ሕገ ሙሴ

ከውክፔዲያ

ሕገ ሙሴብሉይ ኪዳን ዘንድ ከአስርቱ ቃላት ቀጥሎ ከኦሪት ዘጸአት ፳፩ ጀምሮ የሚገኝ እግዚአብሔርደብረ ሲናሙሴ የገለጸው ሕግ ነው።

እስራኤል ልጆች በዘፈንና በወርቃማ ላም ጣኦት ከተገኙ በኋላ፣ ያህዌ የከበደ ሕግ ሰጣቸው። የሕዝቡ ዘር ለተነበዩ በረከቶች እንዲዘጋጅ፣ ለሙሴ ዘመን የተመጣጠነ ሕግ እንዲሆን፣ የሰው ልጆችን በመቸኰል ሳይሆን በመታገሥ ወደ ሥልጣኔ እንዲያስለምዳቸው፣ ከጎረቤቶቹ ከመስጴጦምያ አገሮች ሕግጋት የተሻሸሉ ብያኔዎች እንደ ወሰነ ሊታይ ይቻላል። ከሕገ ሙሴ (ምናልባት 1661 ዓክልበ. የተገለጠ) አስቀድሞ ከወጡት ሕገጋት በተለይ ተመሳሳይ ኹኔታዎች የቆጠሩት የኡር-ናሙ ሕግጋት (1983 ዓክልበ.)፣ የሊፒት-እሽታር ሕግጋት (1832 ዓክልበ.)፣ የኤሽኑና ሕግጋት (1775 ዓክልበ. ግድም) እና የሃሙራቢ ሕግጋት (1704 ዓክልበ.) ይታወቃሉ።

በታሪካዊ ልማዶች ዘንድ፣ የአክሱም መንግሥት ግማሽ ከ950 ዓክልበ. ግድም እስከ 317 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በሕገ ሙሴ ሥር ነበረች። እንዲሁም በአይሁድ መንግሥታት ለምሳሌ የስሜን መንግሥት (317-1619 ዓም) እና ኻዛሪያ (ከ732-1008 ዓም ግድም) ተገኘ።

ትንቢተ ሚክያስ 6:8 መሠረት በሕጉ በድምሩ አስፈላጊ የሆኑት ፫ ጽንሰ ሀሣቦች ፍርድ፣ ምኅረትና ትሕትና ናቸው።

ወደ ፊትም ከሕገ ሙሴ መሠረት ሕገ ወንጌልና በሕገ ወንጌል የተመሠረቱ ሕግጋት (ለምሳሌ እንደ ፍትሐ ነገሥት) ተደረጁ። በኢየሱስ ትምህርት፣ ከሁሉ ትልቁ ሕግ ኦሪት ዘዳግም ፮፡፭ «አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ» የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ትልቁ ኦሪት ዘሌዋውያን ፲፱፡፲፰ «ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ» ነው። አለበለዚያ በሃዋርያት ሥራ ፲፭፡፳፱ ዘንድ፣ ከሕገ ሙሴ ለክርስቲያናት አጥብቀው መጠበቅ ያሉባቸው ደንቦች (ቅጣቶቹም ባይሆኑም) «ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከተናቀም (ከመብላት)፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ» የሚሉት ናቸው። የተረፉት የአይሁዶች ሕግጋት ግን ለማጥናትና ለማወቅ ለብዙ ክርስቲያናት ቁም ነገሮች ናቸው።

ተጽእኖ በሌሎች ሕግጋት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሕገ ሙሴ በነዚህ ኋለኞች ሕግጋት በሰፊ እንደ መሠረት ተጠቀሱ። መሠረት ማለት ስለ ተመሳሳይ ኹኔታዎች የሚቀምሩ ተጨማሪ ድንጋጌዎች በነዚህ ሕግጋት ሌሎች ክፍሎች ውስጥ ደግሞ ሊገኙ ይችላሉ።

ዶም ቦክ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በ885 ዓም የእንግላንድ ንጉሥ ታላቁ አልፍሬድ ባዘጋጁት ዶም ቦክ (ሕገ ፍትሕ)፣ አንቀጾች 1-10 ከአስርቱ ቃላት የተወሰዱ ሲሆን፣ አንቀጾች 11-48 ከሕገ ሙሴ በኦሪት ዘጸአት (ከአንዳንድ ጥቃቅን ለውጦች ጋራ) በሰፊ እንደ መሠረት ይጠቅሳል።

ዘጸአትም ምዕራፍ 21 በሙሉ፣ ምዕራፍ 22 በሙሉ (22:30 ብቻ ቀርቶ)፣ እና ምዕራፍ 23:1-9፣ 23:13 በጥንታዊ እንግሊዝኛ ትርጓሜ ይጠቅሳቸዋል።

ፍትሐ ነገሥት[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

እንዲሁም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 45፡ §1569 ከአስርቱ ቃላት ሲሆን፣ §1570-1601 ከሕገ ሙሴ የሚከተሉትን በሰፊ እንደ መሠረት ይጠቅሳል።

