የኤሽኑና ሕግጋት
Appearance
የኤሽኑና ሕግጋት በሁለት ጽላቶች በ1937 እና 1939 ዓ.ም. በኢራቅ ተገኙ። ምናልባት 1775 ዓክልበ. አካባቢ እንደ ኤሽኑና ሕግ ፍትሕ ሆነው ወጡ፤ የትኛው ንጉሥ እንዳወጣቸው ግን እርግጥኛ አይደለም።
ከነዚህ ሕገጋት ብዙዎቹ የሐሙራቢ ሕግጋት (1704 ዓክልበ. ግድም) ይመስላሉ፤ እንዲሁም ብዙዎቹ በኦሪት ዘጸአት 21 እና 22 በሕገ ሙሴ (1661 ዓክልበ. ግድም) መልስ አገኙ። ሆኖም ከነዚህ ሕጎች መካከል ያላቸው ልዩነቶች ደግሞ ጥቂት አይደሉም።
ሌሎችም ሕግጋት ነበሩ፤ ነገር ግን ጽሑፊ በፍርስራሽ ሆኖ በሙሉ ሊነበብ አይቻልም። ከተረፉት ሕግጋት መሃል፦
- §1) ለአንድ ሰቀል (፱ ግራም ያህል) ብር መግዣው፦
- §2) 1 ሊተር የሰሊጥ ዘይት ለ30 ሊተር ገብስ መደበኛ ነው፤ 1 ሊተር ጮማ ለ25 ሊተር ገብስ፤ 1 ሊተር «የወንዝ ዘይት» ለ8 ሊተር ገብስ
- §3) የጋሪ ኪራይ ከነነጂው፣ ከነበሬው፦ 100 ሊተር ገብስ፣ ወይም 1/3 ሰቀል ብር፣ ለአንድ ቀን ይሆናል።
- §4) የመርከብ መጓጓዣ ኪራይ ለ1 ጉር ይዘት 2 ሊተር ገብስ ነው፤ <...> ሊተር የመርከበኛው ኪራይ ለአንድ ቀን ነው።
- §5) መርከበኛ ቸልተኛ ሆኖ መርከቡ ከሰመጠበት፣ የይዘቱን ዋጋ በሙሉ ይከፍላል።
- §6) ሰው አለግባብ የሌላውን ሰው መርከብ ከወሰደ፣ 10 ሰቀል ብር ይክፈል።
- §7) ምርቱን ያመረተው ዋጋ 20 ሊተር ገብስ፣ ወይም 12 ቅንጣት ብር (0.6 ግራም) ይሆናል።
- §8) ያመነሸው ዋጋ 10 ሊተር ገብስ ነው።
- §9) ሰው ለሠራተኛ ምርቱን ለማምረት ፩ ሰቀል ብር ከሰጠው፣ ሠራተኛው ግን ሥራውን ካልጨረሰው፣ በሠራተኛው ላይ የ10 ሰቀል ብር ቅጣት አለ።
- §9 ሀ) የማጭድ ኪራይ 15 ሊተር ገብስ ነው፣ ለባለቤቱም ይመልስ።
- §10) የአህያ ኪራይ 10 ሊተር ገብስ፣ የነጂውም ኪራይ 10 ሊተር ገብስ፣ ለአንድ ቀን ይሆናል።
- §11) የሠራተኛው ኪራይ (ደሞዝ) 1 ሰቀል ብር እና ለሥንቁ 60 ሊተር ገብስ ለአንድ ወር ይሆናል።
- §12) ማንኛውም ሰው በዜጋ እርሻ፣ በሰብሉ ከተያዘ፦ በመዓልት ከሆነ 10 ሰቀል ብር ይክፈል። በሌሊት በሰብሉ የተያዘው፣ ይሙት በቃ።
- §13) ማንኛውም ሰው በዜጋ ቤት ውስጥ ከተያዝ፦ በመዓልት ከሆነ 10 ሰቀል ብር ይክፈል። በሌሊት በቤቱ የተያዘው፣ ይሙት በቃ።
- §15) ነጋዴው ብር፣ ገብስ፣ ሱፍ ወይም የሰሊጥ ዘይት ከባርያ እጅ አይቀበለም።
