የኡር-ናሙ ሕግጋት

ከውክፔዲያ
«ኡር-ናሙ የኡር ንጉሥ፤ ሐሽሐመር፣ የኢሽኩን-ሲን ኤንሲ፣ አገልጋዩ»

የኡር-ናሙ ሕገጋት እስከ ዛሬ ከተገኙት መንግሥታዊ ሕግ ሰነዶች መኃል ከሁሉ ጥንታዊ የሆነው ሰነድ ነው። ሰነዱ የተጻፈው ከክርስቶስ ልደት ከ1983 ዓመት በፊት (ኡልትራ አጭር) በሱመርኛ ቋንቋ ነበር። በመቅደሙ የኡር ንጉሥ ኡር-ናሙ ስም ቢጠቀስም አንዳንድ ሊቃውንት ግን ምናልባት የልጁ የሹልጊ ሥራ ይሆናል ብለው ያምናሉ።

መጀመርያ የተገኘው ቅጂ በተሰበረ ጽላት በኒፑር ፍርስራሽ ሲሆን፣ በ1944 ዓ.ም. ሊቅ ሳሙኤል ክሬመር አስተረጎሙት። ሆኖም ሰባራ ክፍሎች እንደ መሆኑ ከሕጎቹ ሁሉ 5ቱ ብቻ ሊታነቡ ይችሉ ነበር። ዳሩ ግን ሌሎች ቅጂዎች በኡርና በሲፓር ከተገኙ በኋላ አሁን ከ57 ድንጋጌዎች በጠቅላላ፣ 40 ያሕል ሊታወቁ ተቻለ።

የኡር-ናሙ ሕገጋት ከሃሙራቢ ሕጎች በ300 አመት አስቀደሙ። ሆኖም ሌሎች የሕገጋት ሰነዶች ከኡር-ናሙ ጊዜ በፊት በሱመር እንደ ኖሩ ይታወቃል። የላጋሽ ንጉሥ ኡሩካጊና የሕግ ማሻሻል እንዳወጣ የሚል ጽላት ተገኝቷልና።

በዚህ ሰነድ ሕጎቹ «አንድ ሰው እንዲህ ቢያደርግ፣ እንዲህ ይደረግ» በሚመስል አባባል ይጻፋሉ። ይህም ዘዴ ደግሞ በኋለኛ ሕገ መንግሥታት ይታያል። ከንጉሡ («ሉ-ጋል» ወይም ታላቅ ሰው) በታች፣ ከኅብረተሠቡ 2 አይነት ማእረግ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም፦ 1) «ሉ» ወይም ነጻ ሰው እና 2) «አራድ» (ባርያ) / «ጌሜ» (ገረድ) ናቸው። የ«ሉ» ወንድ ልጅ ሚስት እስከሚያገባ ድረስ «ዱሙ-ኒታ» ይባል ነበር። የሴት («ሙኑስ») ሁኔታ ከሴት ልጅ («ዱሙ-ሚ») ጀመሮ እስከ ሚስት («ዳም») ከዚያም ከባሏ እረፍት ብትኖር ኖሮ እስከ ጋለሞታ («ኑማሱ») ድረስ ይደርስ ነበር።

ደግሞ ይዩ፦ የሕገ መንግሥት ታሪክ

ይዞታ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የኡር-ናሙ ሕግጋት ያሉበት ጽላት በኢስታንቡል ሙዚየም

መቅደሙ እንደ ኋለኛ ሕገ መንግሥታት መቅደሞች ይመሳሰላል። ስለኡር-ናሙ መንግሥት አማልክቱን ካመሰገነ በኋላ በሰፊ ምድር ላይ የእኩልነት አዋጅ ያቀርባል።