  • ዘጸአት 21:1-8፣ 18-19፣ 26-36፤ ዘጸአት 22:14-17፣ 28-30፤ ዘጸአት 23:4-8፤
  • ዘሌዋውያን 5:15-16፤ ዘሌዋውያን 6:2-6፤ ዘሌዋውያን 17:10፤ ዘሌዋውያን 18:7-20፣ 22-23፤ ዘሌዋውያን 19:9-10፣ 13-14፣ 16፣ 27-29፣ 31-37፤ ዘሌዋውያን 20:1-5፣ 10፣ 15፣ 27፤ ዘሌዋውያን 21:7-10፣ 13-14፤ ዘሌዋውያን 22:3-4፣ 10-12፣ 20-21፤
  • ዘኊልቊ 6:22-27፤
  • ዘዳግም 19:14-19፤ ዘዳግም 22:1-3፣ 5፣ 8፤ ዘዳግም 24:7፤ ዘዳግም 25:1-4

ሁሉን ከአንዳንድ ጥቃቅን ለውጦች ጋራ በግዕዝ ትርጓሜ ይጠቅሳቸዋል።

ሕገ ሙሴ ከቀደሙትና ከኋለኞች ሕግጋት ጋር ሲነጻጸር[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሕገ ሙሴ መጀመርያው ክፍል (ኦሪት ዘጸአት ምዕራፎች 21 እና 22:1-18) ከቀደሙት የመስጴጦምያ ሕግጋት ጋር ተመሳሳይ ኹኔታዎች ይቀምራል። በተጨማሪ በኋላ የወጡት ዶም ቦክ እና ፍትሐ ነገሥት ክፍሎች ከሕገ ሙሴ ስለ ተመሠረቱ ልዩነቶቹ ከታች ተሰጥተውል።

  • ኡር-ናሙ 4-5፦ «አንድ ባርያ ገረዲቱን ቢያገባ፣ ከዚያም ነጻነቱን ቢያገኝም፣ ከቤተሠቡ ግን አይወጣም። አንድ ባርያ ነጻ ሴትን ቢያገባ፣ በኲሩ ለጌታው ይሰጥ።»
  • ዘጸአት 21:1-6፦ ባርያ ከ፯ ዓመት በኋላ ነጻ ይወጣል፤ ወደ ባርነት ሳይገቡ ከተዳሩ ሁለቱ ነጻ ይወጣሉ፤ ጌታ ሚስቱን ከሰጠው ግን ልጆችም ካሉአት ቤተሠቡ አይወጣም። ባርያ ከቤተሠቡ መራቅ ካልፈለገ ጆሮውን በመውጋት የሕይወት ባርያ ሊሆን ይችላል።
  • ዶምቦክ 11፦ እንደ ሙሴ፣ ግን ጆሮው የሚወጋበት ደጅ የቤተክርስቲያኑ መሆኑን ይወስናል።
  • ፍትሐ ነገሥት 1570፦ እንደ ሙሴ፣ ግን ጆሮ ስለ መውጋት የለውም።

  • ሃሙራቢ 117፦ ሰው ልጁን ለባርነት ቢሸጥ፣ ልጁ ፫ ዓመት ሠርቶ በ፬ኛው ዓመት ነጻ ይወጣል።
  • ዘጸአት 21:7-8፦ ሰው ሴት ልጁን ቢሸጥ እንደ ወንድ አትወጣም። ደስ ካላሰኘች ግን በዎጆ ይሰዳታል።
  • ዶምቦክ 12፦ እንደ ሙሴ፣ ግን ደስ ካላሰኘች በውጭ አገር ነጻ ትውጣ ይላል።
  • ፍትሐ ነገሥት 1570፦ የባርያው ሴት ልጅ በውጭ አገር እንዳትሸጥ ይላል።

  • ሊፒት-እሽታር 27፦ «የሰው ሚስት ልጆችን ካልወለደችለት የአደባባይ ሸርሙጣ ግን ልጆች ከወለደችለት፣ እርሱ ለዚያች ሸርሙጣ እህልን፣ ዘይትንና ልብስን ያስገኛል።»
  • ዘጸአት 21:9-11፦ ሰው ገረዲቱን ለልጁ ሚስት እንድትሆን ሲገዛ፣ እንደ ሴት ልጁ ትሁን፤ ተጨማሪ ሚስት ቢያጋባው «መኖዋን፣ ልብስዋንም ለምንጣፍዋም ተገቢውን አያጒድልባት» ወይም በነጻ ትወጣለች።
  • ዶምቦክ 12፦ እንደ ሙሴ፣ ግን ስለ 'መኖ' ወይም 'ምንጣፍ' ፈንታ «ልብስዋንም ጥሎሽዋንም ይስጣት» አለው።

  • ኡር-ናሙ 1፦ «አንድ ሰው ሌላውን ቢገድል፣ ሰውዬው ይሙት።»
  • ኤሽኑና 47a፦ «ሰው በጠብ የሌላ ሰው ልጅ መሞት ካደረገበት፣ 2/3 ምና ብር ይክፈል።»
  • ሃሙራቢ 207-208፦ የተመታው ሰው ቢሞት፣ የመታው ሰው ለመግደል እንዳላሠበ ይማል፤ የተገደለው ከልደት ነጻ ከሆነ ግማሽ ምና ይክፈል፤ ነጻ የወጣው ከሆነ 1/3 ምና ይክፈል።
  • ዘጸአት 21:12-14፦ «ሰው ሰውን ቢመታ ቢሞትም፣ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።» ያላሠበው በድንገት እንደ ሆነ ግን፣ ወደ ልዩ ሥፍራ ይሸሽ።
  • ዶምቦክ 13፦ እንደ ሙሴ፣ ግን በድንገት እንደ ሆነ፣ ካሣ ይክፈልና ወደ ውጭ አገር ይሸሽ ይላል።

