መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል

ከውክፔዲያ
(ከዕዝራ ሱቱኤል የተዛወረ)

መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤልኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተከርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ከብሉይ መጻሕፍት የሚፈረጅ ነው። መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል ከዲዩተሮካኖኒካል መጻሕፍት ተቆጥሮ የዕዝራ (ሱቱኤል) ትንቢት ነው።

ትርጉም[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የተጻፈው በዕብራይስጥ ወይም በአራማያ ሲሆን በኋላ (250 አክልበ.) ከ70 ሊቃውንት ብሉይ ኪዳን ጋር ወደ ግሪክ ተተረጎመ፤ ከዚሁም ግሪክ ወደ ሮማይስጥ። እንዲሁም የግዕዝ ትርጉም ከዕብራይስጡ ተሠራ። ከክርስቶስ ስቅለት ውዲህ ግን የአይሁድ ጉባኤ መጽሐፉን ስለ ከለከለው፣ የዕብራይስጥና የግሪክ ትርጉሞች በፍጹም ጠፍተዋል። መጽሐፉ ዛሬው የሚታወቀው ከሮማይስጥ፣ ከግዕዝ፣ ከሶርያ ቋንቋ (ከጥንቱ አራማያ የሚለይ)፣ ከአረብኛና ከአርሜንኛ ትርጉሞች ብቻ ነው።

ይዘት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሚያዩት ገጽ ላይ ወይም እዚህ ላይ [1] በመጫን የመጽሐፉን ገጾች ማንበብ ይችላላሉ

