብሎ ሲጠየቅ ጉድ መጣ ጉድ መጣ ከምድር ውስጥ ልቃቂት ወጣ የሚለው ግጥም መሰል ወይም ዜማ የመፍጠር ሁኔታ ይታይበታል። እናም እወቅልኝ ሲል ይጠይቃል፣ በዜማ፣ ከምድር የሚወጣ በቅርጽም በቀለምም ልቃቂት የሚመስል ነገር ምንድን ነው፣ ብለን ስንመረምር፣ በባህላችን በአካባቢያችን የምናውቀው ነገር ነጭ ሽንኩርት ሆኖ እናገኘዋለን» መምህር መስፍን በመቀጠል እንቆቅልሽ አሉ ምን አውቅልህ አልኻቸው «ወድቆ የማይሰበር ሞቶ የማይቀበር አባቴ የሰጠኝ ወንበር ምንድን ነው እወቂልኝ!» ወድቆ የማይሰበር ሞቶ የማይቀበር ነገር ስም ነው በዘይቤም አነጋገር በአገራችን ስም ከመቃብር በላይ ይውላል የሚባል ነገር አለ» ሲሉ በመቀጠል ያስረዳሉ። እንቆቅልሽ በአገራችን በተለይ ለህጻናቱ እውቀትን ለመገብየት የቋንቋ ችሎታን ለማዳበር ማህበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ያገለግላል። ለምሳሌ እንቆቅልሽ የሚጫወቱ ሰዎች እንቆቅልሽ ሲጠይቁ ህግና ስርአትን አክብረው ነው። እንደ የህብረተሰቡ የተለያየ ስርአት አለው። በእንቆቅልሽ ጨዋታ ጊዜ መጠነኛ የሆነ ስድብም አለ። ስድቡ ተጠያቂው መልስ ባለማወቁ ምክንያት ተሸናፊ ነው። ጠያቂው ደግሞ ተጠያቂው የማይመልሰውን ጥያቄ በማቅረቡ አሸናፊ ነው። አሸናፊው የበላይነቱን ለማሳየትም አገር ስጠኝ ይላል። ተሸናፊው አገር ይሰጠዋል፣ አልበቃኝም አነሰኝ ካለ ይጨምርለታል፣ አይ ይህም አልበቃኝም፣ የጸሃይ መውጫን፣ ምስራቅ ስጠኝ ብሎ ሊያዝም ይችላል። ለምሳሌ ተሸናፊው ጎንደርን ከሰጠ አሸናፊው እሺ ጎንደርን እወስዳለሁ ካለ እንዲህ በማለት የስድም ናዳውን ማውረድ ይጀምራል። «ጎንደር ላይ ተቀምጬ፣ ሁሉ በጄ ሁሉ በደጄ፣ እኔ በሰጋር በቅሎ ተቀምጬ፣ አንተ አሽከሪን በገጣባ አህያ አስቀምጬ፣ አይነት አይነቱን ለነፍሴ፣ ግርድፍ ግርድፉን ለፈረሴ፣


በኔ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆር፣ በአንተ ጉሮሮ አጥንት ይሰንቀር» እያለ የመርገም እና የስድም ናዳ ይደረድራል። ስድቡ ካልበቃውም ይቀጥላል፣ እንደ ሰፊድ ይለምጥህ፣ እንደ ደጋን ያጉብጥህ፣ በመጨረሻ ይህን ሁሉ የስድብ ናዳ ተሸናፊው ላይ ካወረደበት በኻላ፣ በል ጨርሴ እንዳልሰድብህ ሲመሽ አሳዳሪዪ፣ ሲቸግር አበዳሪዩ፤ በማለት የማለዘብያ ነገር ያመጣለታል። ታድያ እንዲህ አይነቱ የስድብም ሆነ የርግማን ሁኔታ ሲኖር፣ በባህሉ ጨዋታ ክቡር ነው፣ የሚለውን ነገር ይገልጻል። ተጫዋቾች ቢሰደቡም፣ ቢረገምም በጨዋታው ሂደት ተቀብሎ ዝም ነው እንጂ፣ ምንም ነገር አይልም። ባይሆን ተሸናፊው ከቻለ ሌላ እንቆቅልሽ አምጥቶ አሸናፊ ሆኖ አገር ስጠኝ የሚልበትን፣ እርግማን ሊያወርድ የሚችልበትን ሁኔታ ሲፈልግ ይታያል። በዚህም ታድያ የእንቆቅልሽ ተጫዋቾች ከአራቱ የቋንቋ ክህሎቶች መካከል የመናገር እና የማዳመጥን ችሎታ በርግጥ ያዳብራሉ። እንቆቅልሾቻችን ነባር የሆነውን ባህላችንን የመግለጽ ሁኔታ ይታይባቸዋል። ይህ ማለት ግን ሰዎች በአካባቢያቸው ያለውን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በእንቆቅልሽ መልክ አይጠቀሙባቸውም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ከዘመናዊው እንቆቅልሽ «እግር የላትም ትራመዳለች፣ አፍ የላትም ትናገራለች» እወቅልኝ! ይህንን ጠይቄ የዛሪውን መረሃ ግብሪን ልደምድም። እግር የላትም ትሄዳለች፣ አፍ የላትም ትናገራለች፣ ሰአት ናት!