  • ሃሙራቢ 195፦ «ልጅ አባቱን ቢመታ፣ እጁ ይቋረጥ።»
  • ዘጸአት 21:15፦ «አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ፈጽሞ ይገደል።»
  • ዶምቦክ 14፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ኡር-ናሙ 3፦ «አንድ ሰው ሌላወን ቢሰርቅ፣ ሰውዬው ይታሠር።»
  • ሃሙራቢ 14፦ «ማንም ሰው የሌላውን ልጅ ቢሰርቅ፣ ይሙት።»
  • ዘጸአት 21:16፦ «ሰውን ሰርቆ ቢሸጥ፣ ወይም በእጁ ቢገኝ፣ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።»
  • ዶምቦክ 15፦ «ነጻ ሰውን ሰርቆ ቢሸጥ፣ ማስረጃም ካለበት፣ በሞት ይጥፋ።»

  • ሃሙራቢ 195፦ «የቁባት ወይም የሸርሙጣ ልጅ ለእንጀራ አባቱ ወይም እናቱ 'አባቴ አይደለህም' ወይም 'እናቴ አይደለሽም' ቢል፣ ምላሱ ይቋረጥ።
  • ዘጸአት 21:17፦ «አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል።»
  • ዶምቦክ 15፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ኤሽኑና 47፦ ሰው ሌላውን በጠብ ከጎዳው፣ 10 ሰቀል ብር ይክፈል።
  • ሃሙራቢ 206፦ ሰው ሌላውን በጠብ ከጎዳው፣ እንዳላሠበው ይማልና ለሕክምናው ይክፈል።
  • ዘጸአት 21:18-19፦ ሰው ሌላውን በጠብ ከጎዳው፣ ለጊዜውና ለሕክምናው ይክፈል።
  • ዶምቦክ 16፦ እንደ ሙሴ፣ ግን «ለሕክምናው ይክፈልና እስኪድን ድረስ ሥራውን በምትኩ ይሥራ» አለበት።
  • ፍትሐ ነገሥት 1571፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ሃሙራቢ 209/211/213፦ ሰው እርጉዝ ሴት ከመታ ሕጻኑም ከጠፋ፣ ከልደት ነጻ ብትሆን 10 ሰቀል፣ ነጻ የወጣች ብትሆን 5፣ ገረድ ብትሆን 2 ሰቀል ይክፈል።
  • ዘጸአት 21:22፦ ሰው እርጉዝ ሴት ከመታ ሕጻኑም ከጠፋ፣ ባሏና ፈራጆቹ ካሣውን ይወስኑ።
  • ዶምቦክ 18፦ ሰው እርጉዝ ሴት ከጎዳት፣ ፈራጆቹ ካሣውን ይወስኑ።

  • ሃሙራቢ 210/212/214፦ ሴቲቱ እራስዋ ከተገደለች፣ ከልደት ነጻ ብትሆን የገዳይዋ ሴት ልጅ ትሙት፣ ነጻ የወጣች ብትሆን ግማሽ ምና፣ ገረድ ብትሆን 1/3 ምና ይክፈል።
  • ዘጸአት 21:23-25፦ ሴቲቱ እራስዋ ከተገደለች፣ ሕይወት ለሕይወት፤ ከተጎዳችም ዓይን ለዓይን፣ ጥርስ ለጥርስ ወዘተ.
  • ዶምቦክ 19፦ ዘጸ. 21:23 ከ§18 ጋር ስለ እርጉዝ ሴት ሕይወት ሲሆን፣ ይኸው §19 ማንም ሰው ከተጎዳ ዓይን ለዓይን ወዘተ. ነው ይላል።

  • ሃሙራቢ 199፦ ሰው የባርያ ዓይን ወይም አጥንት ቢያጠፋ፣ ግማሽ ምና ካሣ ይክፈል።
  • [በሐጾርከነዓን 2002 ዓም የተገኘ አካድኛ ፍርስራሽ፦ ስለባርያው ዓይን 12 ሰቀል፣ ለአፍንጫው 10 ሰቀል፣ ለጥርሱ 3 ሰቀል ይክፈል።]
  • ዘጸአት 21:26-27፦ ሰው የባርያ ወይም የገረድ ዓይን ወይም ጥርስ ቢያጠፋ፣ ነጻ ይውጣ/ትውጣ።
  • ዶምቦክ 20፦ እንደ ሙሴ ነው።
  • ፍትሐ ነገሥት 1571፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ኤሽኑና 54-55፦ «በሬ ተዋጊ ከሆነ፣ ኃላፊውም ለባለቤቱ ቢመሰክርለት፣ እሱ ግን በሬውን ባይጠብቀው፣ ሰውንም ቢገድል፣ የበሬው ባለቤት 2/3 ምና ብር ይክፈል። ባርያን ወግቶ ቢገድል፦ 15 ሰቀል ብር ይክፈል።»
  • ሃሙራቢ 251-252፦ በሬ ተዋጊ ከሆነ፣ ሰዎችም ለባለቤቱ ቢመሰክሩለት፣ ባይጠብቀውም፣ ሰውንም ቢገድል፣ ባለቤቱ ግማሽ ምና ይክፈል፤ ባርያን ቢገድል 1/3 ምና ይክፈል።
  • ዘጸአት 21:28-32፦ በሬ ሰውን ወግቶ ቢገድል፣ በሬው ይወገር፣ ሥጋውም አይበላ። በሬ ተዋጊ ከሆነ፣ ሰዎችም ለባለቤቱ ቢመሰክሩለት፣ ባይጠብቀውም፣ ሰውን ወግቶ ቢገድል፣ ባለቤቱም ይሙት ወይም ዎጆ ይክፈል። ባርያን ቢወጋ 30 ሰቀል ይክፈል።
  • ዶምቦክ 21፦ እንደ ሙሴ፣ ግን ስለተወጋው ባርያ «30 ሺሊንግ» ብር ይላል።
  • ፍትሐ ነገሥት 1572፦ እንደ ሙሴ፣ ግን ስለተወጋው ባርያ «ዋጋው ለጌታው ይሰጥ» ይላል።

