Jump to content

የኖህ ልጆች

ከውክፔዲያ
(ከኖኅ ልጆች የተዛወረ)

የኖህ ልጆችመጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ይዘርዘራሉ።

በአዚህ መጽሐፍ ዘንድ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ከኖህ 3 ልጆች ከሴም ካምያፌትና ከሚስቶቻቸው ተወልደዋል ይባላል። ይህም በአውሮፓ ውስጥ በብዙዎቹ እስከ 19ኛ ክፍለ ዘመን ድረስ እንደ ታሪካዊ ዕውነት ይቆጠር ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ በብዙ አይሁድእስላምክርስቲያን አማኞች ዘንድ ዕውነተኛ ታሪክ ሆኖ ይታመናል።

ሴማውያን አባት ይባላል።

  • ኤላም - የሴም ልጅ። የኤላም ሕዝብ አገራቸውን «ሃልታምቲ» ሲሉት ከጥንት ጀምሮ መንግሥትና ዋና ከተማ ሱሳ ነበራቸው። ኤላምኛ ግን ከሴማዊ ቋንቋዎች ጋር አይቆጠርም። አንዳንድ ሊቃውንት ኤላምኛ ከደቡብ ሕንድ ድራቪዲያን ቋንቋዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ይገምታሉ።
  • አሦር (ደግሞ «አቡር» በኩፋሌ) - የሴም ልጅ። የአሦር አገር ሕዝብ ራሳቸው ከቅድማያታቸውና አምላካቸው ከአሹር እንደተወለደ አመኑ። ደግሞ በጤግሮስ ወንዝ የተመሠረተው ዋና ከተማ ስም አሹር ነበረ።
  • ሉድ - የሴም ልጅ። አብዛኛው የጥንት ጸሐፍያን ይህ ስም ከትንሹ እስያ መንግሥት ከልድያ ጋር ይሄዳል ብለዋል። እነሱም በአሦር መዝገቦች «ሉዱ» ተብለው ታወቁ። ከዚያ ቀድሞ በዚያው ዙሪያ የኖሩት የሉዊያ ሰዎች ደግሞ ተጠቅሰዋል።
  • አራም - የሴም ልጅ። በአካድ ንጉሥ ናራም-ሲን ጽላቶች በ2034 ዓክልበ ገደማ በ«አራም» ላይ ዘመቻ እንደ ተገረገ ሲመዝገብ ይህ የአራም ሕዝብ ጥንታዊነት ይመሰክራል። አራማውያን በቀድሞ ዘመን «አራም-ነሃራይም» ሲባሉ በስሜን-ምዕራብ ሜስጶጦምያ ተገኙ። የአራም ልጆች በካራን እንደ ተሠፈሩ ይባላል። በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ ውስጥ፣ የአራም 4 ልጆች እንደ ሴም ልጆች ቢመስሉም፣ በጥቂት ዕብራይስጥና ግሪክ ቅጂ ግን «እነዚህም የአራም ልጆች ናቸው» የሚሉ ተጨማሪ ቃላት ይገኛሉ።
    • ዑፅ - የአራም ልጅ። ደግሞ በመጽሐፈ ኢዮብ ይጠቀሳል።
    • ሁል - የአራም ልጅ።
    • ጌቴር - የአራም ልጅ። በአረባዊ ልማድ ዘንድ ይህ የጣሙድ አባት ነበረ።
    • ሞሶሕ («ሞሳሕ» በ1 ዜና መዋ.) - የአራም ልጅ።
  • አርፋክስድ - የሴም ልጅ። ልጆቹ በመጽሐፈ ኩፋሌ መሠረት የከላውዴዎን ዑር ሠሩ። ይህም ከተማ ምናልባት ከኤፍራጥስ ወንዝ ደቡብ ያለው የሱመር ከተማ ዑር፤ ወይም ምናልባት ዑርፋ (በዛሬው ደቡብ-ምሥራቅ ቱርክ) ይሆናል።
    • ቃይንም በአንዳንድ ጥንታዊ ምንጭ ዘንድ የአርፋክስድ ልጅና የሳላ አባት ነው። ስሙ በእብራይስጥ ማሶሬታዊ ትርጉም ባይገኝም በግሪክ፣ በኩፋሌና በሉቃስ 3፡36 (የኢየሱስ ትውልድ መጽሐፍ) ይገኛል።
      • ሳላ - የቃይናም (ወይም የአርፋክስድ) ልጅ።
        • ዔቦር - የሳላ ልጅ።