- §17/18) የሰው ልጅ የሙሽሪት ማጫ ብር ለአማቱ ካመጣ፦
- §19) የሚከፍለው ሰው በአውድማ ይቀበል።
- §22) ሰው በሌላ ሰው ላይ ምንም የእዳ ነገር ሳይኖረው፣ ሆኖም የሌላውን ገረድ ከያዘ፣ የገረድ ጌታ በአምላክ ይማል፣ «አንተ በኔ ላይ ምንም ነገር የለህም»፤ ገረዱን የያዘው ሰው እንደ ገረዲቱ ዋጋ ይክፈል።
- §23/24) ሰው በሌላ ሰው ላይ ምንም የእዳ ነገር ሳይኖረው፣ ሆኖም የሌላውን ገረድ ከያዘ፣ በቤቱም እንድትሞት ካደረገ፣ እርሱ ለገረዲቱ ጌታ ፪ ገረዶች ይተካ።
- §25) ሰው በአማቱ ቤት ከታጨ፣ አማቱ ግን በድሎት ልጂቱን ለሌላ ከሰጠ፣ የልጅቱ አባት ፪ እጥፍ የማጫዋን ብር ይመልሳል።
- §26) ሰው ለሴት ልጅ የማጫዋን ብር ካመጣ፣ ሌላ ግን ያለ ወላጆች ፈቃድ በግድ ከያዛት፣ የሕይወት ጉዳይ ነው፤ ይሙት በቃ።
- §27) ሰው ወላጆቿን ሳይጠይቅ ሴት ልጃቸውን ከያዘ፦
- (ሀ) ከዚያም የሠርግ ሥነ ሥርዓትና ውል ካልፈጸመ፣ ለአንድ አመት ሙሉ እቤቱ ውስጥ ብትኖርም፣ «ሚስት» አትሆንም።
- (ለ) ከዚያም የሠርግ ሥነ ሥርዓትና ውል ከፈጸመ፣ «ሚስት» ነች። በሌላ ሰው ጭን ከተያዘች፣ ይሙት በቃ ጉዳይ ነው።
- §29) ሰው በጦርነት ጊዜ ከተማረከ፣ በሌላ አገር ለረጅም ጊዜ ከኖረ፣ ሌላ ሰው ደግሞ ሚስቱን አግብቶ ልጅ ከወለደችለት፣ ቢሆንም ሰውዬው በተመለሰበት ጊዜ ወደ ሚስቱ ሊመለስ ይችላል።
- §30) ሰው ከተማውን ከጠላ፣ ከሸሸ፣ ሌላ ሰው ደግሞ ሚስቱን ከወሰደ፣ ሰውዬው በተመለሰበት ጊዜ ምንም ይግባኝ ማለት የለውም።
- §31) ሰው የሌላውን ሰው ገረድ በወሲብ ከያዘ፣ 1/3 ምና (20 ሰቀል ወይም 180 ግራም) ብር ይክፈል፤ ገረዲቱም የጌታዋ ሆና ትቅር።
- §32) ሰው ልጁን ለአሳዳጊነት ከሰጠ፣ ለሦስት ዓመት ስንቅ በቂ ምግብ፣ ዘይትና ልብስ ካላቀረበለት፣ 10 ምና ለልጁ አሳዳጊነት ይክፈል፣ ልጁም ለርሱ ይመልሳል።
- §33) ገረድ ያለ ሕግ ልጇን ለሌላ ሴት ልጅ አሳዳጊነት ከሰጠችው፣ እሱም አድጎ ጌታው ካወቀው፣ ጌታው ይዞት ሊውሰደው ይችላል።
- §36/37) ሰው ንብረቱ እንዲጠበቅ አደራ ቢያኖር፣ አደራ ያለው ባልንጀራ ማንም ሌባ እቤቱ ሳይገባ ንብረቱ እንዲጠፋ ካደረገ፣ ባልንጀራው ንብረቱን ለሰውዬው ይተካል። ከቤቱም ቢሰረቅ፣ የባለቤት ማጣት ነው፣ ባለቤቱ በቤተ መቅደስ ለሰውዬው በአምላክ ይማል፦ «የኔና ያንተ ንብረት አንድላይ ጠፍተዋል፣ እኔ አልከፋሁም አልበደልኩም።» ይማልና ምንም ዕዳ አይሆንበትም።