  • ሃሙራቢ 267፦ እረኛ ቸልተኛ ቢሆን፣ በመንጋ አደጋ ቢደርስ፣ የራሱን በሬ ወይም በግ ይካሥ።
  • ዘጸአት 21:33-34፦ ሰው ጒድጓድ ቢከፍት፣ በሬ ወይም አህያ ቢወድቅበት፣ ዋጋውን ይክፈል፣ የሞተውም ለርሱ ይሁን።
  • ዶምቦክ 22፦ እንደ ሙሴ፣ ግን 'በሬ ወይም አህያ' ሳይል 'ከብት' አለው።
  • ፍትሐ ነገሥት 1573፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ኤሽኑና 53፦ በሬ ወግቶ በሬን ከገደለ፣ ሁለቱ ባለቤቶች የደኅናውን በሬ ዋጋና የሞተውን በሬ ሬሳ በትክክል ይካፈሉ።
  • ዘጸአት 21:35-36፦ በሬ ወግቶ በሬን ከገደለ፣ ሁለቱ ባለቤቶች የደኅናውን በሬ ዋጋና የሞተውን በሬ ሬሳ በትክክል ይካፈሉ። በሬ ተዋጊ መሆኑ ከታወቀ ግን፣ ባይጠብቀውም፣ በሬ ለበሬ ይመልስና የሞተው ለርሱ ይሁን።
  • ዶምቦክ 23፦ እንደ ሙሴ ነው።
  • ፍትሐ ነገሥት 1573፦ እንደ ሙሴ፣ ግን 'የሞተውን በሬ ሬሳ' ሳይል 'የሞተውን በሬ ዋጋ' እንዲካፈሉ ይላል።

  • ሃሙራቢ 8፦ ሰው በሬ፣ በግ፣ አህያ፣ አሣማ ወይም ፍየል ቢሰርቅ፣ 30 እጥፍ ይካሥ (ወይም ባለቤቱ ነጻነቱን ያገኘው መደብ እንደ ሆነ፣ 10 እጥፍ ይካሥ)። አለዚያው ሌባ ይሙት።
  • ዘጸአት 22:1-4፦ ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅ፣ 5 እጥፍ ለበሬ፣ 4 እጥፍ ለበግ ይካሥ። አለዚያው ሌባው ይሸጥ። እንስሳን እየሰረቀው በእጁ ቢገኝስ ሌባው 2 እጥፍ ይመልስ፣ በሌሊትም ሆኖ ቢገደል ቅጣት የለም።
  • ዶምቦክ 24-25፦ እንደ ሙሴ፣ ግን ለበሬ 2 እጥፍ አለው።

  • ሃሙራቢ 57፦ ሰው ከብቱን የሌላውን እርሻ ቢያስበላ፣ 20 ጉር እህል ለ10 ጋን ጉዳት ይመልስለት።
  • ዘጸአት 22:5፦ ሰው ከብቱን የሌላውን እርሻ ቢያስበላ፣ ከተመረጠው እህል ወይም ወይን ይመልስለት።
  • ዶምቦክ 26፦ ሰው የሌላውን እርሻ በማንኛውም ቢጎዳ፣ ዋጋውን ይካሥ።

