Jump to content

ፎሞራውያን

ከውክፔዲያ

ፎሞራውያን (አይርላንድኛ፦ Fomoire) በአየርላንድ አፈ ታሪክ በጥንታዊ አይርላንድ ከማየ አይኅ በኋላ የተገኘ ወገን ነበሩ። መጀመርያው ሠፋሪ ፓርጦሎን 10 አመት ከደረሰ በኋላ ሥራዊቱ በማግ ኢጠ ውግያ (2274 ዓክልበ. ግድም) እንዳሸነፉቸው በሌቦር ገባላ ኤረን («የአይርላንድ ወረራዎች መጽሐፍ» 1100 ዓ.ም. ግድም) ይተረካል። እነዚህ ፎሞራውያን በመሪያቸው ኪቆል ግሪከንቆስ ተመርተው ከውጭ አገር የወረሩ መርከበኞች ነበሩ። የፎሞራውያን ቁጥር 800 እንደ ነበር ይጨምራል። የኪቆል ትውልድ ወልደ ጎል ወልደ ጋርብ ወልደ ቱዋጣሕ ወልደ ጉሞር ሲሆን «ስሊቭ ጉሞር» (ወይም ኡሞር ወይም ኤሞር) ከተባለ ሀገር እንደ መጡ ይባላል።

ከ300 ዓመት በኋላ ግን የፓርጦሎን ሕዝብ በሙሉ በቸነፈር ጠፉ። በ1954 ዓክልበ. ግድም የፓርጦሎን ዘመድ የነበረው ነመድ በአይርላንድ ደርሶ ፎሞራውያንን አሸነፋቸው። ነመድ የፎሞራውያንን ነገሥታት (ጋንና ሴጋን) ገደላቸው። ከነርሱ በኋላ 2 አዲስ መሪዎች (ኮናንድና ሞርክ) ተነሡ፤ የፎሞራውያን አምባ የኮናንድ ግንብ በቶሪ ደሴት ላይ ነበር። በ1945 ዓክልበ. ነመድ እራሱ ከቸነፈር ሞተ። በ1738 ዓክልበ የነመድ ተወላጅ ፈርጉስ ሌስደርግ ከ60 ሺህ ሰው ሥራዊት ጋር የኮናንድን ግንብ አጠፋ፣ ሞርክ ግን ተመልሶ አሸነፋቸው። ከዚያ ፎሞራውያን የቀሩትን ነመዳውያንን ለ200 ዓመታት በከባድ አስገበራቸው። ከከብታቸው፣ ከምርታቸውና ከልጆቻቸውም 2 ሢሶ ለፎሞራውያን ማቅረብ ነበረባቸው ማለት ነው። በመጨረሻ በ1538 ዓክልበ. ግድም ፊር ቦልግ የተባለው ወገን አይርላንድን ከፎሞራውያን ያዘ።

በ1625 ዓ.ም. አካባቢ የታተመው የሴጥሩን ኬቲን ታሪክ መጽሐፍ የአይርላንድ ታሪክ እንደሚለው ፎሞራውያን ከካም ዘር የወጡ መርከበኞች ነበሩ። በእንግሊዝ ታሪክ ጸሐፊ ራፋኤል ሆሊንስሄድ ዜና መዋዕል (1569 ዓ.ም.) ደግሞ የ'ረጃጅሙ ሰዎች ወገን' መሪ አልቢዮን ታላቅ ብሪታንያ ከኬልቶች ንጉሥ ባርዱስ በ2083 ዓክልበ. ግድም ያዛ፤ ወንድሙም በርጊዮን በአይርላንድና በኦርክኒ ደሴቶች ገዛ። በ1992 ዓክልበ. ግድም ሄርኩሌስሮን ወንዝ (ፈረንሳይ) በሆነ ውግያ አልቢዮንን በርጊዮንን ገደላቸው፤ ረጃጅሞችም ለጊዜው ያለ መሪ ኖሩ።