ሉግ

ከውክፔዲያ
የሉግ ግሩም ጦር በውግያ ጊዜ፣ 1897 ዓ.ም. እንደ ተሳለ

ሉግ «ላምፋዳ» በአየርላንድ ልማዳዊ አፈ ታሪክ ዘንድ ከቱዋጣ ዴ ዳናን ወገን የአየርላንድ ከፍተኛ ንጉሥ ነበር። አባቱ የቱዋጣ ዴ አለቃ ክየን ሲሆን እናቱ ፎሞራዊት ኤጥኒው ነበረች። ክየን ልጁን ሉግን ለቀድሞው ፊር ቦልግ ንጉሥ ዮካይድ ማክ ኤይርክ ሚስት ለታይልቲው አሳዳጊነት ሰጠው ይባላል።

ኑዋዳ ለ፳ ዓመታት ገዝቶ በ1474 ዓክልበ. ብሬስ በፎሞራውያን እርዳታ ተመልሶ ኑዋዳን ተዋግቶ በሁለተኛው የማግ ቱይረድ ውግያ ተሸነፈ። ሆኖም ኑዋዳ እራሱ በዚሁ ውግያ ተገድሎ የዛኔ ሉግ ተከተለው። ብሬስ ተማርኮ ለሕዝቡ ግብርና ቢያስተምር እንዲኖር ተፈቀደ። በኋላ ግን ሉግ በተንኮል ብሬስን ገደለው። እንደ ትውፊቱ፣ ሉግ ፫ መቶ የእንጨት ላሞች ሠርቶ በፋንዲያ ሞላቸው፣ ብሬስንም ተጋብዞ ከዚህ ሲጠጣ ሞተ።

ሉግ ወደ አይርላንድ ካስገባቸው ልማዶች መካከል ፍድቀል (የሠንጠረዥ ዓይነት ጨዋታ)፣ ኳስ፣ እና የፈረስ እሽቅድድም ይጠቀሳሉ። በትውፊቶቹ ዘንድ የሉግ ጦር ግሩም ወይም ታምራዊ አይነት ነበር፤ ሲጣል ሁልጊዜ ዒላማውን አገኘና በቀጥታ ተመለሠ ይባላል።

ዳግዳ ልጅ ኬርማይት ከሉግ ሚስት ጋር ካመነዘረ በኋላ ሉግ ኬርማይትን ገደለው። የኬርማይትም ልጅ ማክ ኲል ቂሙን በቅሎ ሉግን ገደለው። በሉግም ፋንታ የማክ ኲል አያት ዳግዳ (በትክክል «ዮካይድ ኦላጣይር») ተከተለው።

ስለ ሉግ ብዙ ሌሎች ትውፊቶች አሉ። ከኬልቶች አምላክ ሉጉስ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይታሥባል።

ቀዳሚው
ኑዋዳ
አይርላንድ (ባንባ) ከፍተኛ ንጉሥ
1474-1434 ዓክልበ. (አፈታሪክ)
ተከታይ
ዮካይድ ኦላጣይር