  • ኡር-ናሙ 31፦ «አንድ ሰው የሌላውን እርሻ በውኃ ቢሞላ፣ ሦስት ኩር ገብስ ለአንድ ኢኩ እርሻ ይስጠው።»
  • ሃሙራቢ 53-56፦ ሰው የሌላውን እርሻ በውኃ ቢሞላ፣ ይካሠው።
  • ዘጸአት 22:6፦ ሰው የሌላውን እርሻ በእሳት ቢያቃጥል፣ ይካሠው።
  • ዶምቦክ 27፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ኤሽኑና 36-37፦ «ሰው ንብረቱ እንዲጠበቅ አደራ ቢያኖር፣ አደራ ያለው ባልንጀራ ማንም ሌባ እቤቱ ሳይገባ ንብረቱ እንዲጠፋ ካደረገ፣ ባልንጀራው ንብረቱን ለሰውዬው ይተካል። ከቤቱም ቢሰረቅ፣ የባለቤት ማጣት ነው፣ ባለቤቱ በቤተ መቅደስ ለሰውዬው በአምላክ ይማል፦ «የኔና ያንተ ንብረት አንድላይ ጠፍተዋል፣ እኔ አልከፋሁም አልበደልኩም።» ይማልና ምንም ዕዳ አይሆንበትም።
  • ሃሙራቢ 125-6፦ ሰው ንብረቱ እንዲጠበቅ አደራ ቢያኖር፣ ከቤቱም ቢሰረቅ ወይም ቢጠፋ፣ ሰውዬው ንብረቱን ከባለቤቱ ፈልጎ ይተካል፤ በአምላክ ፊት የጠፋው ዋጋ ይማልና ሀሣዊ ከሆነ ፪ እጥፍ ይተካል።
  • ዘጸአት 22:7-15፦ ሰው ንብረቱ እንዲጠበቅ አደራ ቢያኖር፣ ከቤቱም ቢሰረቅ፣ ሌባ ቢገኝ ሌባው ፪ እጥፍ ይክፈል፤ ሌባው ባይገኝ ባለቤቱ በፈራጆች ፊት እጁን በባልንጀራው ሀብት እንዳልዘረጋ ይማል፤ ክርክር ከሆነ ፈራጆች የፈረዱበት ፪ እጥፍ ይክፈል። እንስሳ አደራ ቢያኖር ቢጠፋ፣ አደራ ያለው በእግዚአብሔር ሆን ብሎ እንዳልበደለው ይማልና መካሥ የለበትም። እንስሳው ቢሰረቅ ግን መካሥ አለበት። ጉዳቱም የደረሰው የእንስሳው ባለቤት እያለ ወይም በኪራይ ከሆነ ሌላ መክፈል የለበትም።
  • ዶምቦክ 28፦ ሰው ንብረቱ እንዲጠብቅ ለባልንጀራው አደራ ቢያኖር፣ እራሱ ቢሰርቀው ፪ እጥፍ ይክፈል፤ ማን እንደ ሰረቀው ባያውቅ የዋህነቱን ያስረዳ። ከብት ከሆነና ሥራዊቱ ወሰደው ወይም ሞቷል ቢለው ምስክርም ካለ ምንም አይክፈል። ምስክር ከሌለው ባያመነውም እንዳልበደለው ይማል።
  • ፍትሐ ነገሥት 1574፦ ሰው እንስሳ እንዲጠበቅ አደራ ቢያኖር፣ ባለቤቱም እየሌለ ጉዳት ቢደርስበት፣ ይካሠው። ባለቤቱ ሳለ ወይም በኪራይ ከሆነ ግን አይክፈል።

  • ኤሽኑና 27፦ ወንድ እንዲያግባት ወላጆቿን ሳይጤይቅ ያልታጨችውን ልጅ ከያዘ፣ ከ፩ ዓመት በኋላ እቤቱ ውስጥ ብትገኝ፣ እንደ ሚስቱ ትቆጠራለች።
  • ሃሙራቢ 128፦ የጋብቻ ውል ካልኖረ እንደ ሚስት አትቆጠረም።
  • ዘጸአት 22:16-17፦ ወንድ ካልታጨች ሴት ጋር በወሲብ የተኛ እንደ ሆነ፣ ማጫ ለአባትዋ ይክፈልና ሚስቱ ትሁን፣ አባትዋም ሴት ልጁን ለዚህ ሰው መስጠት እምቢ ቢልም፣ ሰውዬው ግን ብሩን መክፈል አለበት።
  • ዶምቦክ 29፦ እንደ ሙሴ ነው።
  • ፍትሐ ነገሥት 1575፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ኡር-ናሙ 13፦ «ሰው ጠንቋይ ነው ተብሎ ቢከሰስ፣ በወንዝ ውስጥ በመግባት ይፈረድ፤ የዋሕነቱ ከተረዳ ከሳሹ 3 ሰቅል ብር ይክፈለው።»
  • ሃሙራቢ 2፦ ሰው ጠንቋይ ነው ተብሎ ቢከሰስ፣ በወንዝ ውስት በመግባት ይፈረድ፤ የዋሕነቱ ከተረዳ ከሳሹ ይሙት፣ ተከሳሹም ርስቱን ይውረስ።
  • ዘጸአት 22:18፦ «መተተኛይቱን በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድላት።»
  • ዶምቦክ 30፦ እንደ ሙሴ ነው።

ከዚህ ክፍል በኋላ (ከምዕራፍ 22:18 ቀጥሎ) የሚገኙት ሕግጋት ይተለያዩ አዳዲስ ደንቦችና ማስታወሻዎች ናቸው። በኋላ የሚከተሉት ሕግጋት ደግሞ ከኋለኞች ሕግጋት ጋር ሊነጻጽሩ ይቻላል፦