የመጽሐፉ ይዘት እንዲሁ ነው፦

  • ምዕ. 1፦ ዕዝራ በባቢሎን ምርኮ ላይ አዝኖ ወደ እግዚአብሔር ሲጸለይ፣ ስለ አዳምኖኅአብርሃምዘጸአትዳዊትና የምርኮው ታሪክ ይተርካል። ባቢሎን በዕውኑ ከጽዮን ይልቅ እንደ ጸደቀች እግዚአብሔርን ይጠይቀዋል፤ ጽዮንን በባቢሎን ስለሚቀጣት፣ ጽዮንም ስትሠቃይ ባቢሎንም ስትደሰት ነውና።
  • ምዕ. 2፦ መልአኩ ዑርኤል ዕዝራን መልስ ለመስጠት ይላካል። የእግዜርን ፍርድ ለማወቅ አይችልም ይለዋል። ከዚሁ ዓለም መጨረሻ ቀጥሎ በእግዜር መንግሥት ጽድቅ ዋጋውን የሚገኘው ይሆናል። እዝራ ይህ ሁሉ መቼ ይሆንን ቢጠይቀው ዑርኤል የሞቱት ጻድቃን ደግሞ ይህን ለማወቅ ፈልገው ቁጥራቸው ሳይሞላ ግን አይሆንም ብሎ መለሰለት። ለሙታን ትንሳኤ መጠበቁ ለእርግዝና መውለድን እንደ መጠበቅ ይመስላል ብሎ ጨመረለት።
  • ምዕ. 3፦ ዑርኤል የዓለሙን መጨረሻ ሁናቴና ትልልቆቹን ምልክቶች ለእዝራ ያስረዳዋል። ከዚህ በላይ ለመማር 7 ቀን መጾም አለበት። ከ7 ቀን በኋላ ዑርኤልን እንደገና ጠይቆት የእግዜር መንግሥት ቶሎ እንዲመጣ ሰዎች ሁሉ አንድላይ ለምን አልተፈጠሩም ይላል። መሬቲቱ የሰው ልጆች ሁሉ አንዴ መውለድ ከቶ አትችልም ብሎ ዑርኤል ይመልስለታል። እግዜር የሰው ልጅ ሆኖ ወደ ፍጥረቱ እንዴት እንደሚገባ መልአኩን ይጠይቀዋል።
  • ምዕ. 4፦ በዑርኤል አማካኝነት እግዜር እንደ ሰው ልጅ ዓለሙን ለመጎብኝት በፍጥረት መጀመርያ እንዳቀደው ይገልጽለታል። እዝራ የዚህን አለም መጨረሻ ከእግዜር መንግሥት መጀመርያ ምን ይለየዋል ቢጠይቅ፣ ያዕቆብኤሳው ቀጥሎ እንደ ወጣ ይከተላል የሚል መልስ ሰጠ። ስለዚያው ዘመን ሌላ ምልክት ሲጠይቀው፣ በመሬት መንቀጥቀጥና በታላቅ ድምጽ እግዚአብሔር በዓለም የኖሩትን የተነሡትን ሙታን ለመፍረድ በምጽአት መምጣቱን አዋጃ። ከዚህም የተሻለ ኑሮና ከፍተኛ ሥልጣኔ በእግዜር መንግስት ይከተላል። ዕዝራም እንደገና 7 ቀን ይጾማል።
  • ምዕ. 5፦ ዑርኤል ተመልሶ ጠባብ መግቢያዎች ያሉት ሀገር የሚለውን ምሳሌ ይነግረዋል። አዳም በገነት በደል ባደረገ ጊዜ፣ ወደ እግዜር መንግሥት የሚሔደው መንገድ ጠባብ ሆነ ይለዋል። እግዜርን የሚንቁት በገሐነም መጥፋታቸውን ይገልጻል፣ በጎ ሥራ የሚሠሩ ግን መንግሥት ይወርሳሉ። ኅሩያን ስለሚያውቁት ጊዜያዊ መሢሓዊ መንግሥት የሚለውንም ትምህርት ይገልጻል። መሢሓዊው ንጉሥ ከሞቱ በኋላ ሰው ሁሉ ይሞታል፤ ስው ሁሉ ከሞተ በኋላ ምድር ለ7 ቀን ዝም ትላለች። ከ7ቱም ቀን በኋላ፣ የሙታን ትንሳኤ፣ ዕለተ ደይን፣ ለክፋት መሪዎችም ቅጣት፣ ለጻድቃንም መንግሥተ ሠማያት፣ ሁሉም በየተራው ይዘረዝራሉ።
  • ምዕ. 6፦ ዕዝራ ነፍስ ከሰውነት ከተለየ በኋላ ምን ይሆናል ብሎ ይጠይቀዋል። ዑርኤልም መልሶ እስከ ትንሳዔ ድረስ ሲጠብቁ፣ የሙታን ነፍሳት ለክፉዎች ስቃይ ለጻድቃንም ሞገስ እንደሚቀበሉ የ7ቱን ሥርዓት ምስጢር ይገልጻል። በዕለተ ደይን እያንዳንዱ ግለሰብ የግል ፍርዱን ይቀበላል። ሆኖም በሕይወታቸው ገና ሳሉ ንሥሐ ከገቡ ሀጢአትን ማሸነፍ እንደሚቻላቸው ያስተምራል።
  • ምዕ. 7፦ ዕዝራ እግዚአብሔር ምሕረት እንዲያሳይ በለመነበት ጊዜ የእግዜር መልስ ሰው ሁሉ እንዲድን አይቻልም በማለት አስጠነቀቀው። ዘርን የሚዘራው ገበሬው ያለውን ምሳሌ ይነግረዋል። በእድሜያቸው እግዜርን ከቶ ስላልፈለጉት ስለ ሀጥአን ጥፋት እንዳይጨንቅበት እዝራን ይለዋል። ዕዝራ የእግዜር መንግሥት በመጨረሻ ዘመን መቅረቡን ስለሚያሳዩት ምልክቶች እንደገና ይጠይቃል።
  • ምዕ. 8፦ እግዜር ዕዝራን እንደሚለው፣ ያስተማራቸውን የመጨረሻ ዘመን ምልክቶችን ሰው መፈልግ አለበት። የዝንጉ ሰዎችና የታማኝ ሰዎች እድሎች ምስጢር ደግሞ ይናገራል። ከዚያ ዕዝራ ለ7 ቀን በምድረ በዳ ፍራፍሬን ብቻ እየበላ እንዲቆይ አዘዘው። ከ7ቱ ቀንም በኋላ፣ በልጇ ላይ እያለቀሰች አንዲትን ሴት ያገኛል።
  • ምዕ. 9፦ ዕዝራ ካለቀሰችው ሴት ጋር ለመወያየት ሲወድድ፣ ድንገት አገር ሆነችና መልአኩ ተመልሶ እርሷ በዚሁ አለም የእግዚአብሔር መንግሥት ሥር ምሳሌ ኢየሩሳሌም መሆኗን ይገልጽለታል።
ባለ ሦስት ራስ አሞራ ከዕዝራ ራዕይ
  • ምዕ. 10፣ 11፦ ነቢዩ ዳንኤል ቀድሞ እንዳየ ሁሉ፣ ዕዝራ የባቢሎን ተከታይ መንግሥታት መጨረሻ ሁናቴ የሚገልጽ ራዕይ ያያል። ነገር ግን ያልታወቁ አዛጋጆች አስተሳሰባቸውን ወደ ኢትዮጵያዊው ትርጉም አስገብተዋል። እነዚህ ምዕራፎች በሌሎቹ ልሳናት (ሮማይስጥ፣ ፅርዕ፤ ወዘተ.) ለጠፋው ዕብራይስጥ ቅጂ የተሻለውን ትርጉም እንዳላቸው ይሆናል። በቅንፍ ውስጥ ስለ አፊፋኖስ አንጥያኮስ የተጨመረው ቋንቋ መቸም አልተገኘበትም። አፊፋኖስ በ2ኛ መቶ ዘመን ዓክልበ. ስለ ኖረ እንጂ፤ ራዕዩ ግን በተለይ ስለዚሁ አለም መጨረሻ ጥፋት ዘመን ነው። ክርስቶስ ከአፊፋኖስ በኋላ ኖሮ የዳንኤል ራእይ ገና ወደፊት ነው በግልጽ ቢያስተምርም፣ አይሁዶች ግን ዳንኤል ስላለፈው አፊፋኖስ ትንቢት ተናገረ ብለው አስተማሩ። ይህ የአይሁዶች ትምህርት በቅንፉ ውስጥ መታየቱ ስንኳ ጥንታዊነቱን ይመስክራል። ቅንፉን ያስገባው የከስሙናይን ሥርወ መንግሥት ደጋፊ እንደ ነበር ይመስላል (11፡32 ይዩ)። የሚከተለው ከሮማይስጥ / ፅርዕ ትርጉሞች ይወሰዳል፦
በሕልሙ ሳለ፤ ዕዝራ ባለ ሦስት ራስ ንሥር ወይም አሞራ ያያል። 12 ታላላቅ ክንፎችም አሉበት። እነዚህም 12 ታላላቅ ክንፎች እያንዳንዱ በየተራው ይገዛሉ። 2ኛው ታላቅ ክንፍ ከሌሎቹ ሁሉ የረዘመው ዘመነ መንግሥት ይቀበላል። ከርሱም ዘመን በኋላ ድምጽ ከንሥር ሰውነት ይናግራል። «ከዚህ በኋላ የመጡት ክንፎች እንደዛኛው ክንፍ ብዙ ዘመኖች እንዳይቀበሉ፣ ያኛው ክንፍ ከተቀበሉት ዘመኖች ግማሽ ይልቅ አይበልጡ» ይጮሃል። ከዚያ በኋላ የተረፉት ታላላቅ ክንፎች እስከ 12ኛው ታላቅ ክንፍ ድረስ ዘመኖቻቸውን ይጨርሳሉ። በመካከላቸው ደግሞ፣ መንግሥት ሊወድቅ እንደሚል ቢመስልም፣ ሆኖም መንግሥት የዛኔ አይወድቅም።
ከ12ቱ ታላላቅ ክንፎች ቀጥሎ፣ 8 ትንንሽ ክንፎች ይነሣሉ። እነዚህ ሁሉ እስከ ንጉሥ ማዕረግ ድረስ አይደርሱም፤ አንዳንድ ምክትሎች ብቻ ናቸው። መጀመርያ ሁለት ከድንገት በዘመናቸው መካከል ይጠፋሉ። የሚከተሉ ሁለት ዘውድን በመጫን ፋንታ፡ ወደ ቀኝ ባለው ራስ ውስጥ መቆየት ይመርጣሉ። (እኚህ ሦስት ራሶች የንሥሩ መንግሥት ምንጮች ይባላሉ።) ከዚህ መንግሥታዊ ቀውስ የተነሣ፣ 4 ትንንሽ ክንፎች ይተርፋሉ። ከነዚህ አራት 1ኛው ትንሽ ክንፍ ለአጭር ዘመን ብቻ ይገዛል፤ 2ኛው ከዚያ ያነሰ እጅግ አጭር ዘመን ይቆያል። የተረፉት 2 ክንፎች ሊገዙ ሲሉ፤ ድንገት ከንሥሩ 3 ራሶች መካከለኛው ራስ ይነሣል፤ እርሱም ከሁሉ ጨካኝ የሆነ የአለም ንጉሥ ይሆናል። ከታላቁ መከራ አመታት በኋላ ግን በአልጋ ላይ ይሞታልና ወደ ቀኝ ራስ የሄዱት 2ቱ ትንንሽ ክንፎች የዛኔ ለጥቂት ዘመን ይገዛሉ። በነርሱ ዘመን ግን ብሔራዊ ጦርነት አለና አለም በእሳት ይጠፋል። በተጨማሪ አንበሳ (መሢኅ) ንሥሩን በፍጹም ይገስጻል።
  • ምዕ. 12፦ ሰባት ቀን ካለፉ በኋላ ዕዝራ በሌላ ራዕይ አንድ ሰው ከባሕር ሲወጣ ያያል። ሠራዊቶች ሊዋጉ ሲሉ፣ ሰውዬው ተራራን ፈጥሮ ይቀመጥበታልና እሳት ከአፉ እስትንፋሽ ወጥቶ ያጠፋቸዋል። ከዚያ በኋላ ሌላ ሕዝብ ወደርሱ በሰላም ይመጣል። ከዚያም መልዓኩ የራዕዩን ፍች ይሰጠዋል። ይህ ምዕራፍ በአማርኛ ዲዩትሮካኖን እንደገና ከለሎቹ ትርጉሞች (ከጽርዕ ወዘተ.) ይለያል። በሌሎቹ ትርጉሞች ዘንድ፣ ይህ ራዕይ ስለመሢሁ መጨረሻ ምጽአት መሆኑ ግልጽ ነው። የተራራውም ትርጉም ደብረ ጽዮን ወይም የእግዚአብሔር መንግሥት ይባላል። አገሮች ሁሉ በጦርነት ተይዘው ዝም ብሎ በተራራ ላይ ይታያልና ካሸነፋቸው በኋላ ምድርን ለዘላለም ይገዛል። የአማርኛ ትርጉም ግን እንደገና በሌላ አስተያየት ተዛባ፤ በዚያ ውስጥ ተራራ መስቀል ሆኗል፤ ራዕዩም ስለዚሁ አለም መጨረሻ ቀን ሳይሆን፣ ስለ ክርስቶስ ስቅለት የሚተነብይ ሆኗል።