Jump to content

አሻንቲ መንግሥት

ከውክፔዲያ
አሻንቲ መንግሥት

አሻንቲ መንግሥት1662 እስከ 1949 ዓም ድረስ በዛሬው ጋና አካባቢ የነበረ ግዛት ነው። ከአካን ብሔር ግዛቶች አንዱ ነበር። የብሔሩ ስም በአካንኛ በትክክል «አሳንቴ»፣ የአገሩም ስም «አሳንቴማን» ተብሎ ይጠራል። ይህም ከአካንኛ «አሳ» (ጦርነት) እና «-ንቴ» (ስለ) ወይም «ስለ ጦር» ለማለት ነው። «አሻንቲ» የሚለው አጠራር ከእንግሊዝኛው አጻጻፍ የተነሳ አጠራር ሲሆን፣ በአሁኑ ዘመን በጋና ውስጥ ተቀባይነት አለው።

አካን የተባሉት ብሔሮች ከጥንቱ ጋና መንግሥት (በዛሬው ማሊሞሪታኒያ) ከ1068 ዓም በኋላ እንደ ፈለሱ ይነገራል። በዚያን ጊዜ መጀመርያውን አካን ግዛት ቦኖማን መንግሥት መሠረቱ። አገራቸው የወርቅ ማዕድን በብዛት የተገኘበት በመሆኑ በንግዱ ምክንያት ይበልጸግ ነበር። ከ1500 ዓም በኋላ የተለያዩ ተወዳዳሪ ግዛቶች ነበሩ፤ ዋነኛውም እስከ 1692 ዓም ያህል ድረስ የደንክዪራ መንግሥት ሆኖ ነበር። በዚያው ዓመት የአሻንቲ ንጉሥ ኦሰይ ቱቱ ደንክዪራን በማሸንፍ ዋናው ላዕላይ ግዛት ሆነ። የአሻንቲ ንጉሥ ማዕረግ አሳንቴሄኔ ይባል ነበር። በዚህ ዘመን በትውፊታቸው ዘንድ ወርቁ በርጩማ የተባለው ከሰማይ ወረደና የአሻንቲ ነገሥታት ዙፋን ሆነ።

የአሳንቴ ጦር መኮንን፣ 1811 ዓም አካባቢ
አሻንቲ ፎንቶምፍሮም ወይም ነጋሪት ከበሮ

አሻንቲ ደግሞ ፎንቶንፍሮም የተባለ ነጋሪት ከበሮ ፈጠሩ። አካንኛ እና በምዕራብ አፍሪካ ያሉ ብዙ ቋንቋዎች እንደ ቻይንኛ በመምሰል የድምጽ ቃና ያለባቸው ልሳናት ሲሆኑ፣ ይኸው ነጋሪት ቃናዎቹን በትክክል ማስገኘት ስለሚችል፣ በሙሉ አረፍተ ነገር ለመነጋገር ስለሚያስችል፣ የነጋሪት ቋንቋ የተማሩት ጎበዞች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው መልእክት እንደ ቴሌግራፍ በፍጥነትና በርቀት ሊያደርሱ ቻሉ።

ከ1800 ዓም በኋላ ሥራዊታቸው ጠመንጃ ይይዝ ነበር። ከጎረቤቶታቸው በተለይም ከፋንቲ ብሔር በጦርነቶች ይታግሉ ነበር። ሁለቱ ወገኖች ከተማረኩት ቁጥር ወደ ባርነት ይሸጡ ነበር። ከዚያ በኋላ ከ1815 እስከ 1888 ዓም ድረስ የአሳንቴማን ሥራዊት ከብሪታንያ ጋራ አራት ጦርነቶች ተዋጉ። በሦስቱ ጦርነቶች (1815፣ 1855፣ 1866 ዓም) ብሪታንያ አገሩን ቢወረሩም ሊገዙት አልቻሉም። በመጨረሻው ጦርነት ግን በ1888 ዓም የብሪታንያ ሃያላት ድል አድርገው የአሳንቴ ግዛት ያዙ። አሳንቴ ብሔር በ1892 ዓም ካመጹ በኋላ፣ በ1894 ዓም ብሪታን የጎልድ ኮስት ጥብቅ አገር አለው። በ1927 ዓም አሳንቴሄኔው እንዲመልስና አሳንቴ ብሔር ራስ-ገዥ ሁኔታ እንዲያገኙ ተፈቀደላቸው። በ1949 ዓም ዘመናዊው ጋና አገር ሲመሠረት፣ የአሳንቴማን ግዛት አሁን «አሻንቲ ክልል» ተብሎ ከጋና ጋር ተባበረ፤ እስካሁንም አሳንቴሄኔው በክብር ይቀመጣል።