  • ዘጸአት 22:19፦ «ከእንስሳ ጋር የሚረክስ ፈጽሞ ይገደል።»
  • ዶምቦክ 31፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 22:20፦ «ከእግዚአብሔር በቀር ለአንዳች አምላክ የሚሠዋ ፈጽሞ ይጥፋ።»
  • ዶምቦክ 32፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 22:21፦ «በግብጽ ምድር ስደተኞች ነበራችሁና ስደተኛውን አትበድለው፣ ግፍም አታድርግበት።»
  • ዶምቦክ 33፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 22:22-24፦ ወደኔ እንዳይጮሁ እንዳልመታችሁም መበለትንና ድሃ አደጎችን አታስጨንቃቸው።
  • ዶምቦክ 34፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 22:25፦ ለድሃ ባልንጀራህ ብድር ብትሰጠው፣ አራጣ አትጫንበት።
  • ዶምቦክ 35፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 22:26-27፦ «የባልንጀራህን ልብስ ለመያዣ ብትወስድ ፀሐይ ሳትገባ መልስለት...»
  • ዶምቦክ 36፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 22:28፦ «ፈራጆችን አትሰድብ፣ የሕዝብህንም አለቃ አትርገመው።»
  • ዶምቦክ 37፦ «ጌታ አምላክህን አትሰድብ፣ የሕዝብህንም ጌታ አትርገመው።»
  • ፍትሐ ነገሥት 1576a፦ «መኳንንትን አትሟቸው። የወገንህን ሹም አትሳድብ።»

  • ዘጸአት 22:29-30፦ ነዶ፣ ወይን ጭማቂ፣ የልጅ (በግዝረት)፣ በስምንተኛውም ቀን የከብት በኲራት ለእግዜር ያቅርቡ።
  • ዶምቦክ 38፦ የነዶ አሥራትህን የከብት በኲራትህንም ለእግዚአብሔር ስጡ።
  • ፍትሐ ነገሥት 1576b፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 22:31፦ «...በምድረ በዳ አውሬ የቧጨረውን ሥጋ ለውሻ ጣሉት እንጂ አትበሉት።»
  • ዶምቦክ 39፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 23:1፦ «ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ ሐሰተኛ ምስክር ትሆን እንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ።»
  • ዶምቦክ 40፦ «ለሐሰተኛውን ቃል አታዳምጥ፣ ክርክሮቹን አትቀበል ወይም ለእርሱ ምስክር አትሁን።»

  • ዘጸአት 23:2-3፦ «ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር። በፍርድ ነገርም ለድሀው አታድላ።»
  • ዶምቦክ 41፦ «በቃላቸው በጩኸታቸው በኅሊናህ ላይ እንደ ሰነፎች ትምህርት፣ ለሕዝቡ ሞኝነትና ለጠማማ ምኞታቸው አትዙር፤ አትፍቀዳቸውም።»

  • ዘጸአት 23:-4-5፦ «የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው በፍጹም መልስለት...>
  • ዶምቦክ 42፦ «የሰውን ከብት ጠፍቶ ብታገኘው የጠላትህ ቢሆንም አሳውቀው።»
  • ፍትሐ ነገሥት 1577a፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 23:6-7፦ «...የድሀህን ፍርድ አታጥምም። ከሐሰት ነገር ራቅ፤ እኔ ኃጢአተኛውን አላጸድቅምና ንጹሕንና ጽድቅን አትገድል።»
  • ዶምቦክ 43-45፦ «በትክክል ፍረዱ። አንድ ፍርድ ለሀብታሞች፣ ሌላ ለድሆች፣ ወይስ አንድ ለወዳጅህ፣ ሌላ ለጠላትህ፣ አትፍረዱ። ከመከራየት ራቅ፣ ንጹሕንና ጽድቅን አትገድል።»
  • ፍትሐ ነገሥት 1577b፦ «ጽድቁንም በመግደል አትተባበር። ኃጢአተኛውንም አታድን።»

  • ዘጸአት 23:8፦ «ማማለጃን አትቀበል...»
  • ዶምቦክ 46፦ እንደ ሙሴ ነው።
  • ፍትሐ ነገሥት 1577c፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ዘጸአት 23:9፦ = 22:21
  • ዶምቦክ 47፦ = §33 (እንደ ሙሴ ነው።)

  • ዘጸአት 23:13፦ «ያልኋችሁንም ነገር ሁሉ ጠብቁ፣ የሌሎችንም አማልክት ስም አትጥሩ፣ ከአፋችሁም አስማ።»
  • ዶምቦክ 48፦ «በአረመኔዎቹ አማልክት ከቶ አትምሉ፣ ወይም በማንኛውም ጉዳይ አትጩኹላቸው።»



  • ኡር-ናሙ 8፦ «አንድ ሰው የሌላውን ገረድ በግፍ ቢወስድ፣ ሰውዬው 5 ሰቅል (ብር) ይክፈል።»
  • ኤሽኑና 31፦ «ሰው የሌላውን ሰው ገረድ በወሲብ ከያዘ፣ 1/3 ምና (20 ሰቀል ወይም 180 ግራም) ብር ይክፈል፤ ገረዲቱም የጌታዋ ሆና ትቅር።»
  • ዘሌዋውያን 19:20-22፦ ሰው ከታጨች ገረድ (ሴት ባርያ) ጋር ቢተኛ፣ ቅጣት አለባቸው እንጂ አይገደሉም። አውራ በግ ይሠዋ።

ከዘሌዋውያን 20:9 እስከ 20:12 ላለው ክፍል ደግሞ በመስጴጦምያ ተመሳሳይ ሕጎች ተገኝተዋል።

(ዘሌዋውያን 20:9=ዘጸአት 21:17)

