Jump to content

ደቂቅ ዘአካላት

ከውክፔዲያ
10,000 ጊዜ ተልቆ የተነሳ የኮሊ ባክቴሪያ

ደቂቅ ዘ አካላት ወይም በእንግሊዝኛ Microorganisms የሚባሉት በአጉሊ መነጽር ብቻ የሚታዩ ማለትም በባዶ ዓይን የማይታዩ አካላት ናቸው። የነዚህ አካላት ጥናት microbiology ይባላል። ይህም ጥናት የተጀመረው በአንቶን ቫን ሉዊንሁክ ሲሆን በ1675 እ.ኤ.አ. የራሱን የአጉሊ መነጽር ተጠቅሞ የመጀመሪያዎቹን ደቂቅ ዘ አካላት በማግኘቱ ነው።

አርኬአዎች ቅድመኑክለሳዊ አንድህዋሴ አካላት ሲሆኑ፣ በካርል ዎሴ ባለ ሶስት ጎራ ስርዓተ ምደባ መሰረት የመጀመሪያውን ሕይወት ያላቸው አካላት ጎራ ይመሰርታሉ።  ቅድመ ኑክለሳዊ የሚለው ቃል ሲተረጎም ኑክለስና ሌሎች በክርታስ የተሸፈኑ ክፍለ ህዋሳት የሌሉት ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።  አርኬአዎች ቀደም ሲል በአንድ ጎራ አብረዋቸው ተመድበው ከነበሩት ከባክቴሪያ ጋር ይህን ትርጓሜ ይጋራሉ።

አርኬአዎች ከባክቴሪያ የሚለዩት በስነባሕርያቸው እና በባዮኬሚስትሪያቸው ነው። ለምሳሌ የባክቴርያ ሕዋስ ክርታስ የተሰራው ከፎስፎግላይሴራይዶች በኤስተር ቦንድ አማካኝነት ሲሆን፤ የአርኬአዎች ክርታስ ግን የተሰራው ከኢተር ሊፒዶች ነው።[1]

ባክቴሪያዎች ቅድመኑክለሳዊ ማለትም ፦ ኑክለስና ሌሎች በክርታስ የተሸፈኑ ክፍለ ህዋሳት የሌሏቸው መሆናቸው ከአርኬአዎች ጋር ያመሳስላቸዋል። እንደ ታዮማርጋሪታ ናሚቢየንሲስ እጅግ በጣም ጥቂት ወጣ ያሉ ዝርያዎች በስተቀር ባክቴሪያዎች በሙሉ ያለ ማይክሮስኮፕ የማይታዩ ደቂቅ ዘአካላት ናቸው።[2]

ውን ኑክለሳውያን በውስጣቸው እንደ ህዋስ ኑክለስ፣ ጎልጂ እቃ እና ኃይለህዋስ ያሉ ክፍለ ህዋሳት ያሏቸው መሆናቸው ከባክቴሪያዎችና ከአርኬአዎች ይለያቸዋል።

ከውን ኑክለሳውያን ጎራ መካከል ፕሮቲስታዎች በብዛት አንድህዋሴ የሆኑ ሚክሮስኮፓውያን ናቸው።ይህ ጎራ ለምደባ አስቸጋሪ የሆኑ ሰፊ ተልያይነት ያላቸው ፍጡራንን ያቀፈ ነው።[3]ባለብዙ ህዋስ የሆኑ ብዙ የዋቅላሚ ዝርያዎች ፕሮቲስታዎች ናቸው። በፕሮቲስታ ውስጥ የሚገኙ ዝርያዎች ቁጥር በውል አይታወቅም፤ ምክኒያቱም በዚህ ሰፍን ውስጥ የሚገኙ የተለዩ ዝርያዎች በጣም ጥቂት ስለሆኑ ነው።

ፈንገሶች እንደ የዳቦ እርሾ (ሳካሮማይሰስ ሰርቪሴ) ያሉ ብዙ አንድህዋሴ ዝርያዎች አሏቸው።

ዋቅላሚ የሚለው ቃል ከተለያዩ ስርወዘራዊ ቡድኖች የተገኙ እና በተለያዩ የሥርዓተ ምደባ ዘርፎች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሕይወት ያላቸው ፍጡራንን የሚወክል ሰፊ ቡድን ነው። በአጠቃላይ ዋቅላሚዎች ስንል እያልን ያለነው፦ በአብዛኛው እውነተኛ ስር፣ግንድ፣ ቅጠል እና ሥርአተሸንዳ የሌላቸው ባለ ቀላል የመራቢያ መዋቅር የሆኑ እና ምግብሰሪ የሆኑ የውሃውስጥ ዕፅዋትመሰል ፍጡራንን ነው። በመላው ዓለም ማለትም፦ በባሕር፣ በጨው አልባ ዉሃማ አካላት እና እርጥበታማ የየብስ ክፍሎች ተሰራጭተው ይገኛሉ። አብዛኛዎቹ ሚክሮስኮፓዊ ሲሆኑ ጥቂቶች ግን በጣም ግዙፎች ናቸው። ለምሳሌ አንዳንድ የባሕር ውስጥ አረሞች (sea weeds) እስከ ፶ ሜትር ያህል ሊረዝሙ ይችላሉ። [4]

አረንጓዴ ዋቅላሚዎች ብርሃናዊ አስተፃምሮ ማከናወን የሚችሉ ብዙ ውን ኑክለሳውያንን የሚያቅፍ ሰፊ ቡድን ነው። ምንም እንኳን ጥቂት አረንጓዴ ዋቅላሚዎች ከፕሮቲስታዎች ጋር የሚመደቡ ቢሆንም፣ እንደ ክሎሮፋይታ ያሉ ሌሎች ዋቅላሚዎች በዕፅዋት ውስጥ የመደባሉ። እንደ ክላሚዶሞናስ ያሉ በጣም ብዙ አንድህዋሴ የሆኑ አረንጓዴ ዋቅላሚዎች አሉ።




  1. ^ De Rosa, M.; Gambacorta, A.; Gliozzi, A. (1 March 1986). "Structure, biosynthesis, and physicochemical properties of archaebacterial lipids". Microbiol. Rev. 50 (1): 70–80. doi:10.1128/mmbr.50.1.70-80.1986. PMC 373054. PMID 3083222
  2. ^ Schulz, H.; Jorgensen, B. (2001). "Big bacteria". Annu Rev Microbiol. 55: 105–37. doi:10.1146/annurev.micro.55.1.105. PMID 11544351
  3. ^ Cavalier-Smith T (1 December 1993). "Kingdom protozoa and its 18 phyla". Microbiol. Rev. 57 (4): 953–994. doi:10.1128/mmbr.57.4.953-994.1993. PMC 372943. PMID 8302218.
  4. ^ https://www.lenntech.com/eutrophication-water bodies/algae.htm#ixzz6aq4M83Vi