Jump to content

ጋሊልዮ

ከውክፔዲያ
ጋሊልዩ ጋሊሊ

ጋሊልዮ ጋሊሊ ታህሳስ 15, 1564ጥር 8, 1642 የነበረ የጣሊያን ሥነ-ፈለክ አጥኝና ተመራማሪ ነበር።

ጋሊልዩ በዘመኑ የራሱን አጉሊ መነጽር በመስራት ጨረቃ ተራራ እንዳላት፣ጁፒተር የተባለው ፈለክ ልክ እንደ መሬት የራሱ የሆኑ 79 ጨረቃወች እንዳሉት፣ ህብረ ከዋክብት ከከዋክብት ስብስብ እንደተሰሩ፣ ፀሐይ ጥቁር ነጠብጣቦች እንዳሏት፣ ቬነስ ልክ እንደ ጨረቃ የተለያየ ቅርጽ በጥልቁ እንደምትይዝ የመሰከረና በኋላም መጽሃፍ ጽፎ ያሳተመ ሳይንቲስት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ጋሊልዮ የተፈጥሮ ህጎችን/ጉልበቶችን አጥንቷል። በትውፊት እንደሚነገር ጣልያን ውስጥ ባለው የተንጋደደው የፒሳ ግንብ ላይ በመውጣት፣ የተለያዩ ክብደት ያላቸውን የብረት ኳሶች ወደመሬት በመልቀቅ፣ ሁሉም በዕኩል ሰዓት መሬትን እንደሚመቱ አረጋግጧል። ከዚህ በመነሳት እስከሱ ዘመን ይሰራበት የነበረውን የአሪስቶትል አስተሳሰብ (ከባድ ነገሮች ከቀላል ነገሮች በበለጠ ፍጥነት ወደመሬት ይወድቃሉ) ፉርሽ አድርጓል። ሆኖም ግን በጊዜው የአሪስቶትል አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ህሊና ውስጥ በጥብቅ ስለሰረጸ ቆይቶ አይዛክ ኒውተን የጋሊልዮን አስተሳሰብ ልክ መሆኑን በጥናቱ እስካረጋገጠበት ድረስ የአሪስቶትል አስተሳሰብ ተቀባይነት ነበረው።

ጋሊልዩ የብርሃንፍጥነት ለማግኘትም ሞክሮ ነበር። ሙከራውም እንዲህ ነበር፡ ቀኑ ሲጨልም እሱና ፀሐፊው ሁለት ራቅ ያሉ የተለያዩ ኮረብታወች ላይ ወጡ። ሁለቱም የተሸፈነ ፋኖስ ይዘው ነበር። ከዚያ ጋሊልዮ የራሱን ፋኖስ መሸፈኛ ሲያነሳ ፀሐፊው ይህን እንዳየ የራሱን ፋኖስ መሸፈኛ አነሳ። በዚህ መንገድ ፀሓፊው የራሱን ፋኖስ ለመክፈት የወሰደበትን ጊዜ ጋሊልዮ ለካ። በኮረብታወቹ መካከል ያለውን ርቀት እና የጊዜውን ሊዩነት ግምት ውስጥ በማስገባት የብርሃንን ፍጥነት ለመገመት ቻለ። ሙከራው ብርሃን ፍጥነት እንዳለውና በቅጽበት እንደማይጓዝ በትክክል ቢያሳይም ጋሊልዩ የለካው ፍጥነት መጠን ግን ትክክል አልነበረም። አይንን ለመግለጥ እና እጅን ለማንቀሳቀስ የሚወስደው ጊዜ ከብርሃን ፍጥነት ጋር ሲወዳደር ብዙ ስለሆነ ሙከራው ትክክል እንደማይሆን ሳይታለም የተፈታ ነበር።

ጋሊልዩ ከሱ ቀድሞ የተነሳውን የኮፐርኒከስን ሃሳብ (መሬት ሳትሆን ፀሓይ የአለም መካከለኛ ናት) በመደገፉ በካቶሊክ ቤ/ክርስቲያን ለእስር ተዳርጎ ነበር። ይህም በዚያ ዘመን የነበሩ የቤ/ክርስቲያኒቱ አዋቂወች ያምኑት እንደነበረው መሬት ቆማ ሌላው አለም ሁሉ በመሬት ዙሪያ ይሽከረከራሉ የሚለውን ስለተቃወመ ነበር። ከዚህ በኋላ እስከ አረፈበት 1642 ድረስ የቤት እስረኛ ሆኖ ዘልቋል። በቅርቡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የሮማው ፓፓ ጆን ፓውል 2ኛ ጋሊልዮን "የተፈጥሮ ህግጋት ጥናት] አባት" በማለት የካቶሊክ ቤ/ክርስቲያ ከ400 አመት በፊት በጋሊልዮ ላይ ለፈጸመችው ግፍ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ዋቢ ጽሁፎች