  • ኡር-ናሙ 6-7፦ «አንድ ሰው የሌላውን ሚስት በግፍ ቢወስድ፣ ሰውዬው ይገደል። የሰው ሚስት ሌላውን ሰው በማዳራት ብትወስድ፣ ሴቲቱ ትገደል፣ ወንዱ ግን ነጻ ነው።»
  • ኤሽኑና 26-27፦ ሰው ከሌላው ሚስት ወይም እጮኛ ጋር ቢተኛ እርሱ ይሙት በቃ።
  • ሃሙራቢ 129-132፦ ሰው ከሌላው ሚስት ጋር ቢተኛ ሁለቱ ወደ ወንዙ ይጣሉ።
  • ዘሌዋውያን 20:10፦ ሰው ከሌላው ሚስት ጋር ቢተኛ ሁለቱ ይገደሉ። (በሜዳ በግፍ ከሆነ ግን ጩከቷን የሚሰማ ስለሌለ እርሱ ብቻ ይሙት - ዘዳግም 22:25-27)
  • ፍትሐ ነገሥት 1587a፦ እንደ ሙሴ ነው።

  • ሃሙራቢ 154, 157፦ ሰው ከልጁ ጋር ቢተኛ ከከተማው ያባርሩት። ሰው ከእናቱ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ይቃጠሉ።
  • ዘሌዋውያን 20:11 ሰው ከእናቱ ወይንም ከአባቱ ሚስት ጋር ቢተኛ ሁለቱ ይገደሉ። (ከልጁም ጋር የሚተኛ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል - ዘሌዋውያን 18:6, 29)

  • ሃሙራቢ 155፦ ሰው ከምራቱ ጋር ቢተኛ እርሱ ወደ ውኃው ይጣል።
  • ዘሌዋውያን 20:12፦ ሰው ከምራቱ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ይገደሉ።

  • ኡር-ናሙ 18-22፦ ጉዳት ለዓይን - 30 ሰቀል፣ ለጥርስ፦ 2 ሰቀል፣ ለአካል፦ 60 ሰቀል፣ ለአፍንጫ 40 ሰቀል፣ ለእግር 10 ሰቀል ለተጎዳው ይክፈል።
  • ኤሽኑና 42-46፦ ጉዳት ለዓይን - 60 ሰቀል፣ ለጥርስ፦ 30 ሰቀል፣ ለአካል፦ 30 ሰቀል፣ ለአፍንጫ 60 ሰቀል፣ ለጣት ወይም ክሳድ 40 ሰቀል ለተጎዳው ይክፈል።
  • ሃሙራቢ 196-201፦ የተጎዳው ከልደት ነጻ ከሆነ፣ ዓይን ለዓይን፣ ጥርስ ለጥርስ፣ አጥንት ለአጥንት። ነጻነቱን ያገኘው ቢሆን፣ ለዓይን፦ 60 ሰቀል፣ ለጥርስ፦ 20 ሰቀል። ለባርያ ዓይን 30 ሰቀል።
  • ዘሌዋውያን 24:20፦ ስብራት ለስብራት፣ ዓይን ለዓይን፣ ጥርስ ለጥርስ።

  • ኡር-ናሙ 9-10፦ አንድ ሰው የመጀመርያ ጊዜ ሚስት ቢፈታ፣ አንድ ምናን (60 ሰቅል) ይክፈላት። አንድ ሰው ጋለሞታን ቢፈታ፣ ግማሽ ምናን (30 ሰቅል) ይክፈላት።
  • ሃሙራቢ 137- 141፦ ሰው ሚስቱን ቢፈታ፣ አንድ ምናን ወይም ጥሎሽዋንና ለልጆቿ የሚገባ ድርሻ ይክፍላት። ጥፋትዋ ከሆነ ግን አይከፍልም።
  • ዘዳግም 24:1-4፦ ሰው ሚስቱን ቢፈታ የፍች ጽሕፈት ይስጣት። ሌላ ባል ካገባች በኋላ መጄመርያው ዳግመኛ ሊያግባት አይችልም።

የነዋይ ደንቦች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የምግብ ደንቦች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የምግብ ደንቦች ለእስራኤልኦሪት ዘሌላውያን ምዕራፍ 11 ይገኛሉ። ከእንስሶች አንዳንድ አይነቶች ተከለክለዋል። ስለ አትክልትም ዝም ይላል።

ሐዋርያት ሥራ መሠረት ለክርስቲያኖች ተግባራዊ የሆኑት ደንቦች እላይ እንደ ተመለከተው «ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከተናቀም ከመብላት» የሚከለክሉ ብቻ ናቸው።

ለመጀመርያው ደንብ በዝርዝሩም ቅዱስ ጳውሎስ፩ ቆሮንቶስ 10:25 እንዳስረዳው፣ «በሥጋ ገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ከሕሊና የተነሣ ሳትመራመሩ ብሉ... ማንም ግን፦ ይህ ለጣኦት የተሠዋ ነው ቢላችሁ ከዚያ ካስታወቃችሁና ከሕሊና የተነሣ አትብሉ...»