          • ፋሌቅ («ፋሌክ» በኩፋሌ) - የኤቦር ልጅ። ምድር በፋሌቅ ቀን በሴም ካምና ያፌት ልጆች መካከል እንደ ተካፈለ ይባላል።
          • ዮቅጣን - የኤቦር ልጅ።
            • አልሞዳድ - የዮቅጣን ልጅ። ልጆቹ ምናልባት በየመን ሠፈሩ።
            • ሣሌፍ - የዮቅጣን ልጅ። ልጆቹ ምናልባት ሣሊፍ በየመን ነበሩ። ዋና ከተማቸውም ሱላፍ ነበር።
            • ሐስረሞት - የዮቅጣን ልጅ። ምናልባት የሃድራማውት መንግሥት በምስራቅ የመን
            • ያራሕ - የዮቅጣን ልጅ።
            • ሀዶራም - የዮቅጣን ልጅ። ምናልባት ከሁራሪና ጋር ግንኙነት ሊሆን ይችላል። ይህም በአሦር ንጉሥ አስናፈር ጽላቶች ዘንድ በደቡብ አረቢያ የተገኘው ከተማ ሲሆን፣ ከዚህ በላይ በሸዋ ብቻ የሚገኝ የፍራፍሬ አይነት ስም ነው።
            • አውዛል - የዮቅጣን ልጅ። ምናልባት የሳና (የመን) ጥንታዊ ስም «አዛል»
            • ደቅላ - የዮቅጣን ልጅ።
            • ዖባል - የዮቅጣን ልጅ።
            • አቢማኤል - የዮቅጣን ልጅ።
            • ሳባ - የዮቅጣን ልጅ። ሳባ የኩሽ ልጅ ይዩ። ይህ ሳባ ደግሞ ከሳባውያን ጋር እንደሚሄድ ይታስባል።
            • ኦፊር - የዮቅጣን ልጅ። ምናልባት በየመን ወይም ሕንድ።
            • ኤውላጥ - የዮቅጣን ልጅ። ኤውላጥ የኩሽ ልጅ ይዩ። ይህም ኤውላጥ ደግሞ በቀይ ባሕር አጠገብ የሆነ የአረቢያ ክፍል መሆኑ ይታሥባል።
            • ዮባብ የዮቅጣን ልጅ።
  • ኩሽ («ኲሽ»፣ «ኲሳ» በኩፋሌ) - የካም ልጅ። የኩሽ መንግሥት ከጥንት ጀምሮ ከግብጽ ደቡብ እንደ ኖረ ይታወቃል። አንዳንድ ጸሐፊዎች ግን ከሱመር ከተማ ኪሽ ጋራ ወይም ከዚያ ምስራቅ ባሉት በዛግሮስ ተራሮች ከኖሩት ካሣውያን ነገድ ጋራ ግኙነት ያያሉ።
    • ሳባ - የኩሽ ልጅ። ይህ ሳባ (ወይም ሸባ) የኩሽ ልጅ እና 'ሳባ የራዕማ ልጅ' ሁለቱ ከሳባውያን ጋር እንደሚሄዱ ይታስባል። ከሁለቱ ሸባ በኤርትራ ሳባም በየመን እንደ ተገኘ ይታስባል።
    • ኤውላጥ - የኩሽ ልጅ። አብዛኛው ጊዜ ይህ በቀይ ባሕር አጠገብ የሆነ የአረቢያ ክፍል መሆኑ ይታሥባል።
    • ሰብታ - የኩሽ ልጅ። ምናልባት የሃድራሞት (የመን) ጥንታዊ ዋና ከተማ ሳውባጣ? አባ ጎርጎርዮስ እንደሚሉ አቢሲ ነው[1]
    • ራዕማ - የኩሽ ልጅ። ምናልባት በስትራቦን የተጠቀሰው ነገድ ራማኒታይ ወይም በፋርስ ባሕር ላይ ያለው ከተማ ረግማህ?
      • ድዳን - የራዕማ ልጅ።
      • ሳባ (ሸባ) - የራዕማ ልጅ። ከዚህ ላይ ሳባ የሚለውን ተመልከት።
    • ሰበቃታ («ሰብቃታ» በ1 ዜና መዋ.) - የኩሽ ልጅ። ምናልባት «ሳባይቲኩም ኦስቲዩም» ወይም በአንድ የኤርትራ ወደብ ዙሪያ የኖረ የሳባውያን ነገድ።
    • ናምሩድ - የኩሽ ልጅ። ደግሞ «በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ» በመባል ይታወቃል። እሱ ጥንታዊ ባቤልን፣ አካድን፣ ሰናዖርንና ምናልባትም ከተሞች በአሦር እንደ መሠረተ ይጻፋል። በእብራይስጥ ዘፍ. 10፡11 ሁለት ትርጉሞች ይቻላል፤ ስለዚህ «አሦር» ሲል የሴም ልጅ ስም ወይም በናምሩድ የገነባው ሥፍራ መሆኑ እርግጠኛ አይደለም። የዛሬው ትርጉሞች በዚህ ጥያቄ ይለያያሉ።
  • ምጽራይም (ደግሞ «ሜስጥሮም» በኩፋሌ) - የካም ልጅ። ምጽራይም ለጥንታዊ ግብጽ የሆነ ስም ሲሆን ቃል በቃል ከጥንታዊ ግብጽ ቋንቋ ታ-ውይ (ሁለቱ አገሮች) ያስተርጒማል። ዛሬ በአማርኛም ሆነ በአረብኛ «ምስር» የሚለው ስም ከዚህ የተነሣ ነው።
    • ሉዲም - የምጽራይም ልጅ።
    • ዐናሚም - የምጽራይም ልጅ። ከአሦር ንጉሥ 2ኛ ሳርጎን ዘመን የደረሰ መዝገብ በሊቢያ የተገኘ ነገድ «አናሚ»ን ይጠቅሳል።
    • ላህቢም
    • ነፍታሌም (ነፍተሂም በዜና) - የምጽራይም ልጅ። ምናልባት ከሜምፎስ ስም በጥንታዊ ግብስ ቋንቋ («ና-ፕታህ») ጋር ግንኙነት ይሆናል።
    • ፈትሩሲም - የምጽራይም ልጅ። ምናልባት ከጥንታዊ ግብጽኛ ቃል «ፓ-ቶ-ሪስ» (ማለት ደቡባውያን) ጋር ግንኙነት አለው።
    • ከስሉሂም («ፍልስጥኤማውያን ከነሱ የመጡባቸው») - የምጽራይም ልጅ።
    • ቀፍቶሪም (ከፍቶሪም በዜና) - የምጽራይም ልጅ። «ቀፍቶር» ወይም ቀርጤስ (ክረይት) ወይም ቆጵሮስ ወይም ሁለቱ ይሆናል።
  • ፉጥ (ደግሞ «ፉድ» በኩፋሌ) - የካም ልጅ። የጥንት ሊቃውንት «ፉጥ» ጥንታዊ ሊብያውያን («ለቡ» እና «ፒቱ») እንደ ነበሩ በማለት ይስማማሉ። እነዚህ የግብጽ ጎረቤቶች በስተ ምዕራብ ነበሩ።
  • ከነዓን - የካም ልጅ። ዛሬ እስራኤል እና ሊባኖስ በሚባለው በሜዲቴራኔያን ምሥራቅ ጠረፍ ላይ ባለው አገር የተቀመጠ ብሔርና ሕዝብ ስም እንደ ነበር ይታወቃል።
    • ሲዶን - የከነዓን በኲር ልጅ። በፊንቄ ጠረፍ ላይ ያለውም የጥንታዊ ከተማ-አገር ስም ነው።
    • ኬጢያውያንኬጢ» በ1 ዜና መዋ.) - የከነዓን ልጅ። ኬጢያውያን በብሉይ ኪዳን በምድረ ከነዓን ከተገኙት ወገኖች አንዱ ሆነው ከመቆጠራቸው በላይ ወደ ስሜን በትንሹ እስያ ሃይለኛ የኬጢያውያን መንግሥት ነበረ። ይህም በ20ኛው መቶ ዘመን በሥነ ቅርስ ተረጋገጠ።
    • ኢያቡሳውያን («ኢያቡሳዊው» በ1 ዜና መዋ.) - የከነዓን ልጅ። በኢየሩሳሌም ዙሪያ የኖረ ወገን። የኢየሩሳሌም ስም ቀድሞ በመጽሐፈ ነገሥት ዘንድ «ኢያቡስ» ነበረ።
    • አሞራውያን («አሞራዊው» በ1 ዜና መዋ.) - የከነዓን ልጅ። በዮርዳኖስና በኤፍራጥስ ወንዞች መካከል የኖረ ሕዝብ፤ በአካዳውያንና በግብጻውያን ሰነዶች «አሙሩ» ተብለው ታወቁ።
    • ጌርጌሳውያን («ጌርጌሳዊው» በ1 ዜና መዋ.) - የከነዓን ልጅ።
    • ኤዊያውያን («ኤዊያዊው» በ1 ዜና መዋ.) - የከነዓን ልጅ።
    • ዐሩኬዎን («ዐርካዊው» በ1 ዜና መዋ.) - የከነዓን ልጅ። ምናልባት የፊንቄ ከተማ-አገር አርቃ
    • ሲኒ («ሲኒያዊው» በ1 ዜና መዋ.) - የከነዓን ልጅ። ምናልባት ከሲን ምድረ በዳ ጋር ግንኙነት አለ።
    • አራዴዎን - የከነዓን ልጅ። የፊንቄ ከተማ-አገር አርዋድ
    • ሰማሪዎን - የከነዓን ልጅ። የፊንቄ ከተማ-አገር ዘማር
    • አማቲ - የከነዓን ልጅ። የሶርያ ከተማ ሐማት

አፍሪካውያን እንግዲህ በጥንት የካም ልጆች ተባሉ። እስከ ዛሬ ኩሻውያን ወይም ኩሺቲክ ሕዝቦች ሲገኙ በምዕራብ አፍሪቃ የሚገኙት ዮሩባ ሕዝብ የትውልዳቸውን ሐረግ እስከ ካም ድረስ ያደርሱታል። ከ9ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ አንድ አይሁድ የስዋሰው መምህር ይሁዳ እብን ቁራይሽ እንደ አስረዳ የኩሺቲክና የሴሚቲክ ቋንቋ ቤተሠቦች ዝምድናን ያሳያሉ። ዛሬ የቋንቋ ጥናት ሊቃውንት እነዚህን ልሳናት ከግብጽኛበርበርኛቻዲክ፣ እና ኦሞቲክ ቤተሠቦች ጋራ በአንድ ታላቅ አፍሮ-እስያዊ ቋንቋዎች ቤተሰብ ውስጥ ይጨምራሉ። በተጨማሪ በደቡባዊ አፍሪካ ያሉት ቤተሠቦች (እንደ ባንቱ) ከነዚህ የተለዩ ናቸው።

የያፌት ልጆች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
  • ጋሜር («ጎሜር»፣ «ሴሜር» በኩፋሌ) - የያፌት ልጅ። አብዛኛው ጊዜ መታወቂያቸው ከአሦርኛ መዝገቦች የታወቁት ዘላን ሕዝብ ጊሚሩ (ኪሜራውያን) መሆኑ ይገመታል። የዌልስ አፈ ታሪክ ደግሞ ከጋሜር ዘር መሆኗን ይነግራል።
    • አስከናዝ - የጋሜር ልጅ። ምናልባት በእብራይስጥ ፊደል «ዋው» ፈንታ «ኑን» በመሳሳት ስሙ በትክክል «አሽኩዝ» እንደ ሆነ የሚል ግመት አለ። አሽኩዝ እና ኢሽኩዝእስኩቴስ ሰዎች ስሞቻቸው ነበረ። ይኸውም ሕዝብ አንዳንዴ ከአውሮጳና ከእስያ እጅግ ሰፊ ምድር በጥንት ይይዙ ነበር። በአይሁዶች ልማድ ግን አስከናዝ ጀርመንን ያመለክታል።
    • ሪፋት - የጋሜር ልጅ።
    • ቴርጋማ - የጋሜር ልጅ። የአርሜኒያ እንዲሁም የጆርጅያ አፈ ታሪክ ከቴርጋማ መውለዳቸውን ይናግራል። ሌላ ሰዎች ግን ልጆቹ የቱርኪክ ሕዝቦች እንደ ሆኑ ባዮች ናቸው።
  • ማዴ («ማዳይ» በኩፋሌ) - የያፌት ልጅ። በስሜን-ምዕራብ ፋርስ የኖሩ የሜዶን ሰዎች ፤ ኩርዶችም እስካሁን ከሱ እንደተወለዱ ይላሉ።
  • ያዋን («ኢዮአያ»፣ «ኢዮአያን» በኩፋሌ) - የያፌት ልጅ። ይህ ስም የግሪክ ጥንታዊ ነገድ የኢዮንያውያን መነሻ እንደሆነ ይባላል።
    • ኤሊሳ - የያዋን ልጅ። በዮሴፉስ ዘንድ ልጆቹ «አዮሌስ» የተባለው ግሪክ ነገድ ሆነ፣ በሌሎች ትውፊቶች የፖርቱጋል ወይም የጀርመን አባት ሆነ። አሁን ከአላሺያ (ቆጵሮስ) ጋር እንደ ተዛመደ ይታስባል።
    • ተርሴስ - የያዋን ልጅ። በትንሹ እስያ ለሚገኘው ከተማ ጠርሴስ ስሙን እንደ ሰጠ ይታመናል፤ ከዚህ በላይ ስሙን በደቡብ እስፓንያ ላለው አውራጃ ለታርቴሦስ የሰጠ እሱ ነው ባዮች አሉ።
    • ኪቲም - የያዋን ልጅ። በቆጵሮስ ላለው ከተማ ለኪቲዮን ስሙን እንደ ሰጠ ይታመናል፤ ሆኖም ይህ ስም በሌሎች ሰነዶች ልዩ ልዩ ትርጉሞች ይዟል።
    • ሮድኢ - የያዋን ልጅ። አብዛኛው ጊዜ በትንሹ እስያ ዳርቻ አጠገብ ለሚገኘው ታላቅ ደሴት ለሮዶስ ስሙን እንደ ሰጠ ይታመናል።
  • (ይልሳ) - (ይህ የያፌት ልጅ ስም በእብራይስጥ ባይገኝም፣ በአማርኛና በግዕዝ መ.ቅ. መገኘቱ በግሪኩ ስላለ ነው። በዜና መዋዕል ወይም በመጽሐፈ ኩፋሌ የለም። በግሪኩም «ይልሳ» እና «ኤሊሳ» አንድ አጻጻፍ ስላላቸው፣ የያዋን ልጅ ስም በስህተት እንደገና ለያፌት ልጅ እንደ ተጻፈ ይመስላል።)
  • ቶቤል - የያፌት ልጅ። በትንሹ እስያ የተገኘው ሕዝብ ታባላውያን ከሱ እንደ ወጡ ከመባሉ በላይ በካውካሶስ ተራሮች ያሉት ኢቤራውያን እንዲሂም በእስፓንያና በፖርቱጋል ያሉት ኢቤራውያን ደግሞ የኢጣልያና የኢሊርያ ሰዎች ከሱ እንደ ተወለደ ተብሏል። በመጽሐፈ ኩፋሌ ዘንድ ርስቱ ሦስቱ የምድር ልሳናት ነበረ።
  • ሞሳሕ («ሞስክፍ»፣ «ሞሳኮ» በኩፋሌ) - የያፌት ልጅ። - በፍርግያ የኖረው ሙሽካውያን ሕዝብ ስማቸውን ከሱ እንዳገኙ ይባላል። ሙሽካውያን እና ታባላውያን የኬጥያውያን መንግሥት ያፈረሱት ናቸው። ሙሽካውያን ከጆርጅያ ህዝብ አባቶች መካከል የቆጠራሉ፤ ደግሞ በሜዲቴራኔያን ባሕር የዞሩት የባሕር ሕዝቦች ከነሱና ከሌሎች ነበሩ።
  • ቲራስ («ቴራስ» በዜና መዋዕል፤ ደግሞ «ቴሬስ» በኩፋሌ) - የያፌት ልጅ። አብዛኛው ጊዜ ይህ ስም ከጥራክያውያን ጋር ይጠቀሳል። ከዚህ በላይ አንዳንድ ከባሕር ሕዝቦች ነገዶች ለምሳሌ ቱርሻ እና ቲርሴኖይ፤ የድኒስተር ወንዝ ጥንታዊ ስም ቲራስ ወንዝ፤ እና በትንሹ እስያ ስሜን-ምዕራብ የተገኘው ትሮአስ ከዚህ ስም ጋር ግንኙነት እንዳለ ይገመታል።

በአንዳንድ የድሮ እና ዘመናዊ አስተያየቶች ዘንድ የያፌት ስም ከሮማውያን አምላክ ዩፒተር ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚል ክርክር አቅርበዋል። ከዚህ በላይ ከግሪኩ አፈ ታሪካዊ ቅድማያት ከያፔቶስ ጋር ወይም ከሕንድ አፈ ታሪክ ሰው ከፕራ-ጃፓቲ ጋር ግንኙነት እንደ ነበራቸው የሚሉ ጽፈዋል።

በድሮ ታሪከኞች መጻሕፍት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በዮሴፍ ቤን-ማቲትያሁ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
በዮሴፉስ የተገኙት መታወቂያዎች

በ1ኛ ክፍለ ዘመን የጻፈው ሮማዊ-አይሁድ ታሪከኛ ፍላዊዩስ ዮሴፉስ (ዮሴፍ ቤን-ማቲትያሁ) የአይሁዶች ጥንቶች በሚለው መጽሐፍ ውስጥ (1፣ 6) በዘፍጥረት 10 ላሉት ስሞች በየቀገኑ ለማስታወቅ ከሞከሩት አንድ ነው። እሱ የጻፋቸው መታወቂያዎች ለተከታተሉት ደራሲዎች መሠረት ሆነው እንዲህ ነበሩ[2]

  • ጎመር (ጋሜር): «ግሪኮች አሁን 'ገላትያውያን' የሚሏቸው፣ የዛኔ ግን 'ጎሜራውያን' የተባሉት»
    • አስካናክስ (አስከናዝ): «አስካናክሳውያን፣ አሁን በግሪኮች 'ሬጊናውያን' የሚባሉት»
    • ሪጳጥ (ሪፋት): «ሪጴያውያን፣ አሁን 'ፓጵላጎናውያን' ተብለው»
    • ጥሩግራማ (ቴርጋማ): «ጥሩግራሜያውያን፣ ግሪኮች እንደሰየማቸው 'ፍርግያውያን' የተባሉት»
  • ማጎግ: «ማጎጋውያውያን፣ በግሪኮች 'እስኩቴሳውያን' የሚባሉት»
  • ማዳይ (ማዴ): «ማዴያውያን፣ በግሪኮች 'ሜዶናውያን' የሚባሉት»
  • ያዋን: «ኢዮኒያ እና ግሪኮቹ ሁሉ»
    • ኤሊሳ: «ኤሊሴያውያን... አሁንም 'አዮልያውያን' ናቸው።»
    • ጣርሶስ (ተርሴስ): «ጣርስያውያን፣ ኪልቅያ በጥንት እንዲህ ተባለና።» ደግሞ ከተማቸው ጠርሴስ ስለ ጣርሱስ እንደ ተሰየመ ይላል።
    • ከጢሞስ (ኪቲም): «ደሴቲቱ ከጢማ፤ አሁንም ቆጵሮስ ትባላለች።» ደግሞ የከተማቸው ግሪክ ስም ኪቲዮስ ከከጢሙስ ነው ይላል።
  • ጦቤል (ቶቤል): «ጦቤላውያን፣ አሁን 'ኢቤራውያን' የሚባሉት»
  • ሞሶክ (ሞሳሕ): «ሞሶኬናውያን... አሁን ቀጰዶቅያውያን ናቸው።» ደግሞ የዋና ከተማቸው ማዛካ ስም ከሞሶክ ነው ይላል።
  • ጢራስ (ቲራስ): «ጢራሳውያን፤ ግሪኮቹ ግን ስማቸው 'ጥራክያውያን' አደረጉት።»
  • ኩስ (ኩሽ): «እትዮጵያውያን... ዛሬም ቢሆንም በራሳቸውም ሆነ በእስያ ባሉት ሰዎች ሁሉ 'ኩሳውያን' የተባሉ»
    • ሳባስ (ሳባ): ሳባውያን
    • ኤዊላስ (ኤውላጥ): «ኤዊሌያውያን፣ 'ጌቱሊ' የሚባሉ»
    • ሳባጤስ (ሰብታ): «ሳባጤናውያን፣ አሁን ቤግሪኮች 'አስታቦራውያን' ይባላሉ።»
    • ሳባክታስ (ሰብቃታ): ሳባክቴንውያን
    • ራግሞስ (ራዕማ): ራግሜያውያን
      • ዩዳዳስ (ድዳን): «ዩዳድያውያን፣ የምዕራብ ኢትዮጵያውያን ብሔር»
      • ሳባስ (ሳባ): ሳባውያን
  • መስራይም (ምጽራይም): ግብፅ ወይም በሱ አገር «ሜስትሬ» (ምስር) የሚባል
    • «የመስራይምም ልጆን በቁጥር ስምንት ሆነው ከጋዛ እስከ ግብጽ ያለውን አገር ቢያዙም የአንዱን ስም ብቻ ነበራቸው እሱም ፍልስጥኤም ነው፤ ግሪኮች የዛችን አገር ከፊል 'ፓሌስቲና' ይሉታልና። ሌሎቹስ ሉዶዬም፣ ኤነሚምም፣ ሊቢያ ብቻ የኖረበትም አገሩንም ስለራሱ የጠራው ላቢም፣ ነዲምም፣ ጴጥሮሲምም፣ ከስሎዊምም፣ ከፍቶሪምም፣ ስለነሱ ከስሞቻቸው በቀር ምንምን አናውቅም፣ እነዚይ ከተሞች የተገለበጡበት ምክንያት ከዚህ በኋላ የምናስረዳው ኢትዮጵያዊው ጦርነት ነበረና።»
  • ጱት (ፉጥ): ሊቢያ። «በሞራውያን አገር» አንድ ወንዝና ዙሪያ በግሪኮች ዘንድ ገና 'ጱት' ይባል ሲሆን አዲስ ስሙን ግን «ከመስራይም ልጆች መካከል 'ሊብዮስ' ስለተባለው» እንደ ተቀበለ ይነግራል።
  • ከነዓን: ይሁዳ፣ «ከራሱ ስም 'ከነዓን' የሰየመው»
    • ሲዶኒዮስ (ሲዶን): የሲዶኒዮስ ከተማ፣ «በግሪኮች ሲዶን የተባለ»
    • አማጦስ (አማቲ): «አማጢኔ፣ እስከ ዛሬም በኗሪዎቹ 'አማጤ' የሚባል፣ መቄዶናውያን ግን ከዘሮቹ ስለአንዱ 'ኤጲፋኒያ' ብለው ሰየሙት።»
    • አሩዴዮስ (አራዴዎን): «ደሴቲቱ አራዶስ»
    • አሩካስ (ዐሩኬዎን): «በሊባኖስ ያለው አርኬ»
    • «ዳሩ ግን ስለ ሰባት ሌሎቹ (የከነዓን ልጆች) ኬጤዮስ፣ ዬቡሴዮስ፣ አሞሬዮስ፣ ጌርጌሶስ፣ ኤውዴዮስ፣ ሲኔዮስ፣ ሳማሬዮስ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ከስሞቻቸው በቀር ምንምን የለንም፤ ዕብራውያን ከተሞቻቸውን ገለበጡና።»
  • ኤላም: «የፋርሳውያን ቅድማያቶች የሆኑት ኤላማውያን»
  • አሹር: አሦራውያንና በአሦር የተገነባ ከተማቸው ነነዌ
  • አርጳክሳድ (አርፋክስድ): «አርጳክሳዳውያን፣ አሁን ከለዳውያን የሚባሉ»
    • ሳላ
      • ሄበር (ኤቦር): «በመጀመርያ አይሁዶችን 'ዕብራውያን' የጠሩአቸው ከእሱ ነው።»
        • ጳሌግ (ፋሌቅ): «'ፋሌክ' በዕብራውያን ዘንድ 'መለያየት' ማለት ነውና አሕዛብ ወደየአገሩ በመበተናቸው ጊዜ ስለ ተወለደ» እንዲህ እንደ ተሰየመ ያመለክታል።
        • ዮክታን
          • «ኤልሞዳድ፣ ሳሌፍ፣ አሴርሞጥ፣ ዬራ፣ አዶራም፣ አይዜል፣ ዴክላ፣ ኤባል፣ አቢማኤል፣ ሳቤዮስ፣ ኦፊር፣ እዊላትና ዮባብ - እነዚህ ከሕንድ ወንዝ ከኮፈን ጀምሮና ባጠገቡ ባለው በእስያ ክፍል ውስጥ ኖሩ።»
  • አራም: «አራማውያን፣ ግሪኮች 'ሶርያዉያን' ያሏቸው»
  • ላውድ (ሉድ): «ላውዳውያን፣ አሁን 'ልድያውያን' የሚባሉ»

ቅዱስ አቡሊዴስ ዜና መዋዕል (226 ዓ.ም.) በብዙ ሮማይስጥና ግሪክ ቅጂዎች ሲገኝ[3] በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 10 ላሉት ስሞች በየሕዝቡ መታወቂያ ለመስጠት እንደገና ይሞክራል። አንዳንዴ ከዮሴፉስ ውጤት ጋር ተመሳሳይ ቢሆን ልዩነቶቹ ግን ሰፊ ናቸው፣ እነሱም፦

  • ጋሜር - ቀጰዶቅያውያን
    • አስከናዝ - ሳርማትያውያን
    • ሪፋት - ሳውሮማትያውያን
    • ቴርጋማ - አርሜንያውያን
  • ማጎግ - ገላትያውያን፣ ኬልቶች
  • ያዋን
    • ኤሊሳ - ሲኩሊ (የፋሲካ ዜና መዋዕል: ትሮያውያንና ፍርጋውያን)
    • ተርሴስ - ኢበራውያን፣ ቲሬንያውያን
    • ኪቲም - መቄዶናይውያን፣ ሮማውያን፣ ላቲናውያን
  • ቶቤል - «ሔታሊ» (?)
  • ሞሳሕ - እልዋርያውያን
  • ምጽራይም
    • ሉዲም - ልድያውያን
    • ዐናሚም - ጵንፍልያውያን
    • ፈትሩሲም - ሉቅያውያን (1 ቅጂ፦ ቀርጤሳውያን)
    • ቀፍቶሪም - ኪልቅያውያን
  • ፉጥ - ትሮግሎዲታውያን
  • ከነዓን - አፍሪ እና ፊንቄያውያን
  • ዐሩኬዎን - ትሮፖሊታንያውያን
  • ሉድ - ሓሊዞናውያን
  • አርፋክስድ
  • አራም - «ኤትያውያን» (?)

የ346 ዓ.ም. ዜና መዋዕል፣ በክርስቲያን ጸሐፊ ኤጲፋንዮስ ዘሳላሚስ የተጻፈው መጽሐፍ ፓናርዮን (367 ዓ.ም. ገደማ)፣ የፋሲካ ዜና መዋዕል (619 ዓ.ም.)፣ የጅዮርጅያ ታሪከኛ ሙሴ ካጋንካትቫትሲ (7ኛው ክፍለ ዘመን) የጻፈው የአልባንያ ታሪክ እና ዮሐንስ ስኩሊትዜስ የጻፈው የታሪኮች መደምደምያ (1049 ዓ.ም.) ሁሉ የአቡሊዴስን መታወቂያዎች የከተላሉ።


  • ጦቤል: ጤሳልያውያን
  • አርሞት (=?): አረባውያን

በ382 ዓ.ም. ገዳማ የጻፉት ቅዱስ ሄሮኒሙስ (ጀሮም) በጻፉት ጽሕፈት ዕብራይስጥ ጥያቄዎች በዘፍጥረት የዮሴፉስን መታወቂያዎች በአዲስ ዝርዝር አወጣ። የሄሮኒሙስ ዝርዝር በተግባር እንደ ዮሴፉስ ዝርዝር ይመስላል፤ እነዚህ ልዩነቶች ግን አሉ፦

  • የያፌት ልጅ ጡባል (ቶቤል) - «ኢቤራውያን፤ እነሱም ደግሞ ቄልጢበራውያን ከነሱ የተገኙላቸው እስፓንያውያን ናቸው፤ አንዳንድ ሰዎች ግን ኢጣልያውያን መሆናቸውን ይገምታል።»
  • የአራም ልጅ ጌጤር (ጌቴር) - «አካርናንያውያን ወይም ካርያውያን»
  • የአራም ልጅ ማሽ (ሞሶሕ) - ማዮንያውያን

በኢሲዶሬ ዘሰቪሌ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ጳጳሱና መምኅሩ ኢሲዶሬ ዘሰቪሌ 600 ዓ.ም. ገደማ በጻፉት ኤቲሚሎጊያይ የሄሮኒሙስን መታወቂያዎች ሁሉ ይደግማል፣ ከነዚህ ጥቃቅን ልዩነቶች በቀር፦[4]:

  • የኤቦር ልጅ ዮቅጣን - ሕንዳውያን
  • የዮቅጣን ልጅ ሳሌፍ - ባክትርያውያን
  • የያፌት ልጅ ማጎግ - «እስኩቴሳውያንና ጎታውያን»
  • የጋሜር ልጅ አስከናዝ - «ሳርማትያውያን፣ ግሪኮቹ 'ሬጊንያውያን' የሚሏቸው»

የኢሲዶሬ መታወቅያዎች ለያፌት ልጆች እንደገና በሂስቶሪያ ብሪቶኑም ይገኛሉ። የኢሲዶሬ መታወቂያዎች ደግሞ ለብዙ ኋለኞች መካከለኛ ዘመን መምህራን መሠረት ሆኑ።

ዘመናዊ ጥያቄዎች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዘፍጥረት 10 የሚገኘው ትውልድ መጽሐፍ፣ የልጆቹ ስሞች 70 ወይም 72 አገሮችና ቋንቋዎች ሆኑ። ይህ እምነት ለረጅም ዘመን ሳይጠየቅ ተቀበለ። ነገር ግን በቅርቡ ክፍለ ዘመናት የቋንቋ ጥናት ሲመሠረት አዳዲስ ጥያቄዎች በአውሮፓ ተፈጠሩ። ጥያቄዎች የተነሡባቸው ዋን ምክንያቶች፦

በቅዱሳን መጻሕፍት ያልተጠቀሱ የኖህ ልጆች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ኖኅ ከሴም ካምና ያፌት ጭምር ሌላ ልጅ እንደ ተወለደለት የሚናገሩ ልዩ ልዩ ታሪኮች ይገኛሉ። በነዚህ ምንጮች ዘንድ ተጨማሪው ልጅ የሚወለደው ወይም ከማየ አይህ በፊት፣ ወይም በኋላ (ወይም በውሃው ጊዜ እራሱ) በመሆን ይለያል።

ቁራን ሱራ «ሁድ» ዘንድ (11፡42-43) በመርከቡ እንዳይሣፈር እምቢ ያለ ሌላ ወንድ ልጅ ለ ኖኅ ነበረው። በመርከቡ በመሣፈር ፈንታ እሱ በተራራ ወጣና ሰመጠ። አንዳንድ የእስልምና ጸሐፊ ስሙ ወይም ያም ወይም ከነዓን እንደ ነበር ጽፏል።

አይርላንድ አፈ ታሪክ ዘንድ፣ በመርከቡ ለመሣፈር ያልተፈቀደ ቢጥ የተባለ ሌላ ወንድ ልጅ ለኖኅ ነበረው። በዚህ ታሪክ መሠረት ቢጥ ከዚያ በኋላ ወደ አይርላንድ ከነቤተሠቡ (በጠቅላላ 54 ሰዎች) ቢፈልሱም፣ ሁላቸው በማየ አይኅ ግን ሰጠሙ።

በ9ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. በተጻፈ የአንግሎ-ሳክሰን ዜና መዋዕል ዘንድ፣ ሼይፍዌሰክሽ ሥርወ መንግሥት ቅድማያት ሲባል በመርከቡ ላይ የተወለደ የኖህ አራተኛ ወንድ ልጅ መሆኑ ይነገራል። በ1112 ዓ.ም. ገደማ ዊልያም ኦፍ ማልምዝቡሪ የእንግሊዝ ነገሥታት ትውልድ ጽፎ ግን ይህ ሼይፍ በመርከቡ ላይ ከተወለደው ከኖህ አራተኛው ወንድ ልጅ ከስትሬፊዩስ ዘር እንደ ነበር ብሏል።

ኪታብ አል-ማጋል የተባለው ጥንታዊ አረብኛ መጽሐፍ (ከ«ቄሌምንጦስ መጻሕፍት» መሃል) እንደሚለው የኖህ አራተኛ ወንድ ልጅ ቡኒተር ከማየ አይኅ ቀጥሎ ተወልዶ ሥነ ፈለክም ፈጥሮ የናምሩድ አስተማሪ ሆነ[5]። ለዚህ ተመሳሳይ ታሪኮች ለኖህ አራተኛ ልጅ የተለያዩ አጠራሮች ሲሰጡት ይታያል። ከነዚህም ጥንታዊው የግዕዝ ሰነድ መጽሐፈ አዳምና ሕይዋን (ስሙ ባርዊን ሆኖ)፤ ጥንታዊው የጽርዕ ሰነድ የመዝገቦች ዋሻ (ዮንቶን)፤ ፕሲውዶ- ('ሐሰተኛ') ሜቶድዮስ በተባለው ሰነድ (ዮኒቱስ[6])፣ በጽርዕ በ1213 ዓ.ም. የተጻፈው መጽሐፈ ንቡ (ዮናቶን)፤ በዕብራይስጥ በ12ኛው-14ኛው መቶ ዘመን አካባቢ የተጻፈው የይረሕምኤል ዜና መዋዕል (ዮኒጠስ)፣ እና በበርካታ አርሜንኛ ራዕዮች ውስጥ ማኒቶን ይባላል። ከዚህም በላይ ስለ ኖህ 4ኛ ወንድ ልጅ ተመሳሳይ ታሪኮች በጸሐፊዎቹ ጴጥሮስ ኮሜስቶር በ1152 ዓ.ም. ገደማ (ዮኒጡስ)፣ ጎድፍሬይ ዘቪቴርቦ 1177 ዓ.ም. (ኢሆኒቱስ)፤ ሚካኤል ሶርያዊው 1188 ዓ.ም. (ማኒቶን)፤ አቡ ሳሊኅ አርመናዊው 1200 ዓ.ም. ገደማ (አቡ ናይጡር)፤ ያዕቆብ ቫን ማይርላንት 1232 ገደማ (ዮኒቱስ)፤ አብርሃም ዛኩቶ 1496 ዓ.ም. (ዮኒኮ) እና ይሒኤል ቤን ሰሎሞን ሃይልፕሪን 1689 ዓ.ም. ገደማ (ዩኒኩ)።[7]

ማርቲን ዘኦፓቫ (1240 ዓ.ም. ገደማ)፣ የሚራቢሊያ ዑርቢስ ሮማይ ኋለኛ ቅጂዎች፣ እና የጆቫኒ ዲ ማሪንዮላ ክሮኒኮን ቦሄሞሩም (1347 ዓ.ም.) ሁላቸው ሲስማሙ፣ ወደ ጣልያን አገር ፈልሶ ሥነ ፈለክን ፈጥሮ ናምሩድንም ያስተማረው የኖህ አራተኛ ወንድ ልጅ ያኑስ ነበረ (የሮማ አረመኔው አምላክ 'ያኑስ' ሆነ ለማለት ነው)።

በመነኩሴው አኒዮ ዳ ቪቴርቦ ዘንድ (1490 ዓ.ም.)፣ በግሪኮች ዘመን (~300 ዓክልበ) በባቢሎን የጻፈው ታሪከኛ ቤሮሶስ ለኖኅ ከማየ አይኅ በኋላ 30 ልጆች እንደ ተወለዱለት ጽፎ ነበር። ከነዚህም መካከል ቱዊስኮንጵሮሜጤዎስያፔቶስ፣ ማክሮስ፣ «16 ቲታኖች»፣ ክራኖስ፣ ግራናዎስ፣ ውቅያኖስ እና ቲፌዮስ የተባሉ ወንድ ልጆች በስም ይጠቀሳሉ። ደግሞ የኖኅ ሴት ልጆች አራክሳ «ታላቂቱ»፣ ሬጊና፣ ፓንዶራ፣ ክራና እና ጤቲስ ይባላሉ። ነገር ግን አኒዮ ያገኘው ሰነድ የቤሮሶስ ሳይሆን ሐሰተኛ መሆኑ ዛሬ አይጠረጠርም[8]

  1. ^ የኢኦተቤ ታሪክ
  2. ^ Antiquities of the Jews - Book I
  3. ^ Die Chronik des Hippolytus
  4. ^ Etymologies of Isidore, English translation
  5. ^ Seth in Jewish, Christian, and Gnostic Literature p. 54
  6. ^ S.P. Brock እንደሚጽፍ፣ በፕሲውዶ ሜቶድዮስ የቀደሙት ግሪክኛ ቅጂዎች ስሙን ሞኔቶን ሲሉ የጽርዕ ቅጂዎች ዮንጦን አላቸው(Armenian Apocrypha, p. 117)።
  7. ^ Looking for Jonitus by by C.J. Verduin
  8. ^ Travels of Noah into Europe

የውጭ ድረገጾች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]