3 ሰኑስረት
==
3 ሰኑስረት | |
---|---|
የኻኻውሬ ምስል | |
የግብጽ ፈርዖን | |
ግዛት | 1888-1859 ዓክልበ. |
ቀዳሚ | 2 ሰኑስረት |
ተከታይ | 3 አመነምሃት |
ሥርወ-መንግሥት | 12ኛው ሥርወ መንግሥት |
አባት | 2 ሰኑስረት |
==
ኻኻውሬ፣ ፫ ሰኑስረት ግብጽን በመካከለኛ መንግሥት (12ኛው ሥርወ መንግሥት) ከ1888 እስከ 1859 ዓክልበ. ግድም ድረስ የገዛ ፈርዖን ነበረ። የአባቱ 2 ሰኑስረት ተከታይ ነበር።
በኻይከፐሬ 2 ሰኑስረት ዘመነ መንግሥት በ1898 ዓክልበ. ግድም ልጁን ፫ ሰኑስረት ከእርሱ ጋር በጋርዮሽ ወደ ዙፋኑ እንዳስነሣው ይመስላል። አለዚያ በ1898 ዓክልበ. ግድም ፪ ሰኑስረት ዓርፎ ፫ ሰኑስረት በቀጥታ የተከተለው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ የ፫ ሰኑስረት ዘመን መጀመርያ ዓመት የሚቆጠር ከ1898 ዓክልበ. ግድም ይሆናል። በጠቅላላ ፴፱ ዓመታት እንደ ገዛ ይታወቃል።
ማኔጦን ለ፪ ሰኑስረት እና ለተከታዩ ፫ ሰኑስረት ፈንታ ለሁለቱ አንድ ስም ብቻ አለው፤ እሱም ሴሶስትሪስ ሲሆን ለ፵፰ ዓመታት እንደ ገዛ ይለናል። ይሄ ሴሶስትሪስ እስከ እስኩቴስ ድረስ የዘመተ በአፈ ታሪክ (ዲዮዶሮስና ሄሮዶቶስ) ይባላል። ፫ ሰኑስረት ቢያንስ በከነዓን እንደ ዘመተ ይታወቃል፤ ለ፪ ሰኑስረት ግን ምንም ዘመቻ አይታወቅም። የቶሪኖ ቀኖና የሚባለው የፈርዖኖች ዝርዝር ሰነድ ሁለቱንም ይለያል፤ ለ፪ ሰኑስረት ፲፱ ዓመታትና ለ፫ ሰኑስረት ፴ አመታት ይሠጣል።
በ፰ኛው ዓመት ወይም በ1891 ዓክልበ. በኩሽ መንግሥት ላይ ዘመተ፤ ጠረፉን ከ፪ኛው ፏፏቴ ደቡብ አስፋፍቶ አምባ በሰምና መሠረተ። እንደገና በ1889፣ በ1883 እና በ1880 ዓክልበ. በኩሽ ላይ ዘመተ። በ1880 የሆነው ዘመቻ ግን ከኩሽ መሸሽ ነበረበት። ከ1883 በፊት 3 ሰኑስረት ደግሞ በ«መንቱ» (ምድያም)ና በረጨኑ (ከነዓን) ላይ ዘምቶ፣ በ«ሰክመም» (ሴኬም) እንዳሸነፋቸው የሚል የሰበክ-ሁ ጽላት አለ።
በ፳ኛው አመት ወይም በ1879 ዓክልበ. ልጁን 3 አመነምሃት የጋርዮሽ ፈርዖን አደረገው። ከጠቅላይ ሚንስትሮቹ ሶበከምሃት፣ ነቢትና ኽኑምሆተፕ ይታወቃሉ፤ ባጅሮንዱም ኢኸርኖፍረት ይታወቃል።
ቀዳሚው 2 ሰኑስረት |
የግብፅ ፈርዖን | ተከታይ 3 አመነምሃት |
-
የኻኻውሬ እስፊንክስ ራስ
-
የኻኻውሬ ኦሲሪስ ራስ
-
ሌላ ምስል
-
ሌሎች ምስሎች