ደም አለመብላቱ ለኖኅ ልጆች ሁሉ በእርጉማን ታዝዟል። ስለዚህ ማንኛውም ሥጋ ብርንዶ ቢሆንም በደንብ ደሙን ማፍሰስ ያስገድዳል።

ተዋሕዶና በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ዘርፍ ሌሎች ደንቦች ለምሳሌ አሳማ አለመብላቱ በፈቃደኝነት ይከበራሉ። በፍትሐ ነገሥት እንደ ሐዋርያት ሥራ ከማዳገም በላይ «መኅምዝ ጥርሶች ወይም ጥፍሮች» ያላቸው መርዛም ተብለው ይከለከላሉ። በሌላ እንስሳ የተገደለውን ከመብላት ደግሞ ይከለከላል።

በሕገ ሙሴ እራሱ ለእስራኤል የምግብ ደንቦች እስካሁን «ኮሸር» ተብሎ በአይሁዶች ሲጠበቁ እንዲህ ናቸው፦

እስልምና፣ የምግብ ደንቦች በቁርዓን መሠረት ለሕገ ሙሴና ሕገ ወንጌል ተመሳሳይ ናቸው። ከደም፣ ከተናቀም፣ በሌላ እንስሳ ከተገደለው፣ ከአሳማ፣ በአላህ ስም ካልተገደለው እንስሳ ከመብላት፣ አረቄንም ከመጠጣት ይከለከላል። በአንዳንድ የእስልምና ዘርፍ ባሕል ከዚህ ትንሽ ሊለይ ይችላል፤ ለምሳሌ በቱርክ አገር በሚገኘው አሌቪ እስልምና ዘንድ፣ አረቄ ይፈቀዳል፣ ጥንቸልም ይከለከላል። በሺዓ እስልምናም፣ ዛጎል ለበስ ዓሣ (ሠርጠን ወዘተ.) መብላት ይከለከላል።

የዝሙት ደንቦች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ኦሪት ዘሌላውያን እንዲሁም ለክርስቲያኖችና ለእስላሞች ተግባራዊ የሆኑት የወሲብ ሕገጋት እንዲህ ናቸው፦

ማናቸውም ወሲብ ወይም ወሲብ የመሰለ ሌላ ሥራ ከማናቸውም ሌላ ዝርያ እንስሳ ጋር፣ ከማናቸውም ቅርብ ዘመድ ጋር፣ ወይም ከተመሳሳይ ጾታ ጋር በፍጹም ክልክል ነው፣ ዝሙት (ዕብራይስጥ «ዝኑት») ነው። እንዲሁም አካለ መጠን የደረሰ(ች)ና አካለ መጠን ያልደረሰ(ች) አንድላይ ክልክል ነው። በዘሌዋውያን መንገድ የሚፈቀደው በ፩ ወንድና ፩ ሴት ትዳር ውስጥ ብቻ ነው፣ ሴቲቱ ያልታጨች እንደ ሆነ ግን ወንዱ የማጫ ብሩን ከፍሎ እሷን (ወይም አባቷን) ስለ ጋብቻ መግፋፋት ሃላፊነት አለበት። ትዳራቸውም የሁለታቸው አንድነት ይባላል፣ ማመንዘር አይፈቀደም።

በጥንት እስራኤል አንድ ወንድ ሀብታም ከሆነ ተጨማሪ ሚስት ማግባት ሕጋዊ ነበር። እንዲያውም ተጨማሪ ሚስት ማግባቱን የከለከለው የሮሜ መንግሥት ሕገጋት ነበር፤ ይህ ግን በመጀመርያው ቤተ ክርስቲያን ተቀበለና ተጨማሪ ሚስት ያለችው ከሰሚ ምዕመን ደረጃ በላይ ከፍ እንዳይል ወይም ዲያቆን እንዳይሆን ወይም ላንዲቱ ብቻ ጠብቆ ሌሎቹን ካልተወ በቀር እንዳይጠመቅ በአዲስ ኪዳን ይጻፋል።

በእስልምና ደግሞ የዝሙት (ወይም በአረብኛ «ዝና») ሕግጋት በሁሉ ከዘሌዋውያን ጋር ይስማማሉ። በነቢዩ ሙሐመድ ትምህርት ዘንድ ሀብታም ወንድ እስከ አራት ሚስቶች ድረስ ማግባት ይፈቀዳል።

የቄሳውንት ደንቦች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የበሽታ ደንቦች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የመሥዋዕት ደንቦች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

  • (በእግዚአብሔር ቃል ለነቢዩ ኢሳይያስ ምናልባት 709 ዓክልበ. የመሥዋዕት ሥርዓት ተሠረዘ (ትንቢተ ኢሳይያስ ፩፡፲፩፣ ፷፮፡፫)። ይህም መልእክት በኋላ ለመጡት ነቢያት እንደገና ይደጋገም ነበር፤ በትንቢተ ኤርምያስ ፮፡፳ እና በተለይ በትንቢተ አሞጽ ፭፤፳፪ ግልጽ ነው። ሆኖም አይሁዶች እስከ 62 ዓ.ም. ድረስ የኢየሩሳሌም መቀደስ በቤስጳስያን ዘመን እስከ ጠፋ ድረስ መሥዋዕቶቹን አላቋረጡም፤ ኢየሱስም ከመቅደስ ሸያጭ በቀር ልማዱን ታገሠው።)

የበዓላት ደንቦች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሌሎች የተለያዩ ደንቦች[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

: