፩ኛ ወደ ቆሮንጦስ ፫
፩ኛ ወደ ቆሮንጦስ ፫ | |
---|---|
| |
አጭር መግለጫ | |
ፀሐፊ | ጳውሎስ |
የመጽሐፍ ዐርስት | ፩ኛ ወደ ቆሮንጦስ |
የሚገኘው | በአዲስ ኪዳን ፯ኛው መጽሐፍ |
መደብ | የጳውሎስ መልዕክት |
፩ኛ ወደ ቆሮንጦስ በአዲስ ኪዳን ሁለተኛው መልዕክት ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንጦስ እያለ በ፶ ዎቹ ዓ.ም. ለቆሮንጦስ ሰዎች የጻፈው የመጀመሪያ መልዕክት ነው ። ፲፮ ምዕራፎች ይይዛል ። ይህ ፫ኛ ምዕራፍ ሲሆን በ፳፫ ንዑስ ክፍሎች ይከፈላል ።
ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች መልዕክት የጻፈበት ምክኒያት ብዙ ሲሆን ከብዙዎች በጥቂቱ ፣ ከመምህሮቻቸው መዐረግ ሳይደርሱ ደረስን እያሉ በብዙ ቐንቐ በሚናገሩ መምህሮቻቸው እንደነ ራሱ ፣ ጳውሎስ ፣ አጵሎስ... ላይ የሚታበዩ ስለተነሱ ለነዚህ እንደ ዘለፋ እንዲሆን ፤
በቆሮንቶስ ምዕመናን መሀከል መከፋፈላቸውን ሰምቶ ከዚህ ስህታቸው እንዲታረሙ ፤ በተጨማሪም ዓለምን ለማሳፈር እግዚአብሔር ታላቁን ሚሥጥር በዓለም በተናቁት ሰዎች እንዲገለፅ ማድረጉን ለማሳወቅ ጻፈው ።
የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ፩ኛ ወደ ቆሮንጦስ ምዕራፍ ፫
1፤እኔም፥ወንድሞች፡ሆይ፥የሥጋ፡እንደ፡መኾናችኹ፥በክርስቶስም፡ሕፃናት፡እንደ፡መኾናችኹ፡እንጂ፡ መንፈሳውያን፡እንደ፡መኾናችኹ፡ልናገራችኹ፡አልቻልኹም። 2፤ገና፡ጽኑ፡መብል፡ለመብላት፡አትችሉም፡ነበርና፥ወተት፡ጋትዃችኹ፤ 3፤ገና፡ሥጋውያን፡ናችኹና፥እስከ፡አኹን፡ድረስ፡ገና፡አትችሉም።ቅናትና፡ክርክር፡ስለሚገኝባችኹ፡ ሥጋውያን፡መኾናችኹ፡አይደላችኹምን፧እንደ፡ሰው፡ልማድስ፡አትመላለሱምን፧ 4፤አንዱ፦እኔ፡የጳውሎስ፡ነኝ፥ኹለተኛውም፦እኔ፡የአጵሎስ፡ነኝ፡ቢል፡ሰዎች፡ብቻ፡መኾናችኹ፡ አይደለምን፧ 5፤አጵሎስ፡እንግዲህ፡ምንድር፡ነው፧ጳውሎስስ፡ምንድር፡ነው፧በእነርሱ፡እጅ፡ያመናችኹ፡አገልጋዮች፡ ናቸው፤ለያንዳንዳቸውም፡ጌታ፡እንደ፡ሰጣቸው፡ያገለግላሉ። 6፤እኔ፡ተከልኹ፡አጵሎስም፡አጠጣ፥ነገር፡ግን፥እግዚአብሔር፡ያሳድግ፡ነበር፤ 7፤እንግዲያስ፡የሚያሳድግ፡እግዚአብሔር፡እንጂ፡የሚተክል፡ቢኾን፡ወይም፡የሚያጠጣ፡ቢኾን፡አንዳች፡ አይደለም። 8፤የሚተክልና፡የሚያጠጣ፡አንድ፡ናቸው፥ነገር፡ግን፥እያንዳንዱ፡እንደ፡ራሱ፡ድካም፡መጠን፡የራሱን፡ ደመ፡ወዝ፡ይቀበላል። 9፤የእግዚአብሔር፡ዕርሻ፡ናችኹ፤የእግዚአብሔር፡ሕንፃ፡ናችኹ፤ከርሱ፡ጋራ፡ዐብረን፡የምንሠራ፡ነንና። 10፤የእግዚአብሔር፡ጸጋ፡እንደተሰጠኝ፡መጠን፡እንደ፡ብልኀተኛ፡የዐናጺ፡አለቃ፡መሠረትን፡ መሠረትኹ፥ሌላውም፡በላዩ፡ያንጻል። እያንዳንዱ፡ግን፡በርሱ፡ላይ፡እንዴት፡እንዲያንጽ፡ይጠንቀቅ።
11፤ከተመሠረተው፡በቀር፡ማንም፡ሌላ፡መሠረት፡ሊመሠርት፡አይችልምና፥ርሱም፡ኢየሱስ፡ክርስቶስ፡ነው። 12፤ማንም፡ግን፡በዚህ፡መሠረት፡ላይ፡በወርቅ፡ቢኾን፡በብርም፡በከበረ፡ድንጋይም፡በዕንጨትም፡በሣርም፡ ወይም፡በአገዳ፡ቢያንጽ፥የያንዳንዱ፡ሥራ፡ይገለጣል፤ 13፤በእሳት፡ስለሚገለጥ፡ያ፡ቀን፡ያሳያልና፥የያንዳንዱም፡ሥራ፡እንዴት፡መኾኑን፡እሳቱ፡ይፈትነዋል። 14፤ማንም፡በርሱ፡ላይ፡ያነጸው፡ሥራ፡ቢጸናለት፡ደመ፡ወዙን፡ይቀበላል፤ 15፤የማንም፡ሥራ፡የተቃጠለበት፡ቢኾን፡ይጐዳበታል፥ርሱ፡ራሱ፡ግን፡ይድናል፥ነገር፡ግን፥በእሳት፡እንደሚድን፡ይኾናል። 16፤የእግዚአብሔር፡ቤተ፡መቅደስ፡እንደ፡ኾናችኹ፡የእግዚአብሔርም፡መንፈስ፡እንዲኖርባችኹ፡አታውቁምን፧ 17፤ማንም፡የእግዚአብሔርን፡ቤተ፡መቅደስ፡ቢያፈርስ፡እግዚአብሔር፡ርሱን፡ያፈርሰዋል፤የእግዚአብሔር፡ቤተ፡ መቅደስ፡ቅዱስ፡ነውና፥ያውም፡እናንተ፡ናችኹ። 18፤ማንም፡ራሱን፡አያታል፟፤ከእናንተ፡ማንም፡በዚች፡ዓለም፡ጥበበኛ፡የኾነ፡ቢመስለው፡ጥበበኛ፡ይኾን፡ ዘንድ፡ሞኝ፡ይኹን። 19-20፤የዚች፡ዓለም፡ጥበብ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ሞኝነት፡ነውና፦ርሱ፡ጥበበኛዎችን፡በተንኰላቸው፡ የሚይዝ፤ደግሞም፦ጌታ፡የጥበበኛዎችን፡ዐሳብ፡ከንቱ፡እንደ፡ኾነ፡ያውቃል፡ተብሎ፡ተጽፏልና። 21፤ስለዚህም፡ማንም፡በሰው፡አይመካ።ነገር፡ዅሉ፡የእናንተ፡ነውና፤ 22፤ጳውሎስ፡ቢኾን፡አጵሎስም፡ቢኾን፡ኬፋም፡ቢኾን፡ዓለምም፡ቢኾን፡ሕይወትም፡ቢኾን፡ሞትም፡ቢኾን፡ያለውም፡ቢኾን፡የሚመጣውም፡ቢኾን፥ 23፤ዅሉ፡የእናንተ፡ነው፥እናንተም፡የክርስቶስ፡ናችኹ፡ክርስቶስም፡የእግዚአብሔር፡ነው።