- §39) ሰው ድሃ ሆኖ ቤቱን ከሸጠ፤ ገዢው በፈቃዱ በሚሸጥበት ቀን ባለቤቱ ሊገዛው ይችላል።
- §40) ማንም ሰው ባርያ፣ ገረድ፣ በሬ፣ ወይም ሸቀጥ ከገዛ፣ ለማናቸውም ዋጋ፣ ማን እንደ ሸጠው ሊያስረዳ ካልቻለ እርሱ እራሱ ሌባው ነው።
- §42) ሰው የሌላውን አፍንጫ ከቈረጠ፣ ፩ ምናን ይክፈል፤ ለዓይን፦ ፩ ምና፤ ለጥርስ፦ 1/2 ምና (፴ ሰቀል)፤ ለዦሮ - 1/2 ምና። ለጥፊ፦ 10 ሰቀል ብር ይክፈል።
- §43) ሰው የሌላውን ጣት ከቈረጠ፣ 2/3 ምና ይክፈል።
- §44/45) ሰው ሌላውን በጠብ ወደ ምድር ጥሎት እጁን ከሰበረ፣ 1/2 ምና ብር ይክፈል። እግሩን ከሰበረ፣ 1/2 ምና ይክፈል።
- §46) ሰው ሌላውን ከመታ ክሳዱን አጥንት ከሰበረ፣ 2/3 ምና ብር ይክፈል።
- §47) ሰው ሌላውን በጠብ ከጎዳው፣ 10 ሰቀል ብር ይክፈል።
- §47A) ሰው በጠብ የሌላ ሰው ልጅ መሞት ካደረገበት፣ 2/3 ምና ብር ይክፈል።
- §49) ሰው ከተሰረቀ ባርያ ጋር፣ ከተሰረቀች ገረድ ጋር ከተገኘ፣ ባርያ ለባርያ፣ ገረድ ለገረድ መተካት አለበት።:
- §50) ማንም ሹም ከዜጋ የሸሸውን ባርያ፣ የሸሸችውን ገረድ፣ የባዘነውን በሬ ወይም አህያ ወደ ኤሽኑና ካላመጣው ወይም ካላመጣት፣ በቤቱም ውስጥ ከጠበቀው፣ ከአንድ ወር በላይ ካለፈ፣ ቤተ መንግሥት በስርቆት ይከሰዋል።
- §51) የባርነት ምልክት ያለበት የኤሽኑና ባርያ ወይም ገረድ ከኤሽኑና በር ያለ ጌታቸው አይወጡም።
- §52) የመንገደኛ ባርያ ወይም ገረድ ወደ ኤሽኑና በር ገብቶ የባርነት ምልክት ይቀበላል፣ በጌታውም አደራ ይቆያል።
- §53) በሬ ወግቶ በሬን ከገደለ፣ ሁለቱ ባለቤቶች የደኅናውን በሬ ዋጋና የሞተውን በሬ ሬሳ በትክክል ይካፈሉ።
- §54/55) በሬ ተዋጊ ከሆነ፣ ኃላፊውም ለባለቤቱ ቢመሰክርለት፣ እሱ ግን በሬውን ባይጠብቀው፣ ሰውንም ቢገድል፣ የበሬው ባለቤት 2/3 ምና ብር ይክፈል። ባርያን ወግቶ ቢገድል፦ 15 ሰቀል ብር ይክፈል።
- §56/57) ውሻ ተዋጊ ከሆነ፣ ኃላፊውም ለባለቤቱ ቢመሰክርለት፣ እሱ ግን ውሻውን ባይጠብቀው፣ ሰውንም ቢገድል፣ የውሻው ባለቤት 2/3 ምና ብር ይክፈል። ባርያን ወግቶ ቢገድል፦ 15 ሰቀል ብር ይክፈል።
- §58) ግድግዳ ሊወድቅ ቢል፣ ኃላፊው ለባለቤቱ ቢመሰክለት፣ እሱ ግን ግድግዳውን ካልጠነከረ፣ ግድግዳውም ወድቆ የሰውን ልጅ ከገደለ፦ የሕይወት ጉዳይ ነው፤ በንጉሥ ድንጋጌ ነው።