ከታወቁት ህገጋት እነዚህ አሉ፦

1. አንድ ሰው ሌላውን ቢገድል፣ ሰውዬው ይሙት።
2. አንድ ሰው ቢሰርቅ፤ ሰውዬው ይገደል።
3. አንድ ሰው ሌላወን ቢሰርቅ (ማፈን)፣ ሰውዬው ይታሠር።
4. አንድ ባርያ ገረዲቱን ቢያገባ፣ ከዚያም ነጻነቱን ቢያገኝም፣ ከቤተሠቡ ግን አይወጣም።
5. አንድ ባርያ ነጻ ሴትን ቢያገባ፣ በኲሩ ለጌታው ይሰጥ።
6. አንድ ሰው የሌላውን ሚስት በግፍ ቢወስድ፣ ሰውዬው ይገደል።
7. የሰው ሚስት ሌላውን ሰው በማዳራት ብትወስድ፣ ሴቲቱ ትገደል፣ ወንዱ ግን ነጻ ነው።
8. አንድ ሰው የሌላውን ገረድ በግፍ ቢወስድ፣ ሰውዬው 5 ሰቅል (ብር) ይክፈል።
9. አንድ ሰው የመጀመርያ ጊዜ ሚስት ቢፈታ፣ አንድ ምናን (60 ሰቅል) ይክፈላት።
10. አንድ ሰው ጋለሞታን ቢፈታ፣ ግማሽ ምናን (30 ሰቅል) ይክፈላት።
11. አንድ ሰው ያለ ትዳር ውል ጋላሞታን ቢወስድ፣ ብር መክፈል የለበትም።
13. አንድ ሰው ጠንቋይ ነው ተብሎ ቢከሰስ፣ በወንዝ ውስጥ በመግባት ይፈረድ፤ የዋሕነቱ ከተረዳ ከሳሹ 3 ሰቅል ብር ይክፈለው።
14. አንድ ሰው የሌላውን ሚስት አመንዝራ ናት ብሎ ቢከስሳት፤ በወንዝ ውስጥ ገብታ የዋሕነቷ ከተረዳ ከሳሿ የምናን ሢሦ (20 ሰቅል) ይክፈላት።
15. የዕጩ አማች ወደ ዕጩ-አማቱ ቤት ገብቶ፣ አማቱ ግን ከዚያ ሴት ልጁን ወደ ሌላ አማች ቢሰጣት፣ አማቱ ለተጣለው ዕጩ 2 ዕጥፍ ማጫዋን ይመልሰው።
17. አንድ ባርያ ከከተማው ውጭ ቢያመልጥ፣ ከዚያም አንድ ሰው ቢመልሰው፣ ጌታው ለመለሠው ሰው 2 ሰቅል ይክፈለው።
18. አንድ ሰው የሌላውን ዓይን ቢያጠፋ፣ ግማሽ ምናን ይክፈለው።
19. አንድ ሰው የሌላውን እግር ቢቆርጥ፣ 10 ሰቅል ይክፈለው።
20. አንድ ሰው በግፍ የሌላውን አካል በዱላ ቢሰብር፣ አንድ ምናን ይክፈለው።
21. አንድ ሰው የሌላውን አፍንጫ በቢላዋ ቢቆርጥ፣ 2 ሢሶ ምናን (40 ሰቅል) ይክፈለው።
22. አንድ ሰው የሌላውን ጥርስ ቢሰብር፣ 2 ሰቅል ይክፈለው።
25. አንዲት ገረድ እመቤትዋን ብትሰድብ፣ አፏን በ1 ሊትር ጨው ትታጠብ።
28. አንድ ሰው ምስክር ቢሰጥ፣ ምስክሩም ሀሣዊ ቢሆን፣ 15 ሰቅል ይክፈል።
29. አንድ ሰው ምስክር ቢሰጥ፣ ከዚያም ቃሉን ቢሰርዝ፣ እሱ የክሱን ዋጋ ይክፈል።
30. አንድ ሰው የሌላውን እርሻ በስውር ቢያርስ፣ ይህ ግን አይቀበለምና ውጪው ይጠፋበታል።
31. አንድ ሰው የሌላውን እርሻ በውኃ ቢሞላ፣ ሦስት ኩር ገብስ ለአንድ ኢኩ እርሻ ይስጠው።
32. አንድ ሰው እርሻውን ለሌላው አከራይቶ ያው ሰው ግን ባያርሰው፣ ምድረ በዳም ቢያደርገው፣ ሦስት ኩር ገብስ ለአንድ ኢኩ እርሻ